March 8, 2023

ኬንያ ውስጥ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው የሚገኙ 21 ኢትዮጵያዊያን ከሐሙስ የካቲት 23/2015 ጀምሮ በረሀብ አድማ ላይ እንደሆኑ ተነግሯል፡፡

ታሳሪዎቹ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በፍርድ ቤት የተወሰነላቸው ቢሆንም የውሳኔው ተግባራዊነት ዘግይቷል በማለት የረሀብ አድማውን መጀመራቸው የተሰማ ሲሆን፣ በዚህ የተነሳም የኬንያ ፖሊስ ድንጋጤ ላይ መውደቁ ተሰምቷል፡፡

የካቲት 10/2015 ጁጃ ኪያምቡ በሚባል አካባቢ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት ታሳሪዎቹ በፍርድ ቤት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ቢወሰንም፣ የፖሊስ መኮንኖች ታሳሪዎቹ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚያደርገውን የወረቀት ሥራ እስካሁን አልጨረሱም፡፡

እነሱን ወደ አገራቸው ለመመለስ ከሚገባው በላይ ጊዜ ፈጅቷል ያሉት ታሳሪዎችም ተቃውሟቸውን ለማሰማት የካቲት 23 የቀረበላቸውን ምግብ አንመገብም ማለታቸው የተነገረ ሲሆን፣ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም በአድማቸው እንደጸኑ ተሰምቷል፡፡

ታሳሪዎቹ ላይ ከፍተኛ ድካም እንደሚታይባቸው ሲነገር፣ ይህም ፖሊስን ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደከተተው የጁጃ ፖሊስ ጣቢያ መኮንኖች ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩም በቅርበት እየተከታተሉት እንደሆነ የተናገሩት በኬንያ ፖሊስ የድንበር ተሻጋሪ የተደራጁ ወንጀሎች መምሪያ ኃላፊ ጆርጅ ሙቶኒያ፣ ታሳሪዎቹ በቶሎ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ እንሰራለን ማለታቸውን ዘ ስታር ዘግቧል፡፡

በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጉዳዩ ላይ እጁን ስለማገባቱ እስካሁን የተባለ ነገር የለም፡፡

ከሳምንታት በፊት መነሻቸውን ኢትዮጵያ አድርገው ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሻገር ጉዞ ላይ የነበሩ 41 ኢትዮጵያዊንና 2 አዘዋዋሪዎች ናይሮቢ ውስጥ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

(አዲስ ማለዳ)