ተቃውሞ እያደረጉ ያሉ ሱዳናውያን

9 መጋቢት 2023, 13:21 EAT

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በሱዳን ላይ የጣለውን ማዕቀብ አራዘመ።

ምክር ቤቱ ማዕቀቡን እንዲሁም የጦር መሳሪያ ሽያጭ እግዱን ነው ለአንድ ዓመት ነው ያራዘመው።

15 አባላት ያሉት የጸጥታው ምክር ቤት ማዕቀቡን እንዲሁም የመሳሪያ ሽያጭ እገዳውን እንዲከታተሉና እንዲቆጣጠሩ ስልጣን የተሰጣቸው የባለሙያዎች ቡድን ፈቃድን እስከሚቀጥለው ዓመት መጋቢት ድረስ እንዲታደስም ድምጽ ሰጥቷል።

13 አገራት የድጋፍ ድምጻቸውን ሲሰጡ ሩሲያ እና ቻይና በድምጸ ተአቅቦ አልፈውታል።

“ማዕቀቡ ጊዜ ያለፈበት ነው። መሬት ላይ ያሉ ነገሮች ስለተሻሻሉ ሊነሳም ይገባል” ሲሉ የቻይናው ተወካይ ዳይ ቢንግ ተናግረዋል።

“በመንግሥቱ ላይ ማዕቀብ መጣል የዳርፉርን ሁኔታ አያንጸባርቅም። የሱዳን መንግሥትንም ሃገሪቱን ከመገንባት፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገትንም እየከለከለ ነው” ሲሉ የሩስያው ተወካይ ዲሚትሪ ፖሊያንስኪ ተናግረዋል።

የአሜሪካ ተወካይ ጆን ኬሊ በበኩላቸው ክትትል እና ሪፖርት ማድረግ አስፈላጊነትን መቀጠል እንዳለበት ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።

ከሶስት ዓመት በፊት በተፈረመው የጁባ የሰላም ስምምነትን የተቀመጡ መለኪያዎችን በመጥቀስ “ሱዳን እና ህዝቦቿን ወደሚገባቸው ሰላም እና ብልጽግና ያሸጋግራል” ሲሉም ተደምጠዋል።

ሱዳን ከሁለት ዓመት በፊት በጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን በተመራ ጦር በሲቪል የሚመራውን የሽግግር መንግሥት መገርሰሷን ተከትሎ በምጣኔ ኃብት እና በፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች።

ለአስርት ዓመታት ሱዳንንን የገዟት ኦማር አልበሽር በህዝባዊ አብዮት ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ወደ ሲቪል አገዛዝ ልታደርገው የነበረውን ሽግግርም መፈንቅለ መንግሥቱ ገትቶታል ተብሏል።