March 11, 2023 

ብሊንከን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ስለመላው ኢትዮጵያውያን ተጨንቀው አሊያም ስለ አሜሪካና ኢትዮጵያ ኝኙነት ተጠበው አስበው ሳይሆን በዋናነት ትኩረታቸው በሕወሓት የመኖር ሕልውናን የማስቀጠል እና ጠንካራ ሆኖ ወጥቶ በአሜሪካ አጋርነቱ እንዲቀጥል እንዲሁም ወልቃይትና ጠገዴን ለማስመለስ የአብይ አስተዳደር ከሱዳን ጋር በመቀናጀት ማድረግ ያለበትን አሜሪካ መተባበር ያለባትን ስትራቴጄ ለመነጋገር መሆኑ ታውቋል። የአሜሪካ መንግስት መግለጫ በዝርዝር የሰጣቸው መግለጫዎች ከዚህ በታች ይገኛሉ።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን የፊታችን ረቡዕ፤ መጋቢት 6 ወደ ኢትዮጵያ እንደሚሄዱ የመሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ገልጸዋል። ብሊንከን ኢትዮጵያ የሚሄዱት ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ የግጭት ማስወገጃውን ሥምምነት አተገባበር ለመከታተል፣ ሰላምን ለማጠናከርና በሽግግሩ ወቅት ፍትህ እንዲገኝ የሚደረገውን ጥረት ለማበረታታት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ለመምከር መሆኑ ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ወቅት የሰብዓዊ ድጋፍ አጋሮችንና የሲቪል ማኅበራት ተጠሪዎችን እንደሚያነጋግሩና ሰብዓዊ እርዳታ በሚቀላጠፍበት፣ በምግብ ዋስትናና በሰብዓዊ መብቶች ላይ እንደሚመክሩ ታውቋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንክን በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጋር ተገናኝተው በዓለም አቀፍ እና በአህጉራዊ ደረጃ ቅድሚያ ትኩረት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ። ዋሽንግተን ውስጥ በተካሄደው የዩ ኤስ አፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ላይ በተገቡት ቃሎች ዙሪያ ይነጋገራሉ።

አፍሪካ በዓለም አቀፍ ተቋማት በቋሚ መቀመጫ እንድትወከል ዩናይትድ ስቴትስ የምትደግፍ መሆኗን እንደሚያረጋግጡ ከቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ቢሮ የወጣው መግለጫ አውስቷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአዲስ አበባ ጉብኝታቸው በኋላ በማግስቱ ሀሙስ የመጀመሪያቸው ለሚሆነው ጉብኝት ወደኒጀር እንደሚያቀኑ መግለጫው አመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን በመጭው ሣምንት የሚያደርጉት የኢትዮጵያና የኒዠር ጉብኝት ሃገራቸው ለአፍሪካ እየሰጠች ያለችውን ትኩረት የሚያመላክት መሆኑን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ አስታወቁ።

ሚስ ፊ የሚኒስትሩን ጉብኝት አስመልክቶ ዛሬ ለጋዜጠኞች በቴሌኮንፍራንስ በሰጡት ማብራሪያ ፕሬዚዳንት ባይደን ባለፈው ታኅሣስ የአፍሪካን መሪዎች ዋሺንግተን ዲሲ ላይ ማስተናገዳቸውን፣ ብዙ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናትና ክቡራን ዜጎች ወደ አፍሪካ መሄዳቸውን፣ ከመካከላቸውም ቀዳሚት እመቤት ጂል ባይደን፣ የገንዘብ ሚኒስትሯ ጃኔት የለን፣ በመንግሥታቱ ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ እንደሚገኙበት አስታውሰዋል። ሌሎች ብዙ ባለሥልጣናትም ያንን ግንኙነት ለማጠናከርና ለማስፋት እንደሚሄዱ ፊ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲወርድ ብሊንከን ሥራቸውን ከጀመሩ አንስቶ ልዩ ትኩረት ሰጥተው መሥራታቸውን ያመለከቱት ፊ ኬንያና ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በተደረጉ ጥረቶች ባለፈው ጥቅምት 23 ፕሪቶሪያ ላይ ለተፈረመው ግጭት የማቆም ስምምነት ዩናይትድ ስቴትስ ቁልፍ ሚና መጫወቷን ገልፀዋል። የአሁኑ የብሊንከን ጉብኝት ያ ሰላም የሚጠናከርበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚያግዝም አመልክተዋል።

አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላት ሞሊ አስታውሰው “የራሳቸውን ዜጎች ለማሳደግ፣ እንዲሁም በቀጣናው ጉዳዮች ውስጥም በኃላፊነት መንፈስ በመሣተፍ እጅግ ጠቃሚ ተግባር እያከናወኑ ነው” ብለዋል። “በመሆኑም – አሉ ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ በመቀጠል – እኛም ግዝፈታቸውንና ያላቸውን ተፅዕኖ የሚመጥን አፍሪካ ውስጥ ያሉንን ጥቅሞችና ለአህጉሪቱ ያለንን ቁርጠኛነትም የሚተካከል ግንኙነት መፍጠር እንፈልጋለን።”

“ሆኖም ያ ግንኙነት ወደፊት እንዲገፋ የቅርቡን ጦርነት ጨምሮ ሃገሪቱን በብዙ አሥርት ዓመታት ወደኋላ ከዘፈቋት የጎሣ ሁከቶች መውጣት አለባት” ብለዋል ፊ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለዩኤስ – አፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ዋሺንግተን ተገኝተው በነበረ ጊዜ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስርት ብሊንከንና ከብሄራዊ የፀጥታ አማካሪው ጄክ ሱለቫን ጋር ‘መልካም’ ያሏቸውን ውይይቶች ማድረጋቸውንና ከዚያ በኋላም የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ባለሥልጣናት ከኢትዮጵያዊያኑ ጋር በተከታታይ እየተገናኙ መቆየታቸውን ገልፀዋል።

የሚኒስትር ብሊንከን የመጭው ሣምንት ጉብኝት ፀቡን ባስቆመው ስምምነት ውስጥ ቁልፍ የአመራር ሚና ለተጫወቱት ምሥጋና ለማቅረብና አዲስና አዎንታዊ ግንኙነቶችን ለማጠናከርም መንገድ ለመክፍረት የታሰበ መሆኑ ሚስ ፊ አመልክተዋል።

የኤርትራ ወታደሮች በብዙ የወሰን አካባቢዎች አሁንም እንዳሉና የአማሪአ ሚሊሽያም ሰፊ የሆነ አካባቢ ምዕራብና ደቡብ ትግራይ ውስጥ ይዘው እንደሚገኙ እርዳታ አቅራቢዎችና ዲፕሎማቶች እንደሚናገሩ፣ ስለዚህ ጉዳይ እርሳቸው የሚያቁት ይኖር እንደሆነና ብሊንከንም በዚህ ላይ ሊያደርጉ ያሰቡት ሥራ እንዳለ የተጠየቁት ሞሊ ፊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ባደረጓቸው የቀደሙ ውይይቶች ጉዳዩን ማንሳታቸውን ተናግረዋል። እስከሚያውቁት ድረስም ውጊያው ሰሜን ትግራይ ውስጥ መቆሙን፣ ግዙፍ ቁጥር ያላቸው የኤርትራ ወታደሮችም ከሰሜን ትግራይ መውጣታቸውን በስምምነቱ መሠረት የተቋቋመው የአፊሪካ ኅብረት የክትትልና አረጋጋጭ አካል ማረጋገጡን ገልፀዋል።

ሰብዓዊ እርዳታም ግጭት ወደጎዳቸው የሰሜን ማኅበረሰቦች ሁሉ እየደረሰ መሆኑን፤ ትግራይን እጅግ በጎዳ ሁኔታ ተቋርጠው የነበሩ አገልግሎቶች እንደገና መጀመራቸውን ማስተዋላቸውንም የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል አንድ ሥራ ላይ ያለ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኒዠርን ሲጎበኝ አንተኒ ብሊንከን የመጀመሪያው እንደሚሆኑ ተገልጿል።

ዘገባዎቹ የተወሰዱት ከአሜሪካ ድምፅ ነው