March 9, 2023 

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ተደጋጋሚ ጥቃት የሚያደርሰው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በወረዳው ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

በወረዳው ውስጥ በምትገኘው ባቡ ድሬ ቀበሌ በርካታ የሆኑ የሸኔ ታጣቂዎች ከተለያየ ቦታ እየመጡ መሰባሰባቸውን የተናገሩት የአዲስ ማለዳ ምንጮች፣ ከዚህ ቀበሌ ባሻገር ሰው በማይኖርባቸው በረሃዎች በርካታ ታጣቂዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

የሸኔ ታጣቂዎች አጎራባች ከሆኑ የሰሜን ሸዋ ወረዳዎች ወደ ደራ ወረዳ እየገቡ እንደሆነ የተናገሩት ምንጮች፣ የታጣቂዎቹ ብዛት ከዚህ በፊት ከታዩት የበለጠ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ይህም በነዋሪዎች ላይ ስጋት ፈጥሯል ያሉት ምንጮች፣ የሸኔ ታጣቂዎች ከዚህ በፊት በወረዳዋ ነዋሪዎች ላይ ከሚያደርሱት ጥቃት አንጻር ስጋቱ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ለሸኔ ታጣቂዎች ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል እጃቸወን ለፖሊስ ከሰጡ ታጣቂዎች መካከልም የተሀድሶ ስልጠና ሳይሰጣቸው ከኅብረሰተቡ ጋር መቀላቀላቸውን የተናገሩት ምንጮች፣ በጉዳዩ ዙሪያ በመንግስት አካላት ጥንቃቄ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

አዲስ ማለዳ ከቀናት በፊት የወረዳው ነዋሪዎች በሸኔ ታጣቂዎች እየታፈኑ መሆኑን መዘገቧ የሚታወስ ሲሆን፣ የታፈኑት ሰዎች እስከ 300 ሺሕ ብር የሚደርስ የማስለቀቂያ ክፍያ እየተከፈለላቸው መለቀቃቸው ተሰምቷል፡፡

ባለፉት አስራ አምስት ቀናት ውስጥም ሌላ የአፈና ዜና ያልተሰማ ቢሆንም አሁንም ስጋቶች እንዳሉ ምንጮች ተናግረዋል፡፡

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ዙሪያ የወረዳው አስተዳደርን ምላሽ ለማግኘት ጥረት ያደረገች ቢሆንም፣ የወረዳው አስተዳዳሪና የአስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ምላሽ አልሰጡም፡፡

Source :  Addis Maleda