–
March 5, 2023

ባሕርዳር: የካቲት 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመራጭ ተመራጮች የማጠቃለያ ውይይት በክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት እና በተወካዮች መካከል እየተካሄደ ነው፡፡ በማጠቃለያ የውይይት መድረኩ ተመራጮች አሉ ያሏቸውን ውስንነቶች እና እጥረቶች አንስተዋል፡፡
የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ተደጋጋሚ ደም አፋሳሽ ጦርነቶች ተካሂደዋል። በቅርቡ ደግሞ የሰላም ሥምምነት ተደርሶ በሁለቱ ወገኖች መካከል ተኩስ መቆሙ ይነገራል፡፡ ከሠላም ሥምምነቱ ማግስት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ውስጥ አሁንም ድረስ ሁለት ወረዳዎች ነጻ አልወጡም ያሉት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የተከበሩ ወይዘሮ ፀሃይነሽ ገብሬ ናቸው፡፡
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የአበርገሌ እና ጻግብጅ ወረዳዎች አሁንም በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ናቸው ያሉት የተከበሩ ወይዘሮ ፀሐይነሽ “የሁለት ወረዳ ሕዝብ አሁንም ድረስ ነጻ አልወጣም፤ ሰብዓዊ ድጋፍም ማድረስ አልተቻለም” ብለዋል፡፡ አፋጣኝ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ምንም አይነት ድጋፍ እየቀረበ አይደለም ያሉት የምክር ቤት አባሏ የክልሉ መንግሥት ከፌደራል መንግሥት ጋር ችግሩን በጋራ ለመቅረፍ የሄደበትን ርቀት ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
- “ወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮቻችን ቅቡልነት ያለው የሀገረ መንግሥት ምስረታ ሥራችን…
- ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን…
- በከተማዋ የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ሥራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንደሚጠናቀቁ…
- “የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ችግሮችን ለመፍታት የምክር ቤት አባላት ሕዝባዊ…
በጦርነቱ ከአማራ ክልል በላይ ጉዳት የደረሰበት አካባቢ የለም ያሉት የተከበሩ ወይዘሮ ፀሐይነሽ ከሥምምነት በኋላ የሚደረገው ድጋፍ የደረሰውን ችግር የሚመጥን አይደለም ነው ያሉት፡፡ አሁንም ከ67 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በሰቆጣ ጊዜያዊ መጠለያ እንዳሉ ገልጸው ተፈናቃዮቹ ያሉበት ኹኔታ ሲገልጹም “አሳዛኝ ነው” ብለውታል፡፡
የክልሉ መንግሥት የሰሜን ኢትዮጵያን ግጭት ተከትሎ የሠላም ሥምምነት ላይ መድረሱ ተቀብሎ ለሠላም እየሠራ ነው ብለዋል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ(ዶ.ር)። በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በትግራይ ኃይሎች በተያዙ ሁለት ወረዳዎችም ለጊዜው የሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት እንዲደርስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው