የአዲስ አበባው የአድዋ ድል በዓል አከባበር

8 መጋቢት 2023, 18:41 EAT

የአንድ ሰው ሕይወት በጠፋበት የአዲስ አበባው የዓድዋ ድል በዓል አከባበር ላይ ያልተገባ ተግባር ፈጽመዋል ባላቸው የፖሊስ አባላት ላይ እርምጃ መውሰዱ ተገለጸ።

በእነዚህ የፖሊስ አባላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን እና ተጨማሪ የምርመራ ተግባር እየተከናወነ ስለመሆኑ የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይልን ዋቢ አድርገው የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

127ኛው የዓድዋ ድልን ለማክበር በምኒልክ አደባባይ በተሰበሰቡ ነዋሪዎች ላይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተገቢ ያልሆነ ኃይል መጠቀማቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የካቲት 24/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።

በዚህም የፀጥታ ኃይሎች በበዓሉ ታዳሚዎች ላይ ድብደባ መፈጸማቸውን፣ አስለቃሽ ጭስ መተኮሳቸውን፣ የፕላስቲክ እንዲሁም እውነተኛ ጥይቶችን መተኮሳቸውን ኮሚሽኑ ገልጾ ነበር።

ፖሊስ በዓሉን ለማክበር መሃል አዲስ አበባ በሚገኘው የአጼ ምኒልክ አደባባይ ተገኝተው በነበሩ ሰዎች ላይ በወሰደው እርምጃ በርካታ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው የተዘገበ ሲሆን፣ አንድ መምህርም ከፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ተገድሏል።

ሕጋዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋል የተባሉት የፖሊስ አባላት ምን ያህል እንደሆኑ እንዲሁም እርምጃው ምን እንደሆነ ዘገባው ያለው ነገር የለም።

ኢሰመኮ የፀጥታ ኃይሎች ወስደውታል ባለው ከልክ ያለፈ እርምጃ በእድሜ ገፋ ያሉ እና ሕፃናትም ጭምር ለእንግልት መዳረጋቸውን ገልጿል።

በዚህም በዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሲቪክስ መምህር የሆነው ሚሊዮን ወዳጅ በጥይት የተገደለ ሲሆን፣ በርካቶችም የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እና የፀጥታ እና ደኅንነት ግብረ ኃይል አባል ጌቱ አርጋውም በጥይት የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን አረጋግጠዋል።

በዕለቱ በፖሊስ አባላት ላይ ጉዳት መድረሱን እና በዚህም 16 አባላቱ ቀላል እና ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል። በተጨማሪም ሦስት አውቶብሶችና አንድ አምቡላንስ ተሰባብረዋል ብለዋል።

የፀጥታ ግብረ ኃይሉ የዓድዋ ድል አከባበር ላይ ተፈጠረ ካለው ሁከት ጋር ተያይዞ 878 ተጠርጣሪዎች በቁጥር ስር መዋላቸው የተገለጸ ሲሆን፣ “ከእነዚህም ውስጥ 557ቱ ከሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ናቸው” ብሏል።

ፖሊስ እነዚህን ግለሰቦች “የመዲናዋን ሰላም ለማናጋት ሁከት እና ብጥብጥ ለመፍጠር አቅደው ሲንቀሳቀሱ ነበር” በሚል እንደጠረጠራቸው አስታውቋል።

“ሰላም የማይፈልጉ” ብሎ ፖሊስ የጠራቸው ኃይሎች የዓድዋ ድል በዓልን አከባበር “አውድ ለመቀየር እና የከተማዋን ሰላም እና ፀጥታ ለማደፍረስ የብሔር እና የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር ሞክረዋል” ሲልም ከሷል።

“አነዚህ ኃይሎች በተቀናጀ መንገድ የከተማዋን ሰላም ለማናጋት አቅደው የሚሰሩ አካላት ስለመኖራቸው ደርሰንበታል” ብሏል።

በዕለቱ ችግር ፈጥረዋል የተባሉት ቡድኖች በጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ምዕመናን መስለው በመግባት በፀጥታ ኃይሎች ላይ ድንጋይ ወርውረዋል ጉዳትም አድርሰዋልም ተብሏል።

“በአራዳ አካባቢ ንብረት የማውደም እና የመዝረፍ ሙከራዎች የነበሩ ቢሆንም ፀጥታ ኃይሉ መቆጣጠር እንደቻለ” ነው የተገለጸው።

ኢትዮጵያ ቅኝ ገዥውን የጣሊያን ጦር ድል የነሳችበት ዓመታዊውን የዓድዋ ድል በዓል ለመታደም በምኒልክ አደባባይ በተሰበሰቡ ነዋሪዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች በአስለቃሽ ጭስ እና በቆመጥ መበተናቸውን በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህም ሳቢያ በአደባባዩ አካባቢ እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከነበሩ ሰዎች መካከል በርካቶች በአስለቃሽ ጭስ እና በድብደባ ተጎድተው ወደ ሐኪም ቤት መወሰዳቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በምኒልክ አደባባይ ዋናው ዝግጅት ላይ ሕዝቡ እንዳይታደም ወደ አደባባዩ የሚወስዱት መንገዶች ተዘግተው እንደነበር እና እንዳይተላለፍም በፀጥታ ኃይሎች ታግዶ እንደነበር ኢሰመኮ ገልጿል።

ኢሰመኮም በዚሁ መግለጫው በምኒልክ አደባባይ የዓድዋ ድል በዓል እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊስን ዓመታዊ በዓል እያከበሩ በነበሩ ሰዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች በኃይል አላስፈላጊ እና ከመጠን ያለፈ እርምጃ ወስደዋልም ብሏል።