March 9, 2023 

ዓለምአቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ግልጽ ደብዳቤ ለዶ/ር ዓቢይ አህመድ አሊ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስቴር

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

የካቲት 29 ቀን 2015 ዓም (March 8, 2023)

ለተከብሩ ዶ/ር ዓቢይ አህመድ

ለኢትዮጵያ ሀገራችን ትውልድና ታሪክ ተሻጋሪ የሆነ ለውጥ ያመጣሉ በሚል ተስፋ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ እርስዎንና መንግሥትዎን እስከዛሬ ድረስ በሙሉ ልብ ድጋፉን በመስጠት፤ ወደእናት ሀገሩ የእርዳታ ገንዘብ በመላክ፤ መዋዕለ ንዋዩን በማፍሰስ፤ በድርቅና በግጭት በመፈናቀል ብዙ ጉዳት የደረሰባቸዉን ዜጎቻችንን በመርዳትና መልሶ በማቋቋም፤ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት በሞያ የተደገፈ ምክር በመስጠትና በቁሳቁስ በማገዝ ዳያስፖራው ለሀገሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከእነዚህ በተረፈ፣ ለዐባይ የህዳሴ ግድብ ስኬት ገንዘብ በማዋጣትና በዲፕሎማሲው መስክ ድጋፍ በመስጠት ሰፊ የሆነ ያልተቋረጠ እገዛ አድርጓል። ሀገራችን ኢትዮጵያ በሰሜኑ የትግራይ ጦርነት ሳቢያ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ በገባችበት ወቅትም ዳያስፖራው ከእርስዎ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ከመከላከያና የጸጥታ ኃይሎች ጎን በመቆም፣ ሀገራችንን ለማዳን በተደረገው ከፍተኛ እርብርብ፣ በተለይም በዓለም አቀፉ መስክ ግንባር ቀደም በመሆን በዲፕሎማሲና ሕዝብ ግንኙነት ዙሪያ ዳያስፖራው ያደረገውን ታላቅ ተጋድሎና አስተዋጽኦ ምንግዜም ታሪክ አይረሳዉም።

በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. (Nov 4, 2020) ህወሐት በሰሜን እዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመክፈት፣ በሺህ የሚቆጠሩ ንጹሀንን በተኙበት ሳይቀር ጨፍጭፎ፣ በአማራና አፋር ክልሎችም በዘመተበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው የማታውቀው የዲፕሎማቲክ ዘመቻ፣ የኢኮኖሚ ማዕቀብ እና ከምዕራባውያን እና የአለም አቀፍ ሚዲያዎች ከፍተኛ ጫና ገጥሟት ነበር። ይህን ለመቋቋም በዓለም ዙሪያ ያለው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ከጫፍ እስከጫፍ በመነሳትና በየሲቪክ ማህበሮቻችን በመደራጀት፣ ከፍተኛ የሆነ የዲፕሎማቲክ እንቅስቃሴ አድርገን፣ የጥብቅና ዘመቻዎችን በማደራጀት፣ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ በመስጠት፣ በተለይም የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን እና ሌሎች አለም አቀፍ አካላትን ሎቢ በማድረግ ታላላቅ የዲፕሎማሲ ስኬቶችን አስመዝግበናል። በተጨማሪም ከሰላም ደጋፊ “ፓን-አፍሪካን” አጋሮቻችን ጋር በመተባበርና፤ ትግላችንን በማቀናጀት የ“#በቃ” (#NOMORE) ሰፊና ሕዝባዊ ንቅናቄ በዓለም ዙሪያ የህወሐትን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በማክሸፍ፤ የኢትዮጵያ ችግር የአፍሪካ ሁሉ ችግሩ ሆኖ እንዲታይ፤ የምዕራብ አለም ዜጎች አብረውን እንዲቆሙና ድምጽ እንዲሆኑ ታላቅ አስተዋጽዎ አድርገናል። በአምስት አህጉራትና ከሰላሳ ሁለት በላይ አገሮች ውስጥ ታሪካዊ ታላላቅ ሰለማዊ ሰልፎችን በማድረግ፣ ኢትዮጵያ በአለም አደባባይ የተነፈገችውን ትኩረት ድምጽ ልንሆንላት ችለናል።

እኛ፥ ከእዚህ ደብዳቤ በታች የፈረምነው ዓለም አቀፍ የዳያስፖራ ድርጅቶች፣ ግንባር ቀደም መሪ በመሆን ሌትና ቀን ያለእረፍት በመታገል፤ ለሀገራችን ኢትዮጵያ በምንችለው ሁሉ አቅም፣ በእዉቀት፣ በሞያ፣ በገንዘብ፣ በጉልበትና በጊዜ ከፍተኛ መስዋእትነትን የከፈልን ነን። በከፍተኛ ሀገር ፍቅር ስሜትም ተነሳስተን ይህን አስተዋጽኦ ለማበርከት በመቻላችን ልዩ ኩራት ይሰማናል። ይሁን እንጂ፣ ይህን ስናደርግ የእርስዎን “የብልጽግና ፓርቲ” አጠራጣሪ ታሪክ ማለትም፤ የህወሐትን (ኢህአደግ) ጠባብ የብሄር፣ የዘረኝነትና ከፋፋይ የፖለቲካ መስመርና፣ በሕዝብ ላይ የፈጸመውን ግፍና ደባ ለአፍታም ቢሆን በመርሳት አይደለም። ያንን ሁሉ በሆዳችን ይዘን፤ ሀገራችን ኢትዮጵያን ወደላይ ከፍ በማድረግ፤ ለሕዝባችን ነጻነት፣ ፍትሕ፣ እኩልነትና ብልጽግና የሰፈነበት ስርአት እንዲገነባ “እናሻግራታለን” ያሉንን ቃል ኪዳን ተስፋ በማድረግና በማመን ነበር ከጎንዎ የቆምነው። ይሄም በብዙዎች ዘንድ መደገፍ የማይገባውን ስርአት እንደደገፍን አስቆጥሮን ነበር። አሁን እርስዎና መንግሥትዎ በሕዝብ ላይ የሚያደርሱትን በደልና ግፍ ስናስተዉል ግን፤ እኛም ከሕዝባችን ጋር አብረን የተከዳን አይነት ስሜትና ቁጭት ነው የሚሰማን።

በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቃል ገብተው ባፈረሱት ቃል ኪዳን የተነሳ፣ በእርስዎ አመራር ላይ ያለን እምነት ከምንጊዜውም በበለጠ አዘቅት ወርዷል። ሀቁ እንደሚያሳየው፣ እርስዎ ከአምስት አመት በላይ በመንግሥት ሥልጣን መሪነት በቆዩባቸው አመታት ውስጥ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ እጅግ በሚዘገንን ሁኔታ ላይ ትገኛለች፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎች ተጨፍጭፈዋል፤ በሚልዮን የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል፤ የሕዝቡ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከምንጊዜዉም በበለጠ ተጥሰዋል፤ መንግሥት እራሱ ህገ መንግሥቱን አያከብርም፤ የህግ የበላይነትና ተጠያቂነት የሚባሉት በሀገሪቱ ስማቸውም ተረስቷል፤ ሌብነትና ሙስና የኑሮ ውድነት ሕዝቡን አስመርሮታል፤ በሚልዮን የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎች ለረሀብና ለስደት ተጋልጠዋል፤ ችግሩ ተዘርዝሮ አያልቅም!

ከእዚህ በታች ዋና ዋና የሚያሳስቡንን፤ ለሀገራችን ሠላም፣ ለሕዝባችን ደህንነትና ለህልውናዋ የሚያስጨንቁንንና፤ ሌትና ቀን ቁጭት የሚያሳድሩብንን ክስተቶች ለመዘርዘር እንሞክራለን፥

ለእነዚህና ሌሎች ዘርፈ-ብዙ ተግዳራቶች ከቀን ወደቀን እያደጉ ለመጡ የሀገሪቱ ዉስብስብ ችግሮች መፍትሄ ለመሻት ቁርጠኝነት ባለማሳየትዎ፤ በተለይም የፌደራልና የኦሮሚያ ክልል የጸጥታና አስተዳደር አካሎች ግፍ ሲፈጽሙ እያዩ እንዳላዩ፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ድጋፍ በማሳየትዎ፤ በኢትዮጵያ የስርአት አልበኝነት ባህል እንዲነግስና፤ የህግ የበላይነትና ፍትሕ እንዲጠፉ በሩን ከፍቷል። ለምን እና በማን ስልጣን እንደዚህ አይነት ችግር ያለባቸው ፖሊሲዎች አገሪቱ ተከተለች ለሚለው ጥያቄ ሃላፊነት በእርሶ ላይ ነው – የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የመንግስት ርዕሰ መስተዳድር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እርስዎ ስለሆኑ።

አሁንም በቆራጥነትና በቅንነት ተነሳስተው፤ በማስተዋል ወሳኝ የሆኑ መፍትሄዎችን መውሰድና በቶሎ በሥራ ላይ ማዋል ካልቻሉ፤ በዓለም ላይ እራሷን ለማጥፋት የምትጓዝ ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ ትሆናለች። ያኔ እርስዎና መንግሥትዎ በታሪክ ተወቃሽ ይሆናሉ። ስለዚህ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ድምፅ ለሌለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጽ የመሆን ግዴታ አለበት። ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቃል የገቡትን ለማክበር፣ የአገዛዝዎ ብልሹ አሰራርን ማስተካከያ እድሉ አሁን ነው።

ይህንን አደገኛ አካሄድ በአስቸኳይ ለመቀየር እና ጥፋቶችን ለማረም፣ ዜጎችን ለመጠበቅ እና ቅሬታዎችን ለመፍታት ቆራጥ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወስዱ እንጠይቃለን። ዛሬ የመንግሥት መቀጠል ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ እንደ ሀገር የመቀጠል ህልውና አደጋ ላይ ነው ያለው። አስተዳደርዎ ኢትዮጵያን ከአስገባት ከዚህ አጣብቂኝ ጨለማ ለማውጣት እድሉ በእጅዎ ነው። በሰከነና በእውነት መንፈስ የሚወሰዱ እርምጃዎች ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ባለድርሻ አካላት አሳትፎ ሀገራችንን ለማዳን በአስቸኳይ ስራ እንዲጀመር አጥብቀን እናሳስባለን።

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ልጆቿን ይባርክ!!!

ምንጭ  https://sites.google.com/view/diaspora-movements/home