ማኅበራዊ ሚዲያ

9 መጋቢት 2023, 13:20 EAT

በኢትዮጵያ የተወሰኑ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የተጣለው ገደብ እንዲነሳ የመብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ።

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎቹ ከተገደቡ አንድ ወር እንደሞላቸው ዛሬ ሐሙስ የካቲት 30/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው አምነስቲ፣ የአገሪቱ ባለሥልጣናት የጣሉትን ገደብ እንዲያነሱ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሕገወጥ ነው ካለችው የጵጵስና ሹመት እና የሲኖዶስ ምሥረታ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎቹ ከየካቲት 02/2015 ዓ.ም. ጀምሮ መገደባቸውን አምነስቲ አስታውሷል።

የቤተ ክርስቲያኗ አባቶች ከሹመቱ ጋር ተያይዞ መንግሥት ጣልቃ በመግባት ወረራዎች፣ እስሮች እና ግድያዎች ተፈጽመዋል በሚልም ሰልፍ ተጠርቶ የነበረ ሲሆን፣ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎቹ መገደብም ከዚህ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ነው አምነስቲ በመግለጫው ያስታወቀው።

“የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የተወሰኑ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሆኑትን ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ቲክቶክ እና ዩቲዩብ ማኅበረሰቡ እንዳይጠቀም ከገደበ አንድ ወር ሞላቸው። ይህም የዜጎችን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና መረጃን የማግኘት መብቶችን በግልጽ የሚጥስ ነው” ሲሉም የአምነስቲ የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ፍላቪያ ምዋንጎቪ መናገራቸው ሰፍሯል።

በተጨማሪም የአገሪቱ ሕገ መንግሥት እንዲሁም የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች የተቃረነ መሆኑንም ነው ምክትል ዳይሬክተሯ የተናገሩት።

ከቤተ ክርስቲያኗ በተከሰተው ችግር ጋር በተያያዘ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ባልሆነ ኃይል በጥይት እና በድብደባ ግድያዎችን መፈጸማቸውን ኢሰመኮ ማስታወቁ ይታወሳል። በዚህም በጥይት እና በድብደባ ስምንት ሰዎች ሻሸመኔ ውስጥ መገደላቸውን ኢሰመኮ የገለጸ ሲሆን ቤተ ክርስቲያኗ በበኩሏ ቁጥሩ ከዚህ ከፍ ያለ ነው ብላለች።

በቤተ ክርስቲያኗ አባቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረው ችግር እልባት ማግኘቱን እና ቤተ ክርስቲያኗ ችግሩን በሃይማኖታዊ ቀኖና እና ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ እንደተፈታም ማስታወቋ ይታወሳል።

በተመሳሳይ መልኩ በተወሰኑ ማኅበራዊ የትስስር ገጾች ላይ የተጣለው ዕቀባ “የሰዎችን መረጃ የማግኘት ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ገደብ የሚጥል እና የሚጋፋ ስለሆነ” ሊነሳ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ዛሬ ባወጣው መግለጫው ጠይቋል።

በተጨማሪም በአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ ጉዳት ስለማድረሱ እና ሚዲያዎች ሥራቸውን ለሕዝብ እንዳያቀርቡ እክል በመፍጠሩ መንግሥት ገደቡን እንዲያነሳው ከዚህ ቀደም በመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት መጠየቁንም ኢሰመጉ አስታውሷል።

በኢትዮጵያ በተወሰኑ የማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተጣለው እገዳ ምክንያት ተገልጋዮች የትስስር መድረኮቹን ለማግኘት ቪፒኤን የተባሉትን መተግበሪያዎች ለመጠቀም ተገደዋል።

እገዳውን ተከትሎ እነዚህን ዕቀባ የተጣለባቸውን የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮችን በተዘዋዋሪ ለመገልገል የሚውሉትን የቪፒኤን መተግበሪያዎችን ፍላጎት እና ተጠቃሚነት በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ቶፕ ቴን ቪፒኤን የተባለው ድረ ገጽ አመልክቷል።

ኢሰመጉ በበኩሉ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች እነዚህን ማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች በሚያገኙዋቸው ቨርችዋል ፕራይቬት ኔትወርክ ለመጠቀም በመገደዳቸው “የመረጃዎችን የደኅንነት ጉዳይ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንዲገኝ አድርጎታል” ብሏል።

አምነስቲ ባለሥልጣናቱ የጣሉትን ገደብ ሳይዘገዩ እንዲያነሱ እና “በሰዎች ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ እንዲሁም መረጃዎችን የማግኘት እና የመቀበል መብት ላይ ጣልቃ ከመግባት ይቆጠቡ” ሲል አሳስቧል።

ይህ እርምጃም አገሪቱ በሚዲያ ነጻነት ላይ ያላትን አያያዝ የበለጠ የሚያጠለሽ መሆኑንም ምክትል ዳይሬክተሯ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ለዓመታት መጠነ ሰፊ ተቃውሞዎች በሚያጋጥሙበት እና በግጭት አካባቢዎች በተደጋጋሚ ኢንተርኔት እንደሚዘጋ የተለያዩ ድርጅቶች ሪፖርት ማድረጋቸውን የዛሬው የአምነስቲ መግለጫ አስታውሷል።

በዚህም በትግራይ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎም ክልሉ ከማንኛውም የመገናኛ ዘዴዎች እንዲቆራረጥ የተደረገ ሲሆን፣ ከወራት በፊት የተደረሰውን ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ተከትሎም በተወሰነ መልኩ ኢንተርኔት ተመልሷል ብሏል።