የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አባል የሆኑት ወይዘሮ ጠጄ ደነቀን ጨምሮ በቡታጅራ ከተማ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ አሊያም እንዲፈቱ የሕግ ባለሙያዎች ግፊት እያደረጉ ነው። ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ እስር ላይ ከቆዩ 21 ግለሰቦች መካከል የቀድሞ የዞኑ አመራሮች፣ ወጣቶች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እንደሚገኙበት ለተጠርጣሪዎቹ ጥብቅና ለመቆም ጥያቄ ካቀረቡ የሕግ ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት አቶ ቀኙ ሙሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
“ጥብቅና ልንቆምላቸው የሔድን ሰዎች በቅርብ ጊዜ የታሰሩት ቁጥራቸው 21 ነው። በተጠረጠሩበት ወንጀል ፍርድ ቤት መቅረብ ነበረባቸው። ፍርድ ቤት አልቀረቡም” የሚሉት አቶ ቀኙ ተጠርጣሪዎቹ በታሰሩበት ቦታ ለሕግ ባለሙያዎች ውክልና እንዲሰጡ ባይፈቀድላቸውም አራት ጠበቆች ለጉራጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረባቸውን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።Audio Player
00:00
00:00
Use Up/Down Arrow keys to increase or decrease volume.
“ፍርድ ቤት የማይቀርቡ ከሆነ የኢትዮጵያ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት አካልን ነጻ ማውጣት የሚባል ሥነ-ሥርዓት አለ። በዚያ ሥነ-ሥርዓት መሠረት ፍርድ ቤት እነዚህ ሰዎች የተያዙበት መንገድ አግባብ ስላልሆነ፤ ፍርድ ቤትም ስላልቀረቡ የሚፈቱበትን ትዕዛዝ እንዲሰጥ ለመጠየቅ ለመወከል ነው ያሰብንው” ሲሉ ጠበቃው ተናግረዋል።
በቡታጅራ ከተማ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በእስር ላይ ከነበሩት 21 ሰዎች መካከል ሁለቱ ባለፈው ማክሰኞ እና ረቡዕ ተፈተዋል። የጉራጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የደቡብ ፖሊስ ኮሚሽን በተጠርጣሪዎቹ ጉዳይ ላይ ምላሽ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን ጉዳዩ ለመጋቢት 6 ቀን 2015 ተቀጥሯል።
በቡታጅራ፣ ወልቂጤ፣ ቋንጤ እና እና አዲስ አበባ የታሰሩ ሰዎች የጉራጌ ዞን ክልል እንዲሆን ከሚደረገው ግፊት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር የዋሉ ናቸው።
በቡታጅራ በእስር ላይ ከሚገኙት መካከል የካቲት 21 ቀን 2015 በጸጥታ ኃይሎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተወስደው የታሰሩት የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አባል ወይዘሮ ጠጄ ደነቀ ይገኙበታል። ከታሳሪዎች ብቸኛዋ ሴት የሆኑት ወይዘሮ ጠጄ የመውለጃ ቀናቸውን የሚጠባበቁ እርጉዝ መሆናቸው የቅርብ ቤተሰባቸው ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።
“የሰባት ወር ነፍሰ ጡር ናት። የዞኑ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ናት። የቋሚ ኮሚቴ አባል ናት” ያሉት ወንድማቸው አቶ መስፍን ደነቀ የካቲት 21 ቀን ለሊት በደቡብ ክልል ልዩ ኃይል አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።
ወይዘሮ ጠጄ በዞኑ ምክር ቤት አባልነታቸው ወንጀል ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ ካልተያዙ በቀር ያለመከሰስ መብት ነበራቸው። ይኸ መብታቸው ግን ከመታሰር አላዳናቸውም። “የወንጀል ሥነ-ሥርዓቱ የሚፈቅደው የምክር ቤት አባል ያለመከሰስ መብት ቢኖረውም እጅ ከፍንጅ ወንጀል ሲፈጽም ከተገኘ ሊያዝ ይችላል። ወይዘሮ ጠጄ ግን የተያዙበት ሁኔታ ከዚህ የሚለይ ነው” የሚሉት ጠበቃ ቀኙ “ከመኖሪያ ቤታቸው በለሊት እንደተያዙ” ከራሳቸው መረዳታቸውን ገልጸዋል።
ያለ መከሰስ መብት እያላቸው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግን ወይዘሮ ጠጄ ደነቀ ብቻ አይደሉም። በ2005 በተካሔደው የአካባቢ ምርጫ በእንሞር እና ኤነር ወረዳ ተወዳድረው የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ መኑር ረሺድ በአዲስ አበባ ከተማ ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ገጥሟቸዋል። አቶ መኑር በቁጥጥር ሥር ሲውሉ በእጃቸው የምክር ቤት አባል መሆናቸውን የሚያረጋግጥ መታወቂያ እንደነበራቸው ጠበቃቸው አቶ ቶፊቅ በድሩ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።
“በእጃቸው በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት አባል ስለሆኑ እጅ ከፍንጅ ከባድ ወንጀል ሲፈጽሙ ካልተያዙ በስተቀር ያለመከሰስ መብት አላቸው የሚል ስማቸው ተጠቅሶ፤ ፎቷቸው ያለበት መታወቂያ በእጃቸው ይዘዋል። ይኸንን ያለመከሰስ መብት እንዳላቸው ጠቅሰው ለፖሊስ ሰጥተዋል። መታወቂያው ፖሊስ እጅ ነበር” ሲሉ ጠበቃ ቶፊቅ በድሩ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በፌድራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩት አቶ መኑር የካቲት 24 ቀን 2015 በፌድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ከቀረቡ ሰባት ተጠርጣሪዎች መካከል ናቸው። ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አብዛኞቹ የካቲት 22 ቀን 2015 በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉ መሆናቸውን ጠበቃ ቶፊቅ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በዚህኛው ምድብ ከአቶ መኑር በተጨማሪ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ የሆኑት አቶ ጀምበር አብዶ፣ የጉራጌ ሚዲያ ኔትዎርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ በየነ ወልዴ እና የቶቶት ወጣቶች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳለ ንዳ ይገኙበታል።
ለተጠርጣሪዎቹ ጥብቅና ከቆሙ የሕግ ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት አቶ ቶፊቅ “በጉራጌ ዞን አካባቢ በህቡዕ ወጣቶችን አደራጅተው በጦር መሳሪያ የታገዘ አመጽ አሲረዋል፤ በዚሁ ምክንያት በጉራጌ ዞን የሰው ሕይወት አልፏል፤ ንብረት ወድሟል ይኸም የእነሱ እጅ አለበት” በሚል እንደጠረጠራቸው ፖሊስ የካቲት 24 በነበረው ችሎት ማስረዳቱን ይናገራሉ። ፖሊስ “መጠኑ ያልታወቀ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ውጪ አገር ከሚኖሩ የጸረ-ሰላም ኃይሎች እየሰበሰቡ ነው። ይኸን ገንዘብ የሚሰበስቡት ለሽብር ለማዋል ነው» በሚል ጭምር እንደጠረጠራቸው ማስረዳቱን አቶ ቶፊቅ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
የአቶ መኑርን ጉዳይ የካቲት 27 ቀን 2015 የተመለከተው ፍርድ ቤት በነጻ እንዲለቀቁ ወስኖ የነበረ ቢሆንም ትላንት ረቡዕ ዳግም መታሰራቸውን አቶ ቶፊቅ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የቀሪዎቹ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ ፖሊስ ለምርመራ ተጨማሪ ቀናት እንዲሰጠው በጠየቀው መሠረት ለመጋቢት 4 ቀን 2015 ተቀጥሮ የነበረ ቢሆንም ከአዲስ አበባ ወደ ቡታጅራ መወሰዳቸውን ዶይቼ ቬለ ከጠበቆች፣ ከታሳሪዎች ቤተሰቦች እና ጉዳዩን በቅርብ ከሚከታተሉ ግለሰቦች አረጋግጧል።
ባለፈው ጥር 29 ቀን 2015 የተካሔደው ሕዝበ-ሳኔ ውጤት «ደቡብ ኢትዮጵያ» የተባለ ክልል ያቋቁማል ተብሎ ይጠበቃል። ይኸ ደግሞ በጉራጌ ዞን ሥር የሚገኙ ብሔረሰቦችን እና ሐድያ፣ ስልጤ፣ ሐላባ እና ከምባታ ጠምባሮ ዞኖች እንዲሁም የም ልዩ ወረዳን ለብቻቸው ያስቀራቸዋል።
በጉራጌ ዞን ቋንጤ በተባለች አነስተኛ ከተማ የጉራጌ ክልል እንዲመሠረት ከሚደረገው ግፊት ጋር በተያያዘ ሁለት የመንግሥት ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር ውለው እንደነበር ዶይቼ ቬለ ከሥራ ባልደረቦቻቸው አረጋግጧል። ባለፈው አርብ የካቲት 24 እና በማግስቱ የካቲት 25 ቀን ከታሰሩት ሁለት የመንግሥት ሠራተኞች መካከል አንዱ በዋስ ተፈተዋል። የዞኑ ዋና ከተማ በሆነችው ወልቂጤ ከታሰሩ 8 ሰዎች መካከል አራቱ መፈታታቸውን ዶይቼ ቬለ ጉዳዩን በቅርበት ከሚከታተሉ ሰዎች ተረድቷል።
የጉራጌ ክልል እንዲመሠረት የሚደረገው ግፊት የዞኑን ልሒቃን ከክልሉ እና ከፌድራሉ መንግሥት ያቃቃረ ጉዳይ ነው። አቶ ቶፊቅ “ጉራጌ ክልል መሆን አለበት ብለው የሚደግፉትን ግለሰቦች ማሰር እና ማሸማቀቅ” የፍትኅ ሥርዓቱ የደረሰበትን ማሳያ እንደሆነ ይተቻሉ። “ሕገ-መንግሥታዊ መብት ይከበር እያለ የሚጮህ ዜጋ ባለበት አገር በምክር ቤት እጁን አንስቶ ድምጽ ስለሰጠ፤ ክላስተር አልደግፍም ስላለ እሱን ነጥለህ ማሰር እና ፍርድ ቤት አለማቅረብ ሰሚ የሌለ መሆኑን፤ የፍትኅ ሥርዓቱ በጣም አሳዛኝ ሁኔታ ላይ የደረሰ መሆኑን የሚያሳይ ነው” ሲሉ ይተቻሉ።
የጉራጌ ክልል እንዲቋቋም በዞኑ ሲደረግ የነበረው ግፊት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ረገብ የማለት አዝማሚያ አሳይቷል። የዞኑ ምክር ቤት ካሳለፋቸው ውሳኔዎች በተጨማሪ ወልቂጤን ጨምሮ በተለያዩ የጉራጌ ዞን ከተሞች የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ ነዋሪዎች በመንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር ሙከራ ሲያደርጉ ነበር። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው እና ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ የቋንጤ ከተማ ነዋሪ “ግለቱ አለ፤ ነገር ግን እንደ በፊቱ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መጻፉ፤ ሰልፍ መውጣቱ መንግሥት እየወሰደ ያለውን አፈና ተከትሎ በውስጥ እንዲመራ ወጣቱም ጭምር ግንዛቤ እየሰጠ ያለበት ሒደት አለ። ውስጥ ውስጡን እንቅስቃሴዎች አሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
ከሶስት ተከታታይ ሕዝበ-ውሳኔዎች በኋላ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ወደ አራት ተከፍሎ ታሪክ ሊሆን በሒደት ላይ ይገኛል። ደቡብን ታሪክ የሚያደርጉት ሕዝበ-ውሳኔዎች የተካሔዱት ራስን በራስ የማስተዳደርን ጨምሮ በተከታታይ ከተነሱ ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች እና ግፊቶች በኋላ ነው።
የዞኑን ልሒቃን ከክልሉ እና ከፌድራል መንግሥት ያቃቃረው ጥያቄ በምን መንገድ መፍትሔ እንደሚያገኝ እስካሁን በግልጽ አይታወቅም። ባለፈው ጥር 29 ቀን 2015 የተካሔደው ሕዝበ-ሳኔ ውጤት “ደቡብ ኢትዮጵያ” የተባለ ክልል ያቋቁማል ተብሎ ይጠበቃል። ይኸ ደግሞ በጉራጌ ዞን ሥር የሚገኙ ብሔረሰቦችን እና ሐድያ፣ ስልጤ፣ ሐላባ እና ከምባታ ጠምባሮ ዞኖች እንዲሁም የም ልዩ ወረዳን ለብቻቸው ያስቀራቸዋል። ጉዳዩ ከጉራጌ ልሒቃን ተቃውሞ ቢገጥመውም የደቡብ ክልል ባለሥልጣናት “ማዕከላዊ ኢትዮጵያ” የተባለ ክልል ለማቋቋም ዝግጅቶች እያደረጉ ነው። ሒደቱ ግን የዞኑ ነዋሪዎች ለከፋ ሐዘን የዳረገ ጉዳይ ሆኗል።
የወይዘሮ ጠጄ ወንድም አቶ መስፍን “ሰብዓዊነት የተረገጠበት፤ መብታችን የት እንዳለ የማናውቅበት፤ እናት ውኃ ጠማኝ ብላ በወጣችበት ልጇን የተነጠቀችበት አገር ላይ ነው ያለንው” ሲሉ ይናገራሉ። “በብሔር እየተለየ የምንመታበት አገር ሆኗል። ባለማንበት፤ ሰርተን፣ ደፋ ቀና ብለን፣ ዝቅ ብለን እየሰራን አገር ባለማንበት እጣ ፈንታችን ዛሬ ዱላ ሆኗል፤ ጥይት ሆኗል፤ እስር ሆኗል፤ ግራ ገብቶን ቁጭ ብለናል” ሲሉ በሐዘን እና በቁጭት አቶ መስፍን ይብሰለሰላሉ።
በዚህ ዘገባ ላይ ዶይቼ ቬለ የጉራጌ ዞን አስተዳደር የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እና የደቡብ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊዎች መልስ ለማካተት በተደጋጋሚ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
