
7 መጋቢት 2023
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመመርመር ሦስት አባላት ያሉት ኮሚሽን ተቋቁሟል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች ከጦር ወንጀል ጋር የሚስተካከሉ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስለመፈጸማቸው ኮሚሽኑን ጨምሮ ሌሎች ድርጅቶች ባወጧቸው ሪፖርቶች አሳውቀዋል።
የሠላማዊ ሰዎች ግድያ፣ አስገድዶ መድፈርን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀም እና ሌሎች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተፈጸሙ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ጥሰቶቹ ከጦር ወንጀል ጋር የሚስተካከሉ ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ ነበር።
ኢትዮጵያ ኮሚሽኑን ከምሥረታው ጀምሮም ከመቃወም ባለፈ በጀት እንዳያገኝ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።
በቅርቡ በአዲስ አበባ ተካሂዶ በነበረው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ ኮሚሽኑ እንዲበተን የምታደርገውን ጥረት እንዲደግፉ ለኅብረቱ አባላት ጥሪ አቅርበዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በጄኔቭ ለአምስት ሳምንታት በሚያካሂደው ስብሰባው ስለሰሜን ኢትዮጵያ ጉዳይ እንደሚወያይ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ ኮሚሽኑ ሥራው እንዲቋረጥ ጥሪ ለማቅረብ መዘጋጀቷም ተገልጿል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል ኢትዮጵያ ለምታቀርበው የውሳኔ ሐሳብ ድጋፍ እያሰባሰበች ስለመሆኑ ዲፕሎማቶች ነገረውኛል ሲል ዘግቧል።
ዓለም አቀፍ ሲቪል ማኅበራት እና የመብት ተሟጋች የኢትዮጵያን ጥረት ‘ያልተጠበቀ’ እና ዓለም አቀፍ ምርመራን ለማስቀረት የሚደረግ ጥረት ነው ብለውታል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዋችን ጨምሮ ሌሎችም ከስድሳ በላይ የሚሆኑት ተቋማት ለተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ፤ ኢትዮጵያ ምርመራው እንዲቋረጥ የውሳኔ ሃሳብ ለማቅረብ ማቀዷ አሳስቦናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጥረት የምክር ቤቱ አባላት እንዳይቀበሉትም ጥሪ አቀርበዋል።
- በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ረሃብ፣ መደፈርና ሌሎች ጥሰቶች እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን የተመድ ሪፖርት ይፋ አደረገ20 መስከረም 2022
- ስለሽግግር ወቅት ፍትህ የምናውቃቸው አምስት ነጥቦች1 መጋቢት 2023
- ከሰላም ስምምነቱ በኋላም የኤርትራ ወታደሮች በመድፈር ወንጀል ተከሰሱ15 የካቲት 2023
የተፈፀመውን ወንጀል ማን ይመርምር?
ከስድሳዎቹ ተቋማት አንዱ የትግራይ አክሽን ኮሚቴ ነው።
ከ35 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ከነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ወደ ሱዳን ከሸሹ ቤተሰቦች በስደተኞች ጣቢያ እንደተወለደች የምትገልጸው ሐውዜን ገብረመድኅን መሠረቱን አሜሪካን ካደረገውና በሰብዓዊ እርዳታ እና አድቮኬሲ ዙሪያ የተሠማራው የትግራይ አክሽን ኮሚቴ ተባባሪ መስራች ናት።
በትግራይ ‘የዘር ፍጅት’ ተፈጽሟል ብላ የምታምነው ሐውዜን “ወንጀል ፈጻሚው አካል ወንጀሉን እንዲያጣራ መፍቀድ አንችልም። በትግራይ ከ500 ሺህ በላይ ሰው ተገድሏል፤ መቶ ሺህ ሴቶች ተደፍረዋል።
ለዚህ ዋናዎቹ ተጠያቂዎች ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ተባባሪው የነበረው የኤርትራ መንግሥት ናቸው። ስለዚህ ራሳቸው ቢያጣሩት ግልጽነት እንደማይኖረው እናውቃለን” ስትል ተዓማኒነቱ ላይ ጥያቄ ታነሳለች።
በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ሰብዓዊ እና ሕገ መንግሥታዊ ጥሰቶች ተፈጽመዋል ብለው እንደሚገምቱ የሚገልጹት የሕግ ባለሙያው አቶ ባይሣ ዋቅወያ ናቸው። አቶ ባይሣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሠላም እና የግጭት አፈታት ዙሪያ ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ ሠርተዋል።
የሕግ ባለሙያው “ከማንኛውም ጫና ነጻ እና ገልልተኛ በሆነ አካል ጥልቅ ምርመራ ያስፈልጋል” ከሚሉት ወገንም ናቸው።
ለአቶ ባይሣ ጥያቄው “ማን ይመርምር? እንዴት ይመርመር?” የሚለው ነው።
የኮሚሽኑ መቋቋምን ኢትዮጵያ ለምን ከጅምሩ ተቃወመች በሚል በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኘው በርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካ፣ ፌደራሊዝም እና በልማት ጉዳዮች ትንታኔ በመስጠት የሚታወቁት ዶ/ር ብዙነህ ይመኑን ጠይቀናቸዋል።
“መርማሪ ቡድኑ የተቋቋመው ኢትዮጵያ በምዕራባውያን ከፍተኛ ጫና ውስጥ በነበረችበት ወቅት በመሆኑ ኮሚሽኑ ኢትዮጵያን የማንበርከኪያ ዘመቻ እና የፖለቲካ መሣሪያ አካል ሆኖ ታሳቢ ተደርጓል” ይላሉ።
በኮሚሽኑ ገለልተኝነት ላይ ካላት ጥያቄ በተጨማሪ “የኮሚሽኑ ምርመራ ተጠያቂነት ሊያስከትል መቻሉ ነው” ለመቃወሟ ምክንያት ሲሉ ያስረዳሉ።
በሌላ በኩል በሰዓዊ መብት ጥሰት የሚከሰሱት የትግራይ ኃይሎችም ኮሚሽኑን ሲቀበሉት ቆይተዋል።
“ህወሓት ኮሚሽኑ ምርመራውን ከጀመረ የሚያጣው ምንም የለም ወይም አነስተኛ ነው። አብዛኛው ጦርነቱ የተካሄደው ትግራይ ክልል ውስጥ በመሆኑ ብዙዎቹ ተጎጂዎች የትግራይ ተወላጆች ናቸው። በዚህ ምክንያት ህወሓትን በትንሹ ብቻ ተጠያቂ ይሆናል በሚል አመክንዮ ኮሚሽኑን እንዲቀበል ሊያበረታቱት ይችላሉ“ ይላሉ ዶ/ር ብዙነህ።

የሽግግር ወቅት ፍትሕ
ኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ፍትሕን እንደ አንድ አማራጭ አቅርባለች።
የመንግሥትን ሃሳብ በበጎ ጎኑ የሚያዩት ዶ/ር ብዙነህ “ዓላማው እውነትን ማስፈን፣ ተጎጂዎችን መካስ፣ እርቅ እና ትምህርቶችን መውሰድ ከሆነ ፖሊሲው ስኬታማ ሊሆን ይችላል” ይላሉ።
ውጤታማነቱ የሚወሰነው መንግሥት በሚኖረው ቁርጠኝነት እና ገለልተኛ አካል መቋቋም ላይ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
“አገሪቱ እውነተኛ ነጻ ተቋማት የማቋቋም ታሪክ የላትም። በዚህም የሽግግር ወቅት የፍትሕ ኮሚሽኑ ራሱን ችሎ ለመሥራት ይከብደዋል” ሲሉ ስጋታቸውንም ጨምረው ይገልጻሉ።
ለሕግ ባለሙያው አቶ ባይሳ የሽግግር ወቅት ፍትሕ ከተራው የፍትሕ ሂደት ጋር የሚተካካ ሳይሆን “ጎን ለጎን ሊሄድ የሚችል ነው።”
“በሽግግር ወቅት ፍትሕ ስም ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ይቅርታ የሚደረግላቸው ምክንያት የለም። ለፍርድ ቀርበው ከተፈረደባቸው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይቅርታ ሊደረግላቸው ይችላል።”
“የሽግግር ወቅት ፍትሕ ማኅበረሰቡ ወደፊት ቂም እና በቀል ይዞ እንዳይኖር የሚያደርግ ሂደት እንጂ ወንጀለኞችን ነጻ የሚያደርግ ሌላ ተተኪ ወይም አማራጭ የፍትህ ሂደት አለመሆኑን ሕብረተሰቡ ሊያውቅ ይገባል” ይላሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባይቀበለውስ?
ሌላው የመንግሥታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ መንግሥትን ጥያቄ ካልተቀበለ ምን ሊከሰት ይችላል? የሚለው ነው።
ኢትዮጵያ ውሳኔው ውድቅ ልታደርግ ትችላለች የሚሉት ዶ/ር ብዙነህ “ድርጅቱ ወይም ምዕራባውያን አገሪቱ ውሳኔውን እንድትቀበል ለማስገደድ በማዕቀብ ሊያስፈራሯት ወይም ማዕቀብ ሊጥሉባት ይችላሉ” ይላሉ።
ይህ ደግሞ ከሠላም ስምምነቱ በኋላ መልክ መያዝ በጀመረው የአገሪቱ ኢኮኖሚ እና ዲፕሎማሲ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።
ኢትዮጵያ ካልተስማማች በስተቀር ኮሚሽኑ ዓላማውን ለማሳካት ዕድል አያገኝም። በዚህ ሁኔታ የተገኘ ውጤት ደግሞ ሁሉንም አካላት ባለማሳተፉ ገለልተኛነቱ ጥያቄ ይገባና አከራካሪ ሊሆን ይችላል።
“የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዓለም አቀፋዊ ባህሪይ አለው” ለሚሉት አቶ ባይሣ ዓለም አቀፍ ተቋማት የተደረገው ጥሰት ያገባኛል ሊሉ ይችላሉ ሲሉ ያስረዳሉ።
እንደ አቶ ባይሣ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ ሉዓላዊ አገር የውጭ አካል በውስጥ ጉዳዩ ገብቶ ልመርምር ማለት አይችልም ማለት ይችላል።
ይህ ጫና ሊበረታ እንደሚችል በመግለጽም ከዚህ ይልቅ አማራጭ ማየት የተሻለ እንደሆነ ያወሳሉ።
“የተባበሩት መንግሥታትም እኔ ብቻ ልመርምር የሚለውን ትቶ፣ ኢትዮጵያም እኔ ብቻ በማለት ድርቅ ከማለት አማራጭ መፍጠር ይቻላል” ሲሉ ሃሳባቸውን ያስረዳሉ።
እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ከፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት በኋላ መንገድ የያዘ የመስለው የኢትዮጵያ እና የምዕራባዊያን ግንኙነት በዚህ ምክንያት ሊቀዛቀዝ ይችላል።
በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት እና የተንገዳገደውን ኢኮኖሚ ለማደስ የገንዘብ ድጋፍ ያስፈልጋል።
“ኢትዮጵያ ለስምምነቱ ራሷን ተገዢ በማድረግ ያልተገደበ የሰብዓዊ አቅርቦትን በማረጋገጥ፣ የሽግግር ወቅት ፍትህን በማመቻቸት እና ለገለልተኛ ሚዲያዎችን ፈቃድ በመስጠት ፈተናውን ልታልፍ ትችላለች።
“ጥቅማቸውን የሚያስቀድሙት ምዕራባውያንም የተረጋጋች ኢትዮጵያን ማየት አንዱ ፍላጎታቸው ነው። የዐቢይ አስተዳደር ሌሎች ግጭቶችን ከፈታ እና አገሪቱን ካረጋጋ ጫናው ይቀንሳል” ይላሉ።
ኢትዮጵያ “የኮሚሽኑ ሥልጣን የፕሪቶሪያ የሠላም ስምምነትን ተግባራዊነት ያሰናክላል” ትላለች።
አስተያየት ሰጪዎቹም የኮሚሽኑን ግዴታዎች ከግምት በማስገባት የፕሪቶሪያው ስምምነት አተገባበር ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል ይላሉ።
“በተለይም የሠላሙ ሂደት ገና ጅምር ላይ በመሆኑ እና በግጭቱ ውስጥ ያሉ አካላት አሁንም መተማመንን መፍጠር ባለመቻላቸው፤ ከኮሚሽኑ ሊመጡ የሚችሉና አንዱን ወገን የሚወቅሱ መረጃዎች እንደ ጥቃት ሊወሰዱ ይችላሉ። በተጨማሪም የኮሚሽኑ ሥልጣን ከክልል መንግሥታት ጋር እንዲገናኝ ያደርገዋል።
“የፕሪቶሪያ ስምምነት የአንድ ወገን ተሳትፎን የሚከለክል መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት በኮሚሽኑ ፍላጎት ሳይሆን በሠላም ስምምነቱ መሠረት የኮሚሽኑ ሥልጣን ያልተረጋጋ ይመስላል” ሲሉ ዶ/ር ብዙነህ ይገልጻሉ።
የአፍሪካ ኅብረት የፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት እንዲደረስ ቀዳሚ ሚና ነበረው። በዚህ ምክንያት “አባል አገራት እና ኅብረቱ ኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ፍትሕን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት የሚደግፉበትን ዘዴ ሊያመቻቹ ይችላል” ይላሉ።
አገራቱ ተመሳሳይ ምርመራ ለምን አፍሪካ ላይ ብቻ የሚል አቋም ይዘው ከተነሱ ጉዳዩ አወዛጋቢ ሊሆን ይችላል የሚሉት አቶ ባይሣ “መሠረታዊው ነገር ወንጀሎች ተፈጽመዋል፤ ወንጀለኞቹ መቀጣት አለባቸው ላይ ከተስማማን እንዴት እንመርመር የሚለው ላይ አማራጮችን መጠቀም ነው እንጂ አያስፈልግም ብቻ አያዋጣም” ብለዋል።
ሁለቱም ባለሙያዎች የሚስማሙበት ነገር ኢትዮጵያ ውሳኔውን ካልተቀበለች ቡድኑ ለመመርመር ከባድ ሊሆንበት ይችላል የሚለውን ነው።
ሁለቱ አካላት ካልተባበሩ ደግሞ የምርመራው ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ለዶ/ር ብዙነህ “እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በጣም አስፈሪ እና የማይፈለግ ነው።”
“እኔ እስከማውቀው ድረስ ኮሚሽኑ መጥቶ አይመረምርም ነው እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት ወንጀሉ አልተከሰተም አይልም። እኔ በግሌ ከባድ የሰው ልጆች መብት ጥሰት በሰሜን ኢትዮጵያ ተፈጽሟል። እነዚህ መመርመር አለባቸው። ሕዝቡ ይህንን ማወቅ አለበት። [በማንም ይሁን በማን] ጥፋቱን የፈጸሙት መቀጣት አለባቸው። ማን ይመርመር በሚለው ብቻ አላስገባም ማለቱ ከባድ ነው” ያሉት ደግሞ አቶ ባይሣ ናቸው።
“ለትግራይ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ሠላም የሚያመጣ ከሆነ የሽግግር ወቅት ፍትህ እደግፋለሁ” የምትለው ሐውዜን፣ በጦርነቱ የተፈጸሙት ወንጀሎች የማጣራት ጉዳይ ግን ለሦስተኛ ወገን መተው አለበት ባይ ናት፡፡
“ያለ ተጠያቂነት ወደፊት መጓዝ አንችልም። ሠላም እንዲኖር ፍትሕ መኖር አለበት” ብላለች፡፡