አልኮል ሽያጭ

6 መጋቢት 2023, 10:24 EAT

በኢራቅ የአልኮል መጠጥ ሽያጭ እና ወደ አገር ውስጥ ማስገባት መከልከሉ ዴሞክራሲያዊ አይደለም ሲሉ የክርስቲያን ፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃወሙ።

ኢራቅ ከአንድ ወር በፊት የአልኮል መጠጥን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት፣ በአገር ውስጥ ማምረት እና መሸጥ የሚከለክል ሕግ አውጥታ የነበረ ሲሆን የአገሪቱ ገቢዎች ባለስልጣን ሕጉን ከትናንት የካቲት እሁድ 26/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚ ማድረግ ጀምረዋል።

ይሁን እንጂ በአገሪቱ ፓርላማ አምስት መቀመጫዎች ያላቸው ክርስቲያን ፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ ውሳኔውን ለመቀልበስ ጥረት እያደረጉ ነው።

በአብዛኛው የሙስሊም አገር በሆነችው ኢራቅ አልኮል መጠቀም በማሕብረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የለውም፤ ይሁን እንጂ ሰዎች ፍቃድ ካላቸው መጠጥ ቤቶች በይፋ አልኮል መግዛት ይችሉ ነበር።

እአአ 2016 በአገሪቱ ፓርላማ ጸድቆ የነበረ ሕግ የአልኮል መጠጥ ሽያጭ፣ ምርት እና ወደ አገር ማስገባትን ይከለክል ነበር። ይህ ሕግ ከወጣ ከዓመታት በኋላ ተፈጸሚ መሆን እንደሚጀምር የታወቀው ሕጉ በጋዜጣ ከታተመ በኋላ ነው።

ሕጉ ምን ያክል በጥብቅ ተፈጻሚ ይሆናል የሚለው ግልጽ ባይሆንም በሕጉ መሠረት አልኮል ወደ አገር ያስገባ፣ የመረተ ወይም የሸጠ እስከ 15ሺህ የእንግሊዝ ፓወንድ የሚደርስ የገንዝብ ቅጣት ይጠብቀዋል።

ባብሎን ሙቭመንት የተባለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባቀረቡት አቤቱታ ሕጉ የአነሳዎችን መብት እና ነጻነት የሚጋፋ በመሆኑ ሕገ-መንግሥታዊ አይደለም ብለዋል።

ይህ ሕግ የአልኮል ሽያጭ በጥቁር ገበያው እንዲደራ ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።