የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ

8 መጋቢት 2023, 11:15 EAT

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ተግባራዊ እንዲሆን ኮሚሽናቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጹ።

ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ ይህን ያሉት በ52ኛው የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ጉባኤ ላይ የተቋማቸውን እንቅስቃሴ በተመለከተ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ነው።

ኮሚሽነሩ የሽግግር ፍትሕን ጨምሮ በኢትዮጵያ ግጭት ለማቆም በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ሙሉ ተፈጻሚነትን በበጎ እንቀበላለን ብለዋል።

በከፍተኛ ኮሚሽኑ የሚደገፍ በሽግግር ወቅት ፍትሕ የፖሊሲ አማራጭ ዙሪያ የሚካሄደው ብሔራዊ ምክክር መጀመሩን አመልክተው፣ ይህም በመላው አገሪቱ በግጭት በተጎዱ ሰዎች የሚደረግ ውይይት እንደሚኖር ተናግረዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ወቅት ሁሉም ተሳታፊ ወገኖች ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እንደፈጸሙ በመንግሥታቱ ድርጅት እና በመብት ተሟጋቾች ሲገለጽ ቆይቷል።

ጦርነቱን ለማስቆም በተደረሰው ስምምነት መሠረት በሽግግር ፍትሕ ሂደት ጥፈተኞችን ለመለየት እና ተጎጂዎችን ለመካስ የታሰበ ሲሆን፣ የመንግሥታቱ ድርጅትም የባለሙያዎች ቡድን አቋቁሞ ምርመራ እያደረገ ነው።

የኤርትራ እና የአማራ ኃይሎች በትግራይ

ከፍተኛ ኮሚሽነሩ በንግግራቸው የኤርትራ እና የአማራ ኃይሎች አሁንም በትግራይ ስለመኖራቸው ጨምረው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ አዎንታዊ ለውጦች ቢኖሩም በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠያቂ የሚደረጉት የኤርትራ እና የአማራ ኃይሎች በትግራይ ክልል ስለመኖራቸው ለሚመሩት ኮሚሽን ሪፖርት መደረጉን ቱርክ ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የኤርትራ ሠራዊት አባላት፣ የአማራ ክልል ኃይሎች እና የፋኖ ሚሊሻ አባላት በትግራይ እንደመገኙ ሪፖርቶች ደርሰውናል ብለዋል።

የክትትል እና የሪፖርት ሥራዎች መቀጠላቸው መሠረታዊ ነው ያሉት ከፍተኛ ኮሚሽነሩ፣ በግጭት ወቅት ለተከሰቱ የመብት ጥሰቶች ተጨባጭ የሆነ ተጠያቂነት እንዲኖር ተግባራዊ እርምጃ መኖር አለበት ብለዋል።

ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ በተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ያለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ አያያዝ በተለይ ደግሞ በኦሮሚያ እጅጉን አሳሳቢ ነው ብለዋል።

የሁለት ዓመቱን የእርስ በርስ ጦርነት ያስቆመው ስምምነት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መሪዎች መካከል በተፈረመው ውል፣ ከአገሪቱ ሠራዊት ውጪ የሆኑ ኃይሎች ከክልሉ እንዲወጡ እና የህወሓት ኃይሎችም ትጥቅ እንዲፈቱ ከስምምነት መደረሱ ይታወሳል።

አስገዳጁ የኤርትራ ብሔራዊ አገልግሎት

ኮሚሽነር ቱርክ የኤርትራ ሠራዊት አባላት አሁንም በትግራይ ከመኖራቸው በተጨማሪ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አስተዳደር ዜጎችን ለአስገዳጅ ብሔራዊ አገልግሎት መመልመሉን አጠናክሮ ስለመቀጠሉ ሪፖርት ደርሶናል ብለዋል።

“ከባርነት ጋር የሚስተካከለው” አስገዳጅ ብሔራዊ አገልግሎት ዜጎችን አገር ጥለው እንዲሰደዱ ዋነኛ ምክንያት ነው ብለዋል።

ኤርትራ ዘላቂ የሆነ የእድገት ጎዳና ላይ እንድትገባ ይህ አስገዳጅ ብሔራ አገልግሎት በአስቸኳይ ሊቀለበስ ይገባል ብለዋል።

ለዓመታት በኤርትራ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው አስገዳጁ የኤርትራ ብሔራዊ አገልግሎት የጊዜ ገደብ የሌለው ሲሆን መንግሥት ለአገልግሎቱ የሚከፍለው ክፍያም እጅግ አናሳ እንደሆነ ይገለጻል።

ወጣት ኤርትራውያን ከአገር ተሰደው ከሚወጡባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ ይህ አስገዳጅ ብሔራዊ አገልግሎት እንደሆነም ተገፈልጿል።

ኤርትራ ነጻ አገር ከሆነች ጊዜ አንስቶ ሲካሄድ የቆየው አስገዳጅ የብሔራዊ አገልግሎት መብት የሚጥስ መሆኑን እና ዜጎችን ያማረረ መሆኑ ሲነገር ቆይቷል።

ኤርትራ በሰብአዊ መብት አያያዟ በመንግሥታቱ ድርጅት ብቻ ሳይሆን በምዕራባውያን አገራት እና በሁሉም የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ስትወቀስ ቆይታለች።