
8 መጋቢት 2023, 17:13 EAT
የሲያድ ባሬ አስተዳደር ተገርስሶ ሶማሊያ በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ ለሦስት አስር ዓመታት ያህል የተረጋጋ ሰላም የታየባት ሶማሊላንድ በአሁኑ ወቅት በግጭት እየተናጠች ትገኛለች።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የአገርነት እውቅና ያልተሰጣት የራስ ገዝ አስተዳደሯ ሶማሊላንድ በቅርቡ በተቀሰቀሰው ግጭት 200 ዜጎቿ ሞተዋል፣ እንዲሁም ቢያንስ 100 ሺህ ዜጎቿ ተፈናቅለው ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።
ተፈናቃዮቹ በኢትዮጵያ ዶሎ ግዛት መስፈራቸውን የተባበሩት መንግሥታት ያስታወቀ ሲሆን፣ አካባቢውም በአራት አስርት ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ድርቅ መመታቱም ሁኔታውን ፈታኝ አድርጎታል።
ተፈናቃዮች በህንጻዎች ውስጥ ተጠልለው እንዲሁም ከቤት ውጪ ጎዳናዎች ላይ መሆናቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት አመልክቷል።
እነዚህን ተፈናቃዮች ለመድረስ የእርዳታ ሠራተኞች ለሁለት ቀናት ያህል በመኪና መጓዝ ይጠበቅባቸዋል።
- ‘ዜግነታቸውን’ የሚቀይሩት የኢትዮጵያ ከብቶች10 ጥር 2023
- ሶማሊያ የዓለማችን ሙስና የተጠናወታት አገር ተባለች23 ጥር 2020
- በሶማሊያ ወጣት ሴቶችን በሱስ እያማቀቀ ያለው መድኃኒት28 ታህሳስ 2022
የግጭቱ መነሻ
ከቀሪው የሶማሊያ ክፍል በተለየ በተረጋጋ ሁኔታ በሰላም ውስጥ የቆየችውን የሶማሊላንድን ሰላም ያደፈረሰው ግጭት የተቀሰቀሰው በአወዛጋቢዋ ግዛት ላስ አኖድ ውስጥ ነው።
ግዛቲቱ ዋነኛ የንግድ መስመር ስትሆን ሶማሊላንድ እና ቀሪው አጎራባች በሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ስር ያለችው ከፊል ራስ ገዝ አስተዳደሯ ፑንትላንድ በይገባኛል ሲወዛገቡባት ቆይተዋል።
በቅርቡም ላስ አኖድ በምትገኝበት የሱል ክልል የጎሳ መሪዎች የሶማሊያን የፌደራል መንግሥት እንደሚደግፉ እና የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት ወታደሮቻቸውን ከአካካቢው እንዲያስወጡ መግለጫ አውጥተዋል።
ከሱል ክልል በተጨማሪ በሌሎች ሁለት ግዛቶች የሚገኙ የአገር ሽማግሌዎች ወደ ሶማሊያ መቀላቀል እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን ተከትሎ ነው ጥር 29/2015 ዓ.ም. አዲሱ ግጭት የተቀሰቀሰው።
በሶማሊላንድ እና ለሶማሊያ ታማኝ በሆኑ የአካባቢው የጎሳ ኃይሎች መካከል ነግሶ የነበረው ውጥረትም ወደ ግጭት ተቀይሮ ቢያንስ የሁለት መቶ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።
ሶማሊላንድ የሱልን ክልል በአውሮፓውያኑ 2008 ከፑንትላንድ ከወሰደችበት ጊዜ ጀምሮ እያስተዳደረች ትገኛለች።
ይህንንም ተከትሎ በሶማሊላንድ እና በፑንትላንድ መካከል ውጊያዎች እንዲካሄድ ምክንያት ሆኗል።
ከወራት በፊት ደግሞ በላስኖድ ከተማ ለተፈጸሙ ተከታታይ ግድያዎች የሶማሌላንድ ባለስልጣናት ምንም አይነት የተጠያቂነት እርምጃ ባለመስፈናቸውም ህዝቡን እንዲሁም የጎሳ መሪዎችን አስቆጥቷል።
በቅርቡ እንደ አዲስ ለተነሳው ግጭት መነሻው በላስ አኖድ ተሰብሰብው የነበሩ የጎሳ መሪዎች ሶማሊላንድ ግዛቷን ማስተዳደሯን እንደማይቀበሉት እና ይህ ክልልም ሞቃዲሾ ተቀማጭ በሆነው የፌደራል መንግሥት ስር መተዳደርም እንደሚገባው መግለጻቸው ነው።
የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድን ጨምሮ በርካታ አገራት በሁለቱ ኃይሎች መካከል ተኩስ አቁም እንዲኖር ጠይቀዋል።
የተበባሩት መንግሥታትም በላስ አኖድ የተፈጠረው ግጭት ረግቦ እልባት እንዲያገኝ እና ዜጎችም ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ጠይቋል።
ሶማሊላንድ በግዛት አንድነት ላይ አልደራደርም በማለት የጸናች ሲሆን ላስ አኖድ፣ ሱል እና ሳናና ክልሎች የአገሪቱ ግዛት አካል ናቸው ብላለች።
የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት ግጭቱ ከተነሳ ከቀናት በኋላ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረጋቸውን ቢገልጹም፣ ከቀናት በኋላ ሶማሊያ በጦር ኃይሏ ላይ ጥቃት ሰንዝራለች ሲሉ ከሰዋል።
ሶማሊያ ለቀረበባት ክስ ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጠችም።
በሶማሊያ የፌደራል መንግሥት ስር መተዳደር የሚፈልጉት የሱል ክልል አመራሮች በዘላቂነት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ እያቀረቡ ነው።
የሶማሊላንድ ጦር በከተማዋ መግባት እና መውጣቱ አሁንም እንደቀጠለ ገልጸው፣ ዘላቂ ለሆነ የተኩስ አቁም ዝግጁ አይደለም ሲሉ ይወቅሳሉ።
በላስ አኖድ የተነሳው ግጭትም በክልሎች ለረጅም ጊዜ ሲነሳ የነበረው የራስ አገዛዝ አስተዳደርነት ላይ ጥያቄ አስነስቷል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት የሱል እና የሌላኛዋ የሳናግ ክልል ፖለቲከኞች ኻቱሞ ተብሎ የሚጠራ የፌደራል ሥርዓት እንዲመሠረት ቢጠይቁም ከሶማሊላንድ በኩል እውቅና አላገኘም።
ውጥረቱ እንደገና በተቀጣጠለበት በአሁኑ ወቅት የሶማሊላንድ መንግሥት መገንጠል እንፈልጋለን ከሚለው ክልል ጋር ተጨማሪ ደም መፋሰስን ለመከካላከል ድርድር ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል።
በተጨማሪም ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የሶማሊላንድ እና የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት መካከል የሚደረገው ውይይት መጀመር ነገሮችን ሊያረግብ ይገባል ተብሏል።
- የኢትዮጵያ ጦር ያለበት የአፍሪካ ኅብረት ኃይል ሲወጣ ሶማሊያ አልሻባብን መቆጣጠር ትችላለች?16 የካቲት 2023
- ሶማሊያ ታጣቂው ቡድን “አል ሻባብ” በሚለው ስያሜ እንዳይጠራ አገደች7 ህዳር 2022
- ሶማሊያውያን በጉንዳን ‘ሱስ መጠመዳቸው’ እንዳሳሰበው የአገሪቱ ፖሊስ ገለጸ10 ሀምሌ 2022
ጥቂት ስለ ሶማሊላንድ
ሶማሊ ላንድ 4.5 ሚሊዮን ህዝብ ይኖርባታል።
የሶማሊያው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሲያድ ባሬ አገዛዝ በአውሮፓውያኑ 1991 መገርሰሱን ተከትሎ ነጻ አገር ሆና መመስረቷን አስታወቀች።
ሶማሊላንድ በአገርነት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ እውቅና እንዲሰጣት በተደጋጋሚ ብትጠይቅም እስካሁን ድረስ አልተሰጣትም።
ቀውስ በማይለየው ቀጠና ውስጥ የመረጋጋት ተስፋ ተደርጋ የምትታየው ሶማሊላንድ ዕውቅና ባይቸራትም የራሷን መገበያያ ገንዘብ፣ ፓስፖርት እና መንግሥታዊ አስተዳደር አላት።
በዓለም አቀፉ ደረጃ አገር በሚል ዕውቅና የሰጠቻች በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ የምትገኘው ታይዋን ብቻ ስትሆን፣ የአፍሪካ ኅብረት ዕውቅና ችሯት የአህጉራዊው ድርጅት አባል ለመሆንም ለዓመታት ስትጥር ቆይታለች።
ሶማሊያ ከቅኝ ግዛት ወደ ነጻነት፣ በኋላም ወደ እርስ በርስ ጦርነት ያመራችበት መንገድ ረዥም ነው። በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሁለቱ የአውሮፓ ሃያላን አገራት ብሪታንያ እና ጣልያን በቅኝ ግዛት ገዘተዋታል።
የብሪታንያ ሶማሊላንድ እና የጣልያን ሶማሊላንድ በሚልም ለዓመታት ከገዟትም በኋላ በአውሮፓውያኑ 1960 ነጻነታቸውን አግኝተው ኅብረት መስርተው በጋራ ሶማሊያ ተባሉ።
የሶማሊላንድ ዕውቅና አለማግኘት ፖለቲካዊ እንደሆነ ባለሥልጣናቷ ሲናገሩ ይሰማል።
አንዲትን አገር እውቅና የሚያሰጧት ህዝብ፣ ግዛት፣ መንግሥትና ሉዓላዊነት መስፈርቶች አሟልቻለሁ በማለትም ትከራከራለች።
ሶማሊላንድ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች በኋላ ለ30 ዓመታት ያህል ከሶማሊያ ጋር በአንድ ግዛት ስር የነበረች ሲሆን፣ የሲያድ ባሬን መውደቅ ተከትሎ ነው ነጻ አገርነቷን ያወጀችው።
ለሶማሊላንድ ይህ መገንጠል ሳይሆን ተፈጥሮ ከነበረው ኅብረት መውጣት ነው ይላሉ ፖለቲከኞቿ። በዚህም በአውሮፓውያኑ 2001 በተካሄደው ሕገ መንግሥታዊ ሕዝበ ውሳኔ 97 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የሶማሊላንድ እንደ ሃገር መመስረት ደግፏል ይላሉ።
ሶማሊያ በበኩሏ የሶማሊላንድ ጉዳይን የምታየው እንደ መገንጠል ጥያቄ ነው፤ ሶማሊላንድንም በአገር ደረጃ እውቅና አልሰጠቻትም።