
9 መጋቢት 2023, 11:48 EAT
ባለፈው ወር የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪውን የሚመሩት ቻይናዊው ቢሊየነር የባኦ ፋን ደብዛ መጥፋት በአገሪቱ እየተለመደ የመጣውን አወዛጋቢ ክስተት፣ የቢሊየነሮች ደብዛ መጥፋት እንደገና መነጋገሪያ አድርጎታል።
ባኦ ፋን፣ ቻይና ሬናይሰንስ ሆልዲንግስ የተባለ ኩባንያ መሥራች ናቸው።
በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ግዙፍ የኢንተርኔት ኩባንያዎች ቴንሰንት፣ አሊባባ እና ባይዱ ደንበኞቻቸው ሲሆኑ በአገሪቱ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ውስጥም እንደ ታላቅ ነው የሚታዩት።
ባኦ ፋን ለቀናት ያህል ከጠፉ በኋላ ኩባንያቸው “በቻይና ባለሥልጣናት እየተካሄደ ባለው ምርመራ ውስጥ እየተባበሩ ነው” የሚል መግለጫ አወጣ።
በቻይና እንደተለመደው የትኛው የመንግሥት አካል ምርመራውን እንደሚያካሂድ፣ ምርመራው በምን ላይ እንደሆነ እንዲሁም ባኦ ፋን የት እንዳሉ እስካሁን የተገለጸ ነገር የለም።
የባኦ ፋን ደብዛ መጥፋት እንቆቅልሹ እስካሁን አልተፈታም። ባኦ ፋን ብቻ ሳይሆኑ ከዚህ ቀደም የአሊባባ ኃላፊ ጃክ ማን ጨምሮ በርካታ የቻይና ቢሊየነሮች ምስጢራዊ በሆነ ሁኔታ ጠፍተዋል።
ምንም እንኳን ደብዛቸው የጠፉ ቢሊየነሮች ጉዳይ የበለጠ ትኩረት ቢያገኝም በቻይና የት እንዳሉ የማይታወቁ በርካታ ግለሰቦች አሉ።
እነዚህ ግለሰቦች ደብዛቸው የጠፋው የፀረ-መንግሥት ተቃውሞዎችን፣ የሰብዓዊ መብት ዘመቻዎችን ከተሳተፉ በኋላ ነው።
የባኦ ፋን መሰወርም ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በቻይና ምጣኔ ሃብት ላይ ያላቸውን ቁጥጥር ከሚያጠናክሩበት አንዱ መንገድ እንደሆነም ተነግሯል።
የቻይና የፋይናንስ ቁጥጥር ሥርዓትም ላይ በዚህ ሳምንት በተደረገው ሕዝባዊ ኮንግረስ የፓርላማ ጉባኤ ለውጥ መደረጉ ተነግሯል።
አብዛኞቹን የፋይናንስ ዘርፎች የሚከታተል አዲስ ተቆጣጣሪ ተቋምም ይመሰረታል። ባለሥልጣናቱ በትሪሊዮን ዶላር የሚገመተውን የቻይና ፋይናንስ ኢንዱስትሪ በሚቆጣጠሩ በርካታ ኤጀንሲዎች የሚፈጠሩ ክፍተቶችን እንደሚዘጋም ያምናሉ።

- “ዛቻዎች” በርትተውብኛል ያለችው ቻይና ወታደራዊ በጀቷን ከፍ አደረገች6 መጋቢት 2023
- “የቻይናን ኃያልነት ለመግታት ረፍዷል”4 ጥቅምት 2020
- ሁሉንም በደህንነት ካሜራ የምትመለከተው ቻይና9 ጥር 2018
በአውሮፓውያኑ 2015 ብቻ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የእግር ኳስ ክለብ ዎልቨርሃምፕተን ዋንደርደርስ ባለቤትና ፎሱን ኢንተርናሽናል ኩባንያ ሊቀመንበር ጉዎ ጉዋንግቸንግን ጨምሮ አምስት ቢሊየነሮች ተሰውረዋል።
ጉዎ በዚያው ዓመት በታኅሣሥ ወር ከተሰወሩ በኋላ ኩባንያቸው የመንግሥት ባለሥልጣናትን በምርመራ እያገዙ መቆየታቸውን አስታውቋል። ኩባንያው ይህንን ያለው ጉዎ መታየት ከጀመሩ በኋላ ነው።
ከሁለት ዓመት በኋላ ቻይናዊ-ካናዳዊ ቢሊየነር ሺያዎ ጂያንዋ በሆንግ ኮንግ ከሚገኝ አንድ ሆቴል ተወሰዱ። በቻይና ውስጥ ሃብታም ከሚባሉት አንዱ የሆኑት ሺያዎ በባለፈው ዓመት በሙስና ወንጀል ለእስር ተዳርገዋል።
በአውሮፓውያኑ 2020 ደግሞ ሌላኛው ቢሊየነር እና በሪል ስቴት የንግድ ዘርፍ ከፍተኛ ሃብት ያከማቹት ሬን ዚቺያንግ ተሰወሩ። ባለሃብቱ ከመሰወራቸው በፊትም የቻይናው ፕሬዝዳንት ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የወሰዱትን እርምጃ “አስቂኝ እና ቀልደኛ” ሲሉም ተችተዋቸው ነበር።
በዚያው ዓመት ከአንድ ቀን የፍርድ ሂደት በኋላ ሬን በሙስና ወንጀል 18 ዓመታት እስር ተፈረደባቸው።
በቻይና የቢሊየነሮች መሰወር ጋር በተያያዘ ከፍተኛ መነጋገሪያ የሆነው የአሊባባ መሥራች ጃክ ማ ደብዛ መጥፋት ጉዳይ ነው።
በወቅቱ በቻይና በሃብት አንደኛ ስፍራን ተቆጣጥረው የነበሩት ጃክ ማ የአገሪቱን የፋይናንስ ተቆጣጣሪዎች ከተቹም በኋላ ነው የተሰወሩት።
ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር የቻይና መንግሥት ላቋቋመው ‘ኮመን ፕሮስፐሪቲ ፈንድ’ ቢለግሱም በቻይና ከታዩ ሁለት ዓመት በላይ ሆኗቸዋል። እስካሁንም በምንም አይነት ወንጀል አልተከሰሱም።
ጃክ ማ በቅርብ ወራት ውስጥ በጃፓን፣ በታይላንድ እና በአውስትራሊያ መታየታቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች ቢወጡም እስካሁን ስላሉበት ቦታ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም።
የቻይና መንግሥት በበኩሉ በአንዳንድ የአገሪቱ ባለጸጎች ላይ የተወሰደው እርምጃ ሕጋዊ መሠረት ያለው ነው በሚል የሚከራከር ሲሆን ሙስናን ከስር መሠረቱ ለመንቀል ቃል ገብቷል።
የቻይና ድርጊት በአሁኑ ወቅት የዓለም ሁለተኛ ትልቅ ኢኮኖሚ ያደረጋትን የአስርት ዓመታትን የሊበራላይዜሽን ሂደት የሚቃረን ነው።
ቻይና ምጣኔ ሃብቷን መክፈቷ በርካታ ቢሊዮነሮች እንዲፈጠሩ ያደረገ ሲሆን፣ እነዚህም ሃብታሞች ካላቸው ሃብት አንጻርም ሥልጣን እንዲኖራቸውም መንገድ ከፍቷል።
ሆኖም አንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚሉት በፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ አገዛዝ ስር የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ሥልጣኑን በዋነኝነት እንዲቆጣጠር እየተሰራ ነው ይላሉ። ይህም ሁኔታ ምስጢራዊ በሆነ መንገድ መከወኑን ነው እነዚህ ታዛቢዎች የሚያስረዱት።
ትልልቅ ቢዝነሶች በተለይም የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪው ተፅዕኖው እያደገ የመጣው ከፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በፊት በነበሩት ፕሬዝዳንቶች ጂያንግ ዜሚን እና ሁ ጂንታኦ ፖሊሲዎች ነው።
ከዚያ በፊት ቻይና ሥልጣን የፌደራሉ መንግሥት እንዲቆጣጠር እና የጦር ኃይሉ፣ የከባድ ኢንዱስትሪ እንዲሁም የክልል መንግሥታት ሥልጣን በማዕከሉ ስር እንዲሰባሰብ ተደርጓል።
- ቻይናን ማፈን አሜሪካን ታላቅ አያደርጋትም- ቤጂንግ7 መጋቢት 2023
- ምዕራባውያንን ያሳሰቡት በቻይና የሚደረጉ የሰው የዘረ-መል ማሻሻያ ሙከራዎች8 መጋቢት 2023
- አሜሪካ በቲክቶክ ላይ የወሰደችውን እርምጃ ቻይና ተቃወመች28 የካቲት 2023
በእነዚህ ዘርፎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር የማድረጉን ሁኔታ በመቀጠል ፕሬዝዳንት ዢ ተከፍቶ የነበረውን ምጣኔ ሃብት በመንግሥት ቁጥጥር ስር ለመመለስ እየሞከሩ ነው። የፕሬዝዳንቱ ‘ኮመን ፕሮስፐሪቲ’ ፖሊሲ በተለይም በቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪው ላይ በማተኮር በምጣኔ ሃብቱ ላይ አንዳንድ እርምጃዎችን ወስዷል።
“እነዚህ ክስተቶች በተለይም ለተወሰኑ ኢንዱስትሪዎች ወይም ቡድኖች መልዕክት ለማስተላለፍ በሚያስችል መንገድ የተቀነባበሩ ናቸው” ሲሉ ዘ ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒትን በመወከል ኒክ ማሮ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ይህም ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ የፕሬዝዳንት ዢ አስተዳደር ምጣኔ ሃብቱን እና ሥልጣንን በማዕከላዊው መንግሥት ቁጥጥር ስር ለማድረግ እየተደረገ ያለውን ሙከራ ያሳያል” ብለዋል።
“ቻይና ትልልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እና ኃላፊዎች የራሳቸውን ተፅዕኖ እንዳይጨምሩ እና እነሱን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንዳይሆን፣ እንዲሁም ከአገሪቱ እሴቶች በተቃራኒ እንዳይሄዱ ትኩረት ያደረገ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው” በማለት የዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት የሆነው አልብራይት ስቶንብሪጅ ግሩፕ የቻይና እና የቴክኖሎጂ ፖሊሲ ኃላፊ የሆኑት ፖል ትሪሎ ያስረዳሉ።
እንዲሁም ቻይና ላወጣችው ኮመን ፕሮስፐሪቲ ፖሊሲ መሠረቱ የሕግ የበላይነት ነው። እናም ሕጎቹ ለሃብታሞችም ሆነ ለድሆች በተመሳሳይ መልኩ ተግባራዊ መሆን እንዳለባቸው የሚደነግግ ነው።
ቻይና ይህ ፖሊሲ በአገሪቱ እየሰፋ የመጣውን የሃብት ልዩነት ለማጥበብ ያለመ እንደሆነ ትናገራለች። በርካቶችም የሚስማሙበት ጉዳይ ይህ የሃብት ልዩነት ትኩረት ካልተሰጠው የኮሚኒስት ፓርቲውን አቋም ሊያዳክም የሚችል ትልቅ ጉዳይ ነው።
በአገሪቱ ያለው ልዩነት እየሰፋ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የፕሬዝዳንት ዢ ፓርቲ ወደ ሶሻሊስት መሠረቱ መመለስ እንደሚገባውም የግራ አክራሪ ፖለቲከኞች ጫና እያደረጉ ነው ተብሏል።
በቢሊየነሮቹ መጥፋት ዙሪያ ያለው እንቆቅልሽ እንዲሁም ቻይና በቢዝነስ ዘርፉ ላይ ያለው ዕይታ ስጋቶችን ያጫረ ሲሆን፣ ያልተጠበቁ ውጤቶችንም ሊያስከትል ይችላል።
አንዳንድ ታዛቢዎች በበኩላቸው የቻይና መንግሥት እየተከተለ ያለው እርምጃ አዳዲስ ንግዶች እንዳይለመልሙ እንደሚያደርግም ይጠቁማሉ።
“ቻይና የቴክኖሎጂ ቢሊየነሮችን ኢላማ ማድረጓ ያለው አደጋ ቀጣዩ ጃክ ማ ለመሆን እየሰሩ ባሉ የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪዎች ላይ የበለጠ ጫና እየፈጠረ ነው” በማለት ፖል ትሪሎ ይናገራሉ።
ሆኖም ፕሬዝዳንት ዢ በንግድ ላይ ያለውን ተነሳሽነትን መናድ አደጋውን የሚረዱ ይመስላሉ። በዚህ ሳምንት በነበረ አንድ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር የግሉ ዘርፍ ለቻይና ያለውን ጠቀሜታ አበክረው ተናግረዋል።
ነገር ግን የግል ኢንተርፕራይዞች እና ሥራ ፈጣሪዎች “ሃብታም እና ኃላፊነት የሚሰማችሁ፤ ሃብታም እና ትክክለኛ፤ ሃብታም እና አፍቃሪ” እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
የቻይናን የፋይናንስ ሥርዓት የሚቆጣጠረው አካል ይቋቋማል ከመባሉ በተጨማሪ፣ የባንክ ባለሙያዎች ባለፈው ወር የምዕራባውያን አቻዎቻቸውን ምሳሌ እንዳይከተሉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።
ይህ የፕሬዝዳንቱ አስተያየት የአገሪቱ የገንዘብ ሥርዓት ትኩረት እንደተደረገበት ተጨማሪ ማስረጃም እንደሆነ ታዛቢዎች ይናገራሉ።
“በተለይም በቅርብ ወራት ውስጥ የኮመን ፕሮስፐሪቲ (የጋራ ብልጽግና) አጀንዳዎች ወደ ፋይናንስ አገልግሎቶች በተለይም በሥራ አስፈጻሚዎች ደመወዝ እና ቦነስ ላይ፣ እንዲሁም በአስተዳደር እና በዝቅተኛ ሠራተኞች መካከል ያለውን የደመወዝ ክፍተቶችን በተመለከተ አንዳንድ ፍንጮች እያየን ነው” በማለት ኒክ ማሮ ይናገራሉ ።
ፕሬዝዳንት ዢ በቢሊየነሮች ላይ እየወሰዱት ያለው እርምጃ ሥልጣናቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ለማጠናከር ይረዳቸዋል የሚለው ጉዳይ ወደፊት የሚታይ ይሆናል።
ሆኖም በአሁኑ ወቅት በቻይና የፋይናንስ ገበያዎች፣ ቢዝነስ እንዲሁም በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ ያለው መተማመን አደጋ ላይ ነው።