አቶ ጌታቸው ረዳ

6 መጋቢት 2023, 12:45 EAT

በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት ይቋቋማል የተባለው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አለመመስረቱን ህወሓት አስተባበለ።

የህወሓት ቃል አቀባይ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ጥቅምት ወር ፕሪቶሪያ ላይ የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሟል የተባለው ሐሰት ነው ብለዋል።

ለሁለት ዓመት የተካሄደው ደም አፋሳሹ የሰሜን ኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት የተቋጨው የፌዴራል መንግሥት እና ህወሓት ጦርነት ለማቆም ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. ደቡብ አፍሪካ ላይ የሰላም ስምምነት ከፈረሙ በኋላ ነው።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተመስርቷል መባሉን በተመለከተ የህወሓት ቃል አቀባይ ማስተባበያ የተሰማው ፓርቲው 28 አባላት ያሉት ጊዜያዊ አስተዳደር አቋቁሟል የሚል ዜና መሰማቱን ተከትሎ ነው።

የህወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት ጌታቸው ረዳ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚቋቋመው የፕሪቶሪያ ስምምነትን የፈረሙ አካላት ከተወያዩ በኋላ ነው ብለዋል።

“ካለ አዲስ አበባ [ማዕከላዊው መንግሥት] ተሳትፎ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁማል የሚባለው ከእውነት የራቀ ነው። ትግራይ የራሷን ሚና ብቻ እየተጫወተች ነው” ነው ሲሉ ጌታቸው ረዳ እሑድ ዕለት በትዊተር ገፃቸው ላይ ፅፈዋል።

የ Twitter ይዘትን ይለፉት

ይዘቱን Twitter ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በTwitter. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የTwitter ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።Accept and continueየቪዲዮ መግለጫ,ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

የ Twitter ይዘት መጨረሻ

ከሳምንታት በፊት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሚያስችል ኮሚቴ መቋቋሙ ይታወሳል። ይሁን እንጂ ይህን ኮሚቴ በህወሓት እና በትግራይ ኃይሎች አማካይነት የተቋቋመ አካታች ኮሚቴ አይደለም የሚል ትችት በፖለቲከኞች እና በምሁራን ትችት ሲሰነዘርበት ነበር።

ምንም እንኳ የህወሓት ከፍተኛ አመራር የተቋቋመ ጊዜያዊ አስተዳደር የለም ይበሉ እንጂ፣ በትግራይ ክልል ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁሉን አካታች የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ሲጠይቁ ቆይተዋል።

ፓርቲዎች የትግራይ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ከደረሰበት ውድመት እንዲያገግም ሁለን ያሳተፈ ጊዜያዊ አስተዳደር ያሻል ይላሉ።

ፓርቲዎቹ ህወሓት ጊዜያዊ አስተዳደር የመመስረት ሂደትን በበላይነት ተቆጣጥሮታል ሲሉ ቅሬታቸውን ያሰማሉ።

የፕሪቶሪያ ስምምነት ምን ይላል?

የፌዴራል መንግሥት እና የህወሓት ተወካዮች ባለፈው ጥቅምት ወር በደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶሪያ ተገናኝተው የሰላም ስምምነት መፈረማቸው ይታወሳል።

የስምምነቱ ፈራሚዎች ድጋሚ በኬንያ መዲና ናይሮቢ ታኅሣሥ ወር ተገናኝተው የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚያጠናክር ፊርማ አስፍረዋል።

ሁለቱ አካላት ደቡብ አፍሪካ ላይ በደረሱት ሰምምነት በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚመሰረት ተገልጿል።

የፕሪቶሪያው ስምምነት አንቀፅ 10 (1) ሁሉን አካታች የሆነ የትግራይ ጊዜያዊ ክልላዊ አስተዳደር የሚቋቋመው ህወሓት እና የፌደራሉ መንግሥት በሚያደርጉት ፖለቲካዊ ውይይት ይሆናል ይላል።

ጊዜያዊ አስተዳደር የመመስረት ፖለቲካዊ ንግግር የሚደረገው በፕሪቶሪያው ስምምነት አንቀጽ 7.2 (ሐ) መሠረት ህወሓት አሸባሪ ድርጅት ተብሎ የተሰየመው ተሰርዞ የትግራይን ሕዝብ በክልል እና በፌደራል ምክር ቤቶች የሚወክሉ ዕጩዎች ምርጫ በምርጫ ቦርድ አማካይነት ይከናወናል ይላል።