
ኢትዮጵያ ሴቶችን እኩልነትን ከቃል ባለፈ በተግባር የምትቀበል እና የምታሳይ አገር እንድትሆን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ጥሪ አቀረበ።
ኢሰመጉ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ ዛሬ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ፣ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በአውሮፓ እና በአሜሪካ በሚገኙ አገራት በነበሩ የሴቶች እንቅስቃሴዎች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1911 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ሁኔታ ሲከበር የቆየ በዓል መሆኑን አስታውሷል።
ቀኑ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1975 ጀምሮ በተባበሩት መንግስታት ድርጅ አማካኝነት በደማቁ ሲከበር መቆየቱን ያስታወሰው ኢሰመጉ፣ ዘንድሮም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ112ኛ ጊዜ ለ47ኛ ጊዜ እንደሚከበር ገልጿል፡፡
ኢሰመጉ በመግለጫው በኢትዮጵያ በያዝነው 2015 እንዲሁም ባሳለፍነው 2014 ዘርፈ ብዙ የሆኑ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በሴቶች ላይ መፈጸማቸውን የገለጸ ሲሆን፣ ሴቶች በመኖሪያ ቤታቸው፣ በሚማሩበት ትምህርት ቤት፣ በመስሪያ ቤታቸው፣ በመኖሪያ አካባቢያቸው እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የተለያዩ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲሁም ለወሲባዊ ጥቃቶች ተጋልጠዋል ብሏል፡፡
“ይህ ጥቃት የሴቶችን ዘር፣ ሀይማኖት፣ ቋንቋ፣ አመለካከት እንዲሁም ሌሎች ማኅበራዊ መደቦችን ሳይለይ በየትኛውም እድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ሴቶች ላይ ተፈጽሟል፡፡” ያለው ኢሰመጉ፣ ሴቶች ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍልች በመሆናቸው ተገቢ ጥበቃ እና ከለላ ሳይደረግላቸው በመቅረቱ ለበርካታ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መጋለጣቸውን ገልጿል።
በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በሚነሱ ግጭቶች ምክንያት በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴቶች መፈናቀላቸውንም በመግለጽ፤ በረሃብ እንዲሁም በተደጋጋሚ በሚከሰት ድርቅ ምክንያት በርካታ ሴቶችና ህጻናት ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን ጠቁሟል፡፡
በዚህም ሴቶች በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በእኩልነት እንዲሳተፉ ባለመደረጉ፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴቶች በኢኮኖሚያዊ ጥገኝነታቸው ምክንያት ለተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተጋለጭ እንዲሆኑ እና ለመብታቸው እንዳይታገሉ ከፍተኛ ተጽዕኖን ፈጥሯልም ብሏል።
በአገራችን ኢትዮጵያ የሴቶች የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊ እና ሌሎችም መስኮች ላይ ያላቸው ተሳትፎ መሻሻልን ያሳየ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ ሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች ላይ ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ በመሆኑ በቂ እና ተገቢ የሆነ የሴቶች ተሳትፎ እንዳይኖር እንዱሁም ለሴቶች ጉዳይ ትኩረት እንዳይሰጠው ከፍተኛ መሰናክል ሆኗል ሲል ኢሰመጉ ገልጿል፡፡
በዚህም መሰረት፣ ኢትዮጵያ ሴቶችን እኩልነትን ከቃል ባለፈ በተግባር የምትቀበል እና የምታሳይ አገር እንድትሆን፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በሴቶች እኩልነት የሚያምን ህዝብ እንዲሆን፣ የሴቶች እኩልነትን የሚመለከቱ መብቶች የሚከበሩባት እና የሚተገበሩባት አገር እንድትሆን፣ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እና ወሲባዊ ጥቃቶች የሚቆሙባት አገር በመሆን ሴቶች በነጻነት ደህንነት ተሰምቷቸው እኩልነታቸው ተረጋግጦ በተለያዩ የማኅበራዊ ክንዋኔዎች ውስጥ በንቃት የሚሳተፉባት አገር እንድትሆን ጉባዔው በመግለጫው ጠይቋል።
ጾታዊ ጥቃትን፣ ጾታዊ እኩልነትን እና በአጠቃላይ ሴቶችን መሰረት ያደረጉ ህግጋቶች የተሸሻሉባት ኢትዮጵያን ማየት የምንጊዜም ምኞቱ መሆኑን የገለጸው ኢሰመጉ፤ መንግስት ሴቶችን በእኩል ደረጃ አካትቶ የሚይዙ የሕግ ማዕቀፎችን፣ የፖሉሲ እቅዶችን እንዲሁም መዋቅራዊ አሰራሮችን በመተግበር የሴቶችን እኩሌነት በተግባር እንዱያረጋግጥ እንዱሁም በውሳኔ ሰጪነት ላይ ሴቶች ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር ጥሪውን አቅርቧል፡፡
መንግስት፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ የመገናኛ ብዙሀን፣ ሲቪክ ማኅበራት እና ባለድርሻ አካላትም ለጾታዊ እኩልነት መረጋገጥ እና ጾታዊ እኩልነትን የሚቀበል ማኅበረሰብ በመገንባት ረገድ የበኩላቸውን እንዱወጡም ኢሰመጉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡