
ከ 5 ሰአት በፊት
በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎት ውስጥ በተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ በሶማሌ እና በደቡብ ክልል በሚገኙ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች እርዳታ እንደሚያስፍልጋቸው ባለሥልጣናት ተናገሩ።
በአሁኑ ወቅት በምሥራቅ አፍሪካ በሚገኙ አገራት ለተከታታይ ዓመታት ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ባለመዝነቡ በተከሰተ ድርቅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለከፋ የረሃብ አደጋ ተጋልጠዋል።
በኢትዮጵያም በድርቁ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የቤት እንስሳት ያለቁ ሲሆን፣ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ከምግብ እጥረት ችግር ጋር በተያያዘ የሰው ሕይወት ለአደጋ መጋለጡን ሪፖርት ተደርጓል።
በቦረና በርካቶችን ለከፍተኛ ምግብ እጥረት ከዳረገው ድርቅ በተጨማሪ በሶማሌ እና በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የተከሰተው ድርቅ አስቸኳይ ትኩረትን የሚሻ ነው ተብሏል።
የየአከባቢዎቹ ባለሥልጣናት በድርቁ ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የቤት እንስሳት ማለቃቸውን እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ለምግብ እጥረት መዳረጋቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በድርቅ ምክንያት 14 ሺህ ከብቶች ማለቃቸውን እንዲሁም ከ337 ሺህ በላይ ሕዝብ ለምግብ እጥረት መጋለጡን የዞኑ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዱባ የራ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኃላፊው በዞኑ በሚገኙ በስድስት ወረዳዎች በተከሰተ ከባድ ድርቅ ከሞቱት የቤት እንስሳት በተጨማሪ 2.3 ሚሊዮን ከብቶች ክፉኛ በመዳከማቸው መንቀሳቀስ ሳይችሉ ባሉበት ቦታ ሆነው መኖ እየቀረበላቸው ይገኛሉ ብለዋል።
- በሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ እና በሽግግር ወቅት ፍትሕ መካከል የቆመችው ኢትዮጵያ7 መጋቢት 2023
- ዘሪሁን አስፋው፡ “ማስተማርን እንደ ፀጋ የቆጠሩ፣ ማስተማርን እንደ አባትነት የተቀበሉ”ከ 9 ሰአት በፊት
- ኢትዮጵያ ነፍሰ ጡሮች ከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ከሚያጋጥማቸው አገራት ተርታ ተመደበችከ 9 ሰአት በፊት
“ባለፈው ዓመት እንዲሁም ዘንድሮ በቂ ዝናብ አልተገኘም። ይህም በእንስሳት መኖ እና ውሃ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ እጥረትን አስከትሏል። ከ337 ሺህ ሰዎች በላይ የምግብ ችግር አጋጥሟቸዋል” ይላሉ አቶ ዱባ።
በደቡብ ኦሞ ከሚገኙ 13 ወረዳዎች መካከል በስድስት ወረዳዎች ማለትም በማሌ፣ በና ጸማይ፣ ሐመር፣ ዳሰነች፣ ኛንጋቶም እንዲሁም ስላማጎ ወረዳዎች “ከፍተኛ ችግር ተከስቷል” ብለዋል።
በና ጸማይ፣ አሌ እና ሐመር ወረዳዎች የውሃ ምንጭ የነበረው ወይጦ የተበላው ወንዝ በመድረቁም በወረዳዎቹ የውሃ እጥረት ተከስቷል።
አቶ ዱባ በአከባቢያቸው የተከሰተው ድርቅ እስካሁን በሰው ሕይወት ላይ ያደረሰው ጉዳት ስለመኖሩ ሪፖርት አለመደረጉብ ገልጸው፤ 303ሺህ ለሚሆን ሕዝብ ለአንድ ወር የሚሆን የመጀመሪያ ዙር እርዳታ በመንግሥት አማካይነት መደረጉን ገልጸዋል።
“ችግሩ አሁንም እየሰፋ እየሄደ ነው ያለው። ስለዚህ ለምግብ ክፍተት ሊጋለጡ የሚችሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው የሚሄደው። ዝናብ እየዘነበ አይደለም። ከብቶቻቸው እየሞቱ ነው። ሰው ወደ እርሻ ሥራው እየገባ አይደለም” ያሉት አቶ ዱባ የራ ለተቸገሩት ሰዎች እርዳታ ማድርግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በተመሳሳይ በሶማሌ ክልል የተከሰተው ድርቅ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከቀያቸው ሲያፈናቅል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንስሳት መሞታቸውን የክልሉ ሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በሶማሌ ክልል ባለፉት ሦስት ዓመታት በቂ ዝናብ ባለመጣሉ በተለይ ደግሞ በዳዋ፣ አፍዴራ እና ሊበን ዞኖች ድርቅ መከሱን አቶ አብዲቃድር ረሺድ ገልጸዋል።
በዳዋ ዞን በ92 መጠለያ ጣቢያዎች ከ52 ሺህ በላይ ተፈናቃይ የቤተሰብ አባላት ተጠልለው እንደሚገኙ ገልጸው፤ በሦስቱም ዞኖች በቂ ባይሆንም ለሰው እና ለእንስሳት ምግብ እና መኖ መከፋፈሉን ጨምረው ተናግረዋል።
በአፍዴራ እና ሊበን ዞኖች ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀል ባለመጀመራቸው ባሉበት ቦታ ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን አስረድተዋል።
“በዳዋ ዞን ብቻ ግመል፣ ከብት እና ፍየልን ጨምሮ ወደ 334 ሺህ እንስሳት ሞተዋል። 420 ሺህ በላይ እንስሳት ደግሞ ወደ ሞት እየተቃረቡ ነው” ያሉ ሲሆን ከዳዋ ውጪ ባሉት ዞኖች የእንስሳት ሞት አልጀመረም ብለዋል።
ከሶማሌ ክልል አቀማመጥ እና የአየር ፀባይ ጋር በተያያዘ የውሃ እጥረት በመኖሩ የውሃ እጥረት ሲከሰት ቀድመው የሚጎዱት እንስሳቶች ናቸው የሚሉት አቶ አብዲቃድር፤ በክልሉ ድርቅ በተከሰተባቸው ሦስቱ ዞኖች የእንስሳት መኖ አዳርሰናል ብለናል።
ላለፉት ተከታታይ ዓመታት የሚጠበቀው ዝናብ በወቅቱ ባለመዝነቡ የተነሳ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም ኬንያ እና ሶማሊያ ውስጥ ድርቅ ከባድ አደጋን ደቅኗል።
በዚህም የተነሳ በአገራቱ ውስጥ የሚገኙ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በአየር ንብረት መቃወስ የተነሳ በተከሰተው ድረቅ ሳቢያ የእርዳታ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የመንግሥታት ድርጅት አሳውቋል።