March 7, 2023 

በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ ለአራት ዓመት ሙሉ በቀጠለው ድርቅ የተነሳ ሰዎች እየሞቱ እንደሆነ የልዩ ወረዳው የግብርና ጽህፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ ገለጸ፡፡

አስከፊ በሆነው ድርቅ ምክንያት ከ96 ሺሕ 800 በላይ ዜጎች አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የጠቀሰው ጽህፈት ቤቱ፣ በዚህ የተነሳ በተለይ ከረሃብ ጋር ተያይዞ በሚፈጠሩ በሽታዎች በየቀኑ ሰዎች እየሞቱ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

ዜጎች በረሃብ ምክንያት በሽታዎችን መቋቋም ባለመቻላቸው፣ መሞት በሌለባቸው በሽታዎች ጭምር እየሞቱ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

በተለይ ሕጻናት እና እናቶች ለከፋ የረሃብ አደጋ ተጋልጠዋል ያለው ጽህፈት ቤቱ፣ ክልሉም ሆነ የፌደራል መንግሥቱ ለአካባቢው ድርቅ የሰጡት ምላሽ እጅግ አናሳ እና ተስፋ አስቆራጭ ነው ብሏል፡፡

100 ሺሕ የሚጠጋ የድርቅ ተጎጂዎች ባሉበት አማሮ ልዩ ወረዳ ከግንቦት ወር ወዲህ የቀረበ እርዳታ እንደሌለም ተመላክቷል፡፡

የአማሮ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ቅድመ ማስጠንቀቂያ እና የአደጋ መከላከል ሥራ ሂደት ቡድ መሪ ሀብታሙ አሬዶ፣ ድርቁ በደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በስፋት መኖሩን ጠቅሰው፤ በተለይ በአማሮ፣ ቡርጂ፣ ኮንሶ እና ደራሼ አካባቢዎች ያለው ድርቅ ከሌሎች በጣም የከፋ ነው ብለዋል፡፡

በደቡብ ክልል በጌዶኦ፣ በጋሞ እና በደቡብ ኦሞ ዞኖችም ብዙዎችን ለችግር የዳረገ አንጻራዊ ድርቅ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡

የከፋ ድርቅ ባለባቸው አካባቢዎች እንስሳትም እየሞቱ መሆኑን የጠቀሱት ባለሙያው፣ በአማሮ ልዩ ወረዳ ብቻ ባለፈው ሳምንት በተደረገ ሪፖርት ከ200 በላይ የቁም እንስሳት እንደሞቱ ተናግረዋል፡፡

በተለይ በልዩ ወረዳው ቆላማ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ እንስሳት ከፍተኛ ጉዳት ድርሶባቸዋል ካሉም በኋላ፣ በአጠቃላይ በሕይወት ያሉት እንስሳትም በጣም የተጎዱና አጥንታቸው ብቻ የቀሩ መሆናቸውን ባለሙያው አስረድተዋል፡፡

በአማሮ ልዩ ወረዳ ለአራት ዓመታት ሙሉ በቂ ዝናብ አለመዝነቡን ያነሱት ባለሙያው፣ ከድርቁ በተጨማሪ የሸኔ ታጣቂዎች በፈጠሩት የፀጥታ ችግር ከ44 ሺሕ በላይ ሕዝብ ተፈናቅሎ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ በድርቅ እና በጸጥታ ችግሮች ከተጎዱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ውስጥ በደቡብ ክልል ያለው ሰፊ ቢሆንም ከሌሎች አካባቢዎች አንጻር የተሰጠው ትኩረት ግን እጅግ ያነሰ ነውም ተብሏል፡፡

አዲስ ማለዳ