በየዓመቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ ዩኬ ይገባሉ
የምስሉ መግለጫ,ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ 45ሺህ ስደተኞች በጀልባ ወደ ዩኬ ገብተዋል

ከ 8 ሰአት በፊት

በዩኬ ለአገር ውስጥ ሚኒስቴር ልዩ ሥልጣን ተሰጠው፤ ይኽም ማንኛውም ከእንግዲህ ወደ ዩኬ የሚገባ ሕገ ወጥ ስደተኛን ጨርሶ የማባረር ሥልጣን ነው።

ይህ ረቂቅ ሕግ ዛሬ ማክሰኞ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ‘ዘ ሰን’ ጋዜጣ ላይ ጉዳዩን አስመልክተው በጻፉት ሐተታ ‘ይህ ሕግ አገሪቱ ውስጥ ላሉትም ሆነ ሕጋዊ የጥገኝነት ጥያቄ ለሚያቀርቡ ፍትሐዊነትን የሚያረጋግጥ ነው’ ብለዋል።

ተቀናቃኛቸው የሌበር ፓርቲ መሪ ሰር ስታመር ግን ሕጉ “መናኛና የማይሠራ” ሲሉ ተችተውታል።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ 45ሺህ ስደተኞች በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ዩኬ ገብተዋል።

እነዚህም ከአውሮፓ በተለይም ከፈረንሳይ በጀልባ ተጭነው የገቡ ናቸው።

ይህ አሐዝ በ2008 ዓ/ም በፈረንጆች 300 ብቻ ነበር።

በየጊዜው በጀልባ ወደ ዩኬ እየገቡ ያሉ ስደተኞች በመንግሥት ላይ ጫና አሳድረው ቆይተዋል።

ጉዳዩ በአገሪቱ ፖለቲካ ቁልፍ አጀንዳ ሆኖም ቆይቷል።

ከዚህ ቀደም ዩኬ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ ሐሳብ ነበራት። ይህ ሐሳብ ገና ከመጀመሩ ተጨናግፏል።

በአዲስ ዕቅድ መሠረት የዩኬ አገር ውስጥ ሚኒስቴር (Home Secretary) እነዚህን ስደተኞች በገቡበት ፍጥነት ከአገር ማስወጣት ብቻ ሳይሆን ከዚያ በኋላ በምንም ዓይነት ወደ ዩኬ እንዳይገቡ እግድ የመጣል ሥልጣንን ይሰጣል።

ይህም ማለት አዲሱ “የማባረር ሥልጣን’ ከዚህ በፊት በዩኬ ይሠራበት የነበረውን ‘ማንኛውም አገሪቱን የረገጠ ሰው ጥገኝነት የመጠየቅ መብት’ የሚተካ ይሆናል።

አዲሱ ሕግ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑና የጤና ሁኔታቸው አሳሳቢ ለሆኑ ሰዎች ተፈጻሚነት ላይኖረው ይችላል።

በዚህ አዲስ ሕግ ከአገር የተባረረ ስደተኛ ከዚያ በኋላ በምንም ሁኔታ የእንግሊዝ ዜግነት አያገኝም።

ይህ ሕግ ዛሬ ማክሰኞ ከጸደቀ በኋላ ለወራት ሥራ ላይ ባይውልም ከዛሬ ጀምሮ ወደ ዩኬ በሚገቡ ማናቸውም ሕገ ወጥ ስደተኞች ላይ ወደ ኋላ ተመልሶ ተፈጻሚነት ይኖረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ “አገራችን ዩኬ ስደተኞን የማስጠለል አኩሪ ታሪክ ያላት አገር ናት’ ካሉ በኋላ ነገር ግን ይህ ተግባር በሕገ ወጦች መበዝበዝ እንደሌለበት አስምረውበታል።

እርሳቸው እንደሚሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብዙ ቁጥር በጀልባ ወደ ዩኬ እየገቡ ያሉት ስደተኞች የደኅንነት አደጋ የተጋረጠባቸው ሐቀኛ ስደተኞች አይደሉም።

ይልቅ በአውሮፓ አገራት ሲዘዋወሩ ቆይተው በመጨረሻ ወደ ዩኬ በጀልባ ለመግባትና ለመኖር የወሰኑ ‘ሕገወጦች’ ናቸው ሲሉ ‘ዘ ሰን’ ጋዜጣ ላይ ጽፈዋል።

ይህ አዲስ ረቂቅ ሕግ ተግባራዊ ሲሆን የሕገ ወጥ አስተላላፊዎችን ወሽመጥ የሚበጥስ ይሆናል ይላሉ ሱናክ።

ለዴይሊ ኤክስፕረስ አስተያየት የሰጡት የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ሱላ ብሬቨርማን አዲሱ ሕግ ‘ዓለም አቀፍ ስደተኞችን የመቀበል ሕግን የሚገዳደርበት ሁኔታ እንዳለ ካመኑ በኋላ ነገር ግን ችግሩን ለማቆም ሁነኛው መንገድ ይህ ነው ብለዋል።

አዲሱ ስደተኞችን የማባረር ዕቅድ በመብት ተሟጋቾችና በተቀዋሚ ፓርቲዎች እየተተቸ ነው ያለው።

ሪሽ ሱናክ ወደ ሥልጣን ሲመጡ በተለይ 5 ቁልፍ ተግባራትን እንደሚያከናውኑ ቃል ገብተው ነበር፤ ሦስቱ ከኢኮኖሚ ጋር የሚያያዙ ሲሆኑ አንዱ ከብሔራዊ ጤና አገልግሎት ጋር የሚገናኝ ነው።

ሱናክ በ5ኛ ደረጃ ቃል የገቡት ደግሞ በጀልባ ወደ ዩኬ በሕገ ወጥ መንግድ የሚገቡ ስደተኞችን እስከናካቴው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም ነበር።