March 11, 2023 – BBC Amharic

ሺ ሺንፒንግ
የምስሉ መግለጫ,ሺ ታማኛቸው የሆኑትን ሊን አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው ሾመዋል

ከ 6 ሰአት በፊት

የቻይናው ሺ ጂንፒንግ ለሦስተኛ ዙር አገሪቱን ለመምራት ቃለ መሐላ ፈጸሙ።

ሺ የሕይወት ዘመን መሪ ቢሆኑም በደንቡ መሠረት የቻይና የተወካዮች ምክር ቤት በሚባለው አዳራሽ ተገኝተው ቃለ መሐላ ፈጽመዋል።

የ69 ዓመቱ ሺ በቻይና ታሪክ ከፍተኛ ሥልጣንና የፖለቲካ ቁጥጥር ካላቸው መሪዎች ተርታ ይመደባሉ።

በቻይና መንግሥት መዋቅር ከፍተኛው ሥልጣን የሚመነጨው ከፓርቲው ነው።

የእርሳቸው ከፍተኛው የሥልጣን እርከንና ቁጥጥርም ከፕሬዝዳንትነት ይልቅ የኮሚኒስት ፓርቲው ዋና ጸሐፊ እንዲሁም የማዕከላዊ ወታደራዊ ኮሚሽን (CMC) ሊቀመንበር ከመሆናቸው ላይ ነው።

ሁለቱን ቁልፍ ሥልጣኖች ሺ የተረከቡት ባለፈው ጥቅምት ነበር።

ሺ ያን ጊዜ ለሦስተኛ ዙር ፕሬዝዳንት እንደሚሆኑም የሚጠበቅ ነበር።

ከፕሬዝዳንት ሺ ቃለ መሐላ መፈጸምና ሦስተኛ ዘመን በፕሬዝዳንትነት ሥራ ከመጀመር ይልቅ አሁን ትኩረት የተሰጠው አዲስ ለሚሾሙ ሚኒስትሮች ማንነት ነው።

የፕሬዝዳንቱ ታማኝ ናቸው የሚባሉት ሊ ቺያንግ ከጥቂት ሰዓታት በፊት አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሰይመዋል።

ሊ ይህን ሥልጣን ከመቆናጠጣቸው በፊት በቻይና ትልቅ ከተማ ሻንጋይ የኮሚኒስትር ፓርቲ መሪ ነበሩ።

ሊ ቺያንግ 63 ዓመታቸው ነው።

ድምጽ በሚሰጥበት ጊዜ ማንም ጋዜጠኛ እንዲገባ ያልተፈቀደ ሲሆን በውጤቱም 2936 አባላት ድምጽ ሰጥተዋቸዋል። ተቃውሞም ሆነ ድምጽ ተአቅቦ አልተመዘገበም።

በዚህም መሠረት ሊ ቺያንግ በቻይና ሁለተኛው ቁልፍ ባለ ከፍተኛ ሥልጣን ይሆናሉ ማለት ነው።

አዲስ የሚሾሙት ሌሎች ሚኒስትሮች ለሺ ጂንፒንግ ፍጹም ታማኝ የሆኑት ብቻ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

ቻይና ዜሮ የኮቪድ ፖሊሲ የፈጠረባት ተቃውሞና የወሊድ ምጣኔ መቀነስ የቅርብ ጊዜ ፈተናዎች ሆነው ተመዝግበዋል።

የወሊድ ምጣኔው መቀነስ የቻይና የኢኮኖሚ ግስጋሴን እንዳይገታው ስጋት አለ።

ቤጂንግ ከዋሺንግተን ጋር በየጊዜው እየሻከረ የመጣው ግንኙነት በአዲሱ አስተዳደር ምን ሊመስል ይችላል የሚለውም ሌላው የፖለቲካ ተንታኞችን የሳበ ጉዳይ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቻይና ላከቻቸው የተባሉ የስለላ ፊኛዎች የሁለቱን ኃያል አገራት ግንኙነት በመጠኑ አበላሽቶታል።

ከማኦ ዜዶንግ ወዲህ በቻይና ፕሬዝዳንቶች ከሁለት ዘመን በላይ እንዳያገለግሉ ይደረግ ነበር።

ከአምስት ዓመታት በፊት ይህን ደንብ የሻሩት ሺ አሁን ለሦስተኛ ጊዜ በፕሬዝዳንትነት ለማገልግል ቃለ መሐላ ፈጽመዋል።

ትናንት ዐርብ በተደረገው ጉባኤ የ68 ዓመቱ ሃን ዠንግ ምክትል ፕሬዝዳንት አድርጎ መርጧቸዋል። ዠንግ የፖሊት ቢሮ ቋሚ ኮሚቴ አባል ናቸው።

በቻይና ምክትል ፕሬዝዳንትና ሌሎች ሥልጣኖች በትክክል ኃላፊነታቸው በውል የሚታወቅ ባይሆንም የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ዋንግ ኪሻን የጸረ ሙስና ዘመቻን የመሩ ሰው ናቸው።

ምናልባት አዲሱ ምክትል ፕሬዝዳንትም ይህን ኃላፊነት የሚወጡ ሰው ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።