
8 መጋቢት 2023
አዶናይ ይሄይስ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነበረች። በጣም ጎበዝ ተማሪ።
በአንድ ግለሰብ ተደጋጋሚ አስገድዶ መድፈር ሲፈጸምባት ነበር።
መስከረም 14/2015 ዓ.ም. ደግሞ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደለች።
በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቿ ላይ በስለት ተወግታ ነው የተገደለችው።
ይህን ድርጊት የፈጸመው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ውሏል። ድርጊቱን መፈጸሙን አምኗል።
የአዶናይን ስቃይ ትንሽ ቀደም ብሎ ማስቆም ለምን አልተቻለም?

ሰብለ ንጉሤ በማስተርስ ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሸን በማዕረግ ተመራቂ ነበረች።
12 ዓመታት በሰው ሃብት አስተዳደር ዘርፍ አገልግላለች።
ብዙ መሥሪያ ቤቶች ሠርታለች። ኅብረት ባንክ ነበረች አሳዛኙ ፍጻሜዋ ሲቃረብ።
ታኅሣሥ 30/2014 ዓ.ም. ከባድ ድብደባ ተፈጸመባት። በስለት ተወጋች።
ይህ አልበቃ ብሎ ሳኒታይዘር በሰውነቷ ላይ ተርከፍክፎ በቃጠሎ እንድትሞት ሆነ።
ይህ አሰቃቂ ድርጊት የተፈጸመው ‘ፍቅረኛዬ’ በምትለው ግለሰብ ነው።
ሕይወቷን ባይተካም ወንጀለኛው በቅርቡ ሞት ተፈርዶበታል፤ ትንሽ ቀደም ብንል ኖሮ የሰብለን ሕይወት ማትረፍ አይቻልም ነበር ይሆን?

ጽጌረዳ ግርማይ ገና 20 ዓመቷ ነበር። አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ነበረች።
ጥር 23/ 2014 ዓ.ም. ምሽት ላይ የዩኒቨርስቲው ቤተ መጻሕፍት አካባቢ ሰው ይፈልግሻል ተብላ ተጠራች።
እንደደረሰች በስለት ተወጋች።
ተጠርጣሪው በአንድ የትምህርት ገበታ አብሯት የሚማር ነበር።
የፍቅር ጥያቄዬን ውደቅ አድርገሻል በሚል ምክንያት የተቆጣ ጎረምሳ ነው።
ይህ ወጣት ጽጌረዳን በለጋ ዕድሜዋ ቀጠፋት።
ጡቷ እና ግራ ጎኗ አካባቢ በጭካኔ በተደጋጋሚ በስለት ወጋት።
ሕይወቷ አለፈ።
ግለሰቡ ይህን ጥቃት ከመፈጸሙ በፊትም “አስቸጋሪ” ባህሪ የነበረው ተማሪ እንደነበረ ቢቢሲ በወቅቱ በሠራው ዘገባ እማኝ ጠቅሶ ጽፏል።
ሌሎች ሴቶችንም ‘ካልወደዳችሁኝ’ እያለ ያስፈራራ እንደነበርም ተዘግቦ ነበር።
ታዲያ ሞገደኛ የነበረ ግለሰብ ነፍስ ከማጥፋቱ በፊት እንዴት ማቆም ሳይቻል ቀረ?
የሴቶችን ጥቃት ለማስቆም ያልሞከርነው አዲስ መንገድ ይኖር ይሆን?
- የዓለም የሴቶች ቀንን ማን ጀመረው?8 መጋቢት 2020
- ከሦስት ሴቶች አንዷ ለጥቃት ተጋልጣለች – የዓለም ጤና ድርጅት10 መጋቢት 2021
- “በድብደባ እና በከፋ ድብደባ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?”4 መጋቢት 2023

“ገዳዮቹም ከማኅበረሰቡ የተቀዱ ናቸው”
ቤተልሔም ደጉ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር የፕሮግራም ዳይሬክተር ናቸው።
“ከጊዜ ወደ ጊዜ በጾታዊ ጥቃት ሕይወታቸውን የሚያጡ፣ አካላቸው የሚጎድል ሴቶች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ነው” ይላሉ።
እነ ቤተልሔም የጥቃት ቁጥሩ እንደጨመረ የሚረዱት የሕግ ድጋፍ ፈልገው እነርሱ ጋር በሚመጡ ተጠቂዎች ብዛት ነው።
የእነርሱ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ያሉት ደግሞ በሁሉም ቦታ አይደለም።
አገር አቀፍ የሆነ ጥናት ቢደረግ ቁጥሩ ከፍተኛ እንደሚሆን ከዚህ መገመት አይከብድም።
ማኅበሩ በፈረንጆች 2022 ዓ.ም. ብቻ በቢሮዎቹ ከተደረጉለት የእርዱኝ ጥያቄዎች 47ቱ የግድያ እና ግድያ ሙከራዎች ነበሩ፣ 32 አስገድዶ መድፈሮች እንዲሁም 158 በሴቶች ላይ የደረሱ አሰቃቂ ድብደባዎች ናቸው።
አሁን ልብ ማለት የሚኖርብን ወደ ማኅበሩ የሚመጡት ጥሪዎች በአገር ደረጃ ኢምንት መሆናቸውን ነው።
ይህ ሴቶች ላይ የሚደርሰው የጥቃት መደጋገም ነገሩ ‘የተለመደ’ እንዲሆን እያደረገው ይመስላል።
ጾታዊ ጥቃት ‘ያው ያለ ነው’ እየተባለ መታለፍ ከተጀመረ የማኅበረሰብ ዝቅጠት መባቻ ነው። ካላስደነገጡን-ካላስቆጡን ጥሩ አይደለም።
በፊት የምናያቸው ኡኡታዎች፤ በአገር ደረጃ የሚሰሙ ጩኸቶች፣ እንዳይደገም የሚያስብሉ ብሔራዊ ሐዘኖች፣ ከጋራ እሴት የሚነሱ ብግነቶች የት ገቡ? እየከሰሙ ነው? ወይስ ብሔራዊ ሐዘን እና ሰቆቃን እየለመድን መጣን?
“ጭራሽ በእህቶቻችን ሞት መቆጨቱ ቀርቶ እኮ አሁን አሁን በማኅበራዊ ሚዲያ አጥቂውን፣ ‘ደግ አረገ’ የሚሉ ድምጾች መስተጋባት ጀምረዋል” ይላሉ ቤተልሔም ደጉ።
ከአሰቃቂ የሴቶች ጥቃት ማግስት “እና ምን ይጠበስ?” ዓይነት ስሜቶች ከተስተጋቡ ለአንድ ማኅበረሰብ የሞራል ዝቅጠት ምልክቶች ናቸው፤ አደገኛ አዝማሚያዎች ናቸው፤ የቁልቁለት መንገዱን እንደጀመርን ማሳያዎች ናቸው።
በቅርብ ያየናቸው ለምሳሌ፣ “የእሱን ማን አየለት”፣ “ይሄኔ አቃጥላው ነው የሚሆነው” የሚሉ አስተያየቶች ማንበብ ደግሞ ለተጠቂ ሁለት ጊዜ ሞት ይላሉ በርካቶች።
“አዎ እንዲህ ዓይነት ከአጥቂ ጎን የሚቆሙ አስተያየቶች በዝተዋል” የሚሉት ቤተልሔም፣ “… ልንረዳ የሚገባው ግን ሴቷ ምንም ዓይነት በሞራል ተቀባይነት የለውም የምንለውን ነገር ብትፈጽም እንኳ ወንዱ እሷን የመግደል መብትን አያጎናጽፈውም” ይላሉ።
የመግደል መብት የሚሰጥ ጥፋት የለም። ምናልባት ፍርደ ገምድል የሚያደርገን ዞሮ ዞሮ የተባእታዊ ሥርዓት ውጤቶች መሆናችን ይሆን?
ይህ ተባእታዊ ‘እሴት’ የትኛውንም ከባል የሚመጣ የግፍ ጽዋ ሴቷ እንድትጨልጠው ያበረታታል።
ቤተልሔም “ገዳዮቹም ከእኛው ናቸው” የሚሉት ለዚህ ይሆናል።
ጥቃቶችን ማስቆም አይቻልም?
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሰማናቸው ጥቃቶች ምን ያመሳስላቸዋል ካልን የቅርብ በሚባል ሰው መፈጸማቸው ነው። ባል፣ የእንጀራ አባት፣ ፍቅረኛ፣ እጮኛ፣ ወዘተ።
ቤተልሔም አንዱ ፈተናም ይኸው ነው ይላሉ።
“ጥቃቶቹ በብዛት ተጠቂዎቹ ‘የእኔ!’ በሚሉት ሰው ነው የሚፈጸሙት።”
ነገሩን አስቸጋሪ የሚያደርገውም ይኸው ነው። ሰው አደጋ ሲገጥመው ሮጦ ከለላ የሚፈልገው ከቤተሰቡ ነው። ባሎች፣ የፍቅር አጋሮች፣ እጮኛ፣ አባት የቤተሰብ አካል ናቸው። አደጋ ጣይ እነሱው ሲሆኑ ወዴት ይኬዳል?ሴቶች ላይ የሚፈጸም አሰቃቂ ጥቃትን ቀድሞ ለማነፍነፍም ፈታኝ የሆነውም ለዚሁ ነው።
ከለላ ሰጪዎች ራሳቸው አጥቂዎቹ ስለሚሆኑ።
“ባእድ ከሆነ ጠላት ይሸሻል፤ ቤት ውስጥ ካለ ወገኔ ከምንለው ሰው ግን ወዴት ይሸሻል?”
በእርግጥ በራስ ሰው መጠቃት አጥቂውን ቶሎ ለፖሊስ አካል ሪፖርት ለማድረግ ማመንታት ውስጥ ሊከት ይችላል።
ነገር ግን አንዳንዶቹ ጥቃቶች ለፖሊስ ሪፖርት ተደርገውም ነው ኋላ ላይ ትልቁን መዘዝ ይዘው የሚመጡት። ቶሎ እርምጃ ስለማይወሰድ። ከሕግ አስፈጻሚው በኩል ክፍተት ሳይኖር አይቀርም።
ፖሊስ መረጃ የሚሰበስብበት መንገድ፤ ለማኅበረሰብ ጠንቅ የሆነን ሰው የሚከታተልበት መልክ ገና አልዘመነም።
በዚህ መጠነ ዙሪያ (ራዲየስ) እጅ ያነሳህባት ሴት ጋር እንዳትቀርብ የሚያስብሉ ሕጎችን አልተለማመድንም።
“ባሌ ሊገድለኝ ነው” ብላ ለፖሊስ የምታመለከት ሴት ቃሏን የሚቀበላት ወንድ ፖሊስ ምን ሊላት እንደሚችል መገመት አያዳግትም።
ምናልባት ከዚህ አንጻር የሕግ አስፈጻሚ አካላት ቸልተኝነት፣ ንቃት፣ ግንዛቤ ማነስ ይኖር ይሆን?
ቤተልሔም “የችግሩ ስር መሠረት አንድ አስፈጻሚ አካል ላይ የሚደፈደፍ አይደለም” ይላሉ። የችግሩ ክፍተት ፖሊስ ብቻ ነው ካልን ስህተት ላይ እንወድቃለን ባይ ናቸው።
ችግሩ ውስብስብ ነው። አንዱ ላይ ብቻ አድብተን ከሠራንም ችግሩ አንቀርፍም ነው የሚሉት።
ከሕጉ በኩል፣ ሕጉን ከማስፈጸም በኩል፣ አስተማሪ ቅጣት ካለመወሰን ወዘተ ጥቃቶች ተበራክተው ይሆናል።
“ስር መሠረቱ ግን በዋናነት ሴትን ዝቅ አድርጎ የሚመለከት ማኅበረሰብ ነው” ሲሉ የነገሩን ውል ያስሩታል።
ጥቃት አድራሹም ያደገበት ማኅበረሰብ ውጤት ስለሆነ።
“የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ጥቃት ለመበራከቱ የሕጉ ክፍተት ብቻ ነው መንስኤ ብሎ አያምንም፤ ሁሉም ላይ መሠራት እንዳለበት ነው የምናምነው” ይላሉ የፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት ቤተልሔም ደጉ።
ሁሉም የራሱን ኃላፊነት ሲወጣ፣ እንደ ማኅበረሰብ ራሳችንን ስንፈትሽ፣ ለሴቶች ያለን አመለካከት ሲቀየር፣ በባህላችን ውስጥ ልክ ነው ያልነው ልክ እንዳልሆነ ሲገባን ጥቃቶች ቀስ በቀስ ሊቀንሱ ይችሉ ይሆናል።
እስከዚያው ግን መከራችን ይቀጥል ይሆናል።