
ከ 4 ሰአት በፊት
የቻይናና የአሜሪካ ግንኙነት በጣም የተዛባና ግጭት ሊፈጥርም የሚችል ነው ሲሉ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስጠነቀቁ።
“ቻይናን መቆጣጠር እና ማፈን አሜሪካን ታላቅ አያደርጋትም። የቻይናን መበልጸግና መታደስ አያቆምም” ሲሉም ኪን ጋንግ ተናግረዋል።
በአሜሪካ የቀድሞ የቻይና አምባሳደር ኪን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላ የመጀመሪያ መግለጫቸውን ማክሰኞ፣ የካቲት 28/ 2015 ዓ.ም ሰጥተዋል።
በተለይም በቅርቡ በግዛቴ ሲሰልል ነበር ያለችውን የቻይና ፊኛ አሜሪካ ማፈንዳቷን ተከትሎ የሃያላኑን መንግሥታት አለመግባባት ከፍ አድርጎታል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃገራቱን ግንኙነት ለማሻሻል ጥረት ቢደረግም ፍሬ ማፍራት አልቻለም።
“አሜሪካ፣ ቻይናን እንደ ተቀዳሚ ተቀናቃኝ እና የጂፖኦለቲካዊ ተግዳሮች አድርጋ ነው የምትመለከታት። ይህ ዕይታ ስህተት ነው ፤ በምሳሌ ብናየውም የሸሚዝ ቁልፍ የመጀመሪያው ከተዛነፈ ሁሉም ይዛነፋል” ብለዋል።
አዲሱ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይህንን ያሉት በሃገራቱ መካከል ያለው መካረር እየጨመረ ባለበት ወቅት ጤናማ ግንኙነት መመስረት ይቻላል ወይ? በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው።
- የኤርትራ ጦር ከትግራይ የመውጣቱ ሂደት አዝጋሚ መሆኑን ተመድ ገለጸከ 5 ሰአት በፊት
- ኢትዮጵያ ነፍሰ ጡሮች ከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ከሚያጋጥማቸው አገራት ተርታ ተመደበችከ 4 ሰአት በፊት
- እስከ 18 ዓመቱ ማንበብ እና መጻፍ ሳይችል የቆየው በእድሜ ትንሹ ፕሮፌሰር ለመሆን በቃከ 9 ሰአት በፊት
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በቡድን 20 ጉባኤ ላይ ሁለቱ ሃገራት የጥበቃ ሃዲድ እንዲያበጁ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህንንም አስመልክቶ ምላሽ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “ቻይና በምትተነኮስበት ወቅት አጸፋዊ እርምጃዎችን በቃላት ወይም በተግባር እንዳትመልስ ለማድረግ ነው” ብለዋል። ፕ
ሬዚዳንት ባይደን” ከቻይና ጋር ብትወዳደርም ግጭት አትፈልግም” ብለው ነበር።
“አሜሪካ ቆም ብላ ካላሰበችና በተሳሳተ መንገድ መጮኋን ከቀጠለች ምንም አይነት የጥበቃ ሃዲድ ቢበጅም መገለባበጡን ሊያቆመው አይችለም። ወደ ግጭትና ሁከት ውስጥ መገባቱ አይቀርም። ይህንን መዘዝ የሚሸከመው ማን ነው?” ሲሉም ጠይቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም በፊኛው ክስተት የተፈጠረውን ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ማስቀረት ይቻል እንደነበር ጠቅሰው ነገር ግን አሜሪካ የወሰደችው እርምጃ “ጥፋተኛ እንደሆንን በማመን ነው” ብለዋል።
አሜሪካ የተጠረጠረውን የስለላ ፊኛ “የአሜሪካን ሉዓላዊነት በግልፅ የጣሰ” ስትል ገልጻዋለች። ቻይና በበኩሏ ፊኛው የሷ መሆኑን ብታምንም የሲቪል እንደሆነና ስለ አየር ንብረትም መረጃ የሚሰበስብ ነው ብላለች።