በጎንደር በሚገኝ ካምፕ ውስጥ ምግብ እርዳታ ለማግኘት የተሰለፉ ኢትዮጵያዊያን
የምስሉ መግለጫ,በጎንደር በሚገኝ ካምፕ ውስጥ ምግብ እርዳታ ለማግኘት የተሰለፉ ኢትዮጵያዊያን

ከ 9 ሰአት በፊት

የመንግሥታቱ ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ እጅግ ድሃ በሆኑ አገራት የሚገኙ ነፍሰ ጡሮች ዘንድ ከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መስተዋሉን ገለጸ።

ድርጅት እንዳለው በእነዚህ ድሃ አገራት ነፍሰ ጡር ሆነው በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ያሉ ሴቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ታይቷል።

ይህ ሪፖርት እንደሚያትተው ከድሃ አገሮች መካከል ለእናቶች ያለው ሁኔታ የከፋ የሆነው በአፍጋኒስታን፣ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ነው።

ዩኒሴፍ እንደሚገምተው በዓለም አንድ ቢሊዮን ሴቶች በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ይሰቃያሉ።

በተለይ የኮቪድ ወረርሽኝን ተከትሎ እንዲሁም ጦርነት ሴቶች የሚያስፈልጋቸውን መሠረታዊ አልሚ ምግብ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል።

ዩኒሴፍ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለዚህ ችግር ቅድሚያ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርቧል።

የዩኒሴፍ ሪፖርት እንደሚለው በዓለም አንድ ቢሊዮን ሴቶች፣ በተለይም ልጃገረዶች ክብደታቸው ከአማካይ በታች ነው፤ ከፊሎቹም ቀንጭረዋል።

በዚህ የተነሳ አስፈላጊ የሚባሉ ንጥረ ነገሮችን አያገኙም፤ ይህም ለሳንባ ምች ያጋልጣቸዋል።

በተለይ በደቡብ እስያ እና ከሰሐራ በታች ባሉ አገራት ይህ ችግር የከፋ ነው ብሏል ዩኒሴፍ።

የዩኬ አገር ውስጥ ሚኒስቴር ሕገወጥ ስደተኞችን እንዲያባርር ልዩ ሥልጣን ተሰጠው7 መጋቢት 2023

በእነዚህ አካባቢዎች 68 በመቶ ሴቶች እና ልጃገረዶች የክብደት ሚዛናቸው ዝቅተኛ ነው። ከእነዚህ መካከል ደግሞ 60 በመቶ የሚሆኑት ለሳንባ በሽታ የተጋለጡ ናቸው።

“ሴቶች የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘታቸው ለከፍተኛ መዳከም ይዳርጋቸዋል፤ የበሽታ መከላከል አቅማቸውን የሚያሳጣም ነው። የአእምሮ እድገታቸውም ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይፈጥራል፤ ይህ ደግሞ በእርግዝና እና በወሊድ ወቅት የከፋ ችግር ያስከትላል” ይላል ዩኒሴፍ።

ነፍሰጡሮች የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘት ደግሞ በተለይ በሚወለዱ ልጆች ዘንድ የማይቀለበስ አደጋን ያስከትላል። ይህም ከሞት ጀምሮ መላው እድገታቸው ላይ ችግር ያስከትላል።

ዩኒሴፍ እንደሚገምተው ከፈንጆቹ 2020 እስከ 2022 በነፍሰጡር እና በሚያጠቡ እናቶች ዘንድ ከ5.5 ሚሊዮን ወደ 6.9 ሚሊዯን ጨምሯል።

ይህም የሆነው ከፍተኛ የምግብ እጥረት በሚታይባቸው 12 ድሃ አገራት ዘንድ ነው።

እነዚህ 12 እጅግ ድሃ አገራት መሀል ደግሞ አፍጋኒስታን፣ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ይገኙበታል።

“የዓለም ማኅበረሰብ ካልተረባረበ ለትውልድ የሚሸጋገር መቅሰፍት ነው ይዞ የሚመጣው” ብለዋል የዩኔሴፍ አለቃ የሆኑት ካትሪን ራስል።