
ከ 7 ሰአት በፊት
የመካከለኛው ምሥራቅ ሁነኛ ባላንጣ ሆነው ላለፉት ሰባት ዓመታት ሲቆራቆሱ የቆዩት ኢራንና ሳኡዲ አረቢያ ግንኙነታቸውን በአዲስ መልክ ለመጀመር ተስማሙ።
ይህ ያልተጠበቀ ዜና የተሰማው የሁለቱ ወገን ባለሥልጣናት ለአራት ቀናት በዝግ ከመከሩ በኋላ ነው።
የሁለቱ አገሮች ባለሥልጣናት ምክክር የተደረገው በቻይና ሲሆን ሁለቱን ባላንጣዎች በማቀራረብ የቻይና መንግሥት ሁነኛ ሚና ተጫውቷል።
ሳኡዲ ከኢራን ጋር ለመጨረሻ ጊዜ ግንኙነቷን ያቋረጠችው በፈረንጆቹ ጥር ወር፣ 2016 ነበር።
ይህም በቴህራን የሚገኘው ኤምባሲዋ ላይ አደጋ መድረሱን ተከትሎ ነበር።
ኤምባሲዋ በተቃውሞ አደጋ የደረሰበት ደግሞ አንድ ዕውቅ የሺአ ኢስላም የሃይማኖት አባት በሪያድ በስቅላት መቀጣታቸው የቀሰቀሰው ቁጣ ነው።
ኢራንና ሳኡዲ ሁለቱም በአካባቢው ኃያል አገር ሆኖ ለመውጣት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።
ለዚህም እንዲረዳቸው በአካባቢያቸው አገራት የሚደረጉ ጦርነቶችን በጦር መሣሪያና በመረጃ ይደግፋሉ፤ በገረቤት አገር ፖለቲካዎች እጃቸውን ያስገባሉ።
- አንቶኒ ብሊንከን በመጪው ረቡዕ በአዲስ አበባ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው10 መጋቢት 2023
- የትግራይ ኃይሎች አባላት ስለደም አፋሳሹ ጦርነት እና ስለሰላም ስምምነቱ ምን ይላሉ?ከ 8 ሰአት በፊት
- እግር ኳስ ከ90 ወደ 60 ደቂቃ ያጥር ይሆን? ወይስ በተጨማሪ ደቂቃዎች ከፍ ይላል?ከ 8 ሰአት በፊት
በሌባኖስ፣ በሶሪያ፣ በኢራቅ፣ በተለይ ደግሞ ግልጽ በሆነ መንገድ በየመን ሁለቱ አገሮች ተዋጊ ኃይሎችን በመደገፍ ይገዳደራሉ።
በየመን ኢራን የሁቲ አማጺያንን ስትደግፍ ሳኡዲ በበኩሏ ከሥልጣን የተባረረውን የየመን አስተዳደር ትደግፋለች።
በዚህ የተነሳ ከፈረንጆቹ 2014 ጀምሮ ሳኡዲ በተለይ በየመን የአየር ጥቃት በመሰንዘር ከባድ ጥፋት አድርሳለች።
በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች በበኩላቸው በሳኡዲ የነዳጅ ማውጫ መሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ይሰነዝራሉ።
አሜሪካና ሳኡዲ በነዳጅ ማውጫ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ከጀርባ ሆና የምትመራው ኢራን ናት ብለው ይከሳሉ።
ኢራን በበኩሏ እጄ የለበትም ስትል ታስተባብላለች።
ሁለቱ አገሮች በቻይና ያደረጉትን ስምምነት ተከትሎ በሁለት ወራት ውስጥ በቴህራንና ሪያድ የተዘጉ ኤምባሲዎቻቸውን ለመክፈት ተስማምተዋል።
የንግድና የደኅንነት ጸጥታ ጉዳዮች ላይ አብረን እንሠራለን ብለዋል።
አሜሪካ ይህን ስምምነት በጥንቃቄ እንደምትመለከተው ገልጻለች።
የዋይት ሃውስ የብሔራዊ ደኅንነት ካውንስል ቃል አቀባይ ጆን ከርቢ “መንግሥታችን በአካባቢው ያለውን ውጥረት ሊቀንስ የሚችል ማንኛውንም ስምምነት ይደግፋል’ ካሉ በኋላ፣ ‘ይሁንና ኢራን ቃሏን ታከብራለች ብለን አናስብም፤ እስኪ የምናየው ይሆናል” ሲሉ በስምምነቱ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ አስተጋብተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ጉተሬዝ ቻይና በአስታራቂነት ለተጫወተችው ሚና አመስግነዋል።
ሁልጊዜም ኢራንን በአይነ ቁራኛ የምትከታተላት እስራኤል ለጊዜው በስምምነቱ ዙርያ ያለችው ነገር የለም።