March 11, 2023 – BBC Amharic 

በኳታሩ የዓለም ዋንጫ በርካታ ደቂቃዎች በባከነ ሰዓትነት ተጨምረዋል
የምስሉ መግለጫ,በኳታሩ የዓለም ዋንጫ በርካታ ደቂቃዎች በባከነ ሰዓትነት ተጨምረዋል

ከ 8 ሰአት በፊት

የኳታሩ የዓለም እግር ኳስ ውድድርን ሊዮኔል ሜሲ በስተመጨረሻ ታላቁን የእግር ኳስ ዋንጫ የሳመበት ሆኖ ተመዝግቧል።

ነገር ግን የዶሃው ውድድር ሌላ መነጋገሪያ የነበረው ጉዳይ አራተኛ ዳኞች ወደላይ የሚሰቅሉት የጨዋታው ጭማሪ እና ቀሪ ደቂቃዎች ማሳያ ሰሌዳ ነበር።

ከዚህ ጋር በተያያዘም የ2022 ዓለም ዋንጫ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በጣም ረዥም ጊዜ የወሰዱ ጨዋታዎች የታዩበት ሆኖ አልፏል።

የዓለም እግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪ ፊፋ አራተኛ ዳኞች እያንዷንድ የባከነች ሰከንድ እንዲቆጥሩ አዟል።

ይህ አዲሱ መመሪያ ምናልባትም በሚቀጥሉት የውድድር ዘመናት ወደ አገራት ሊጎች ወርዶ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል።

የጨዋታ ሕግጋትን የሚቆጣጠረው ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር ቦርድ ባለፈው ጥር ለንደን ውስጥ ስብሰባ አድርጎ ፍትሃዊ የግጥሚያ ሰዓት ይኑር ብሏል።

መመሪያው ይቀየር ወይስ ሕጉ የሚለው አሁንም አከራካሪ ጉዳይ ነው። የተጨማሪ ሰዓት ነገር እግር ኳስን ይቀይረው ይሆን?

60 ደቂቃ?

ምንም እንኳ እግር ኳስ የ90 ደቂቃ ጨዋታ ቢሆንም የጨዋታው ትክክለኛ ሰዓት ቢሰላ ከ90 ያነሰ ነው።

ተጨማሪ ደቂቃ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ ላይ የዋለው በፈረንጆቹ 1891 ነው። ዓላማው ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች የተበጣጥሶ የባከነውን የጨዋታ ሰዓት ማካካስ ነው።

በቀደመው ጊዜ ተጨማሪ ደቂቃ በአብዛኛው ተጨዋቾች ተጎድተው ለሚያባክኑት ሰዓት የሚሰጥ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የተጫዋች ቅየራም ታክሎበታል።

አልፎም የቪድዮ እገዛ ወደ እግር ኳስ ከመጣ በኋላ ዳኞች የቪድዮ ምልከታ ለማድረግ የሚወስዱት ጊዜ፣ ጎል ከገባ በኋላ ተጫዋቾች ደስታቸውን የሚገልጹበት፣ ተጨዋቾች ሆነ ብለው የሚያባክኑት ጊዜ በተጨማሪ ደቂቃ ውስጥ ይካተታሉ።

በዚህም ምክንያት ጨዋታው መቼ እንደሚገባደድ የሚያውቁት ዳኞች ብቻ ናቸው።

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የቀድሞው የኔዘርላንድስ እግር ኳሰኛ ማርኮ ቫን ባስተንን ጨምሮ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የቀድሞ ዳኛ ማርክ ክላተንበርግ እና የቀድሞው የአርሰናል አለቃ ዳቪድ ዲዬን እግር ኳስ 60 ደቂቃ ይሁን እያሉ ነው።

እኒህ ሰዎች የሚሉት እግር ኳስ አንድ ሰዓት ይሁንና ኳስ ከጨዋታ ውጪ በሆነች ቁጥር ሰዓት መቁጠር ይቁም ነው።

ምንም እንኳ አሁን ካለው 90 ደቂቃ ወደ 60 እንዲወርድ ማድረጉ የእግር ኳስ ጨዋታ ጊዜን የሚያሳጥረው ቢመስልም እውነታው ግን ይህ አይደለም።

ለምሳሌ በ2018 የሩሲያው ዓለም ዋንጫ ወቅት አማካይ የጨዋታ ጊዜ 58 ደቂቃ ነበር።

ምንም እንኳ ኳስ ከጨዋታ ውጪ በሆነች ቁጥር የሚቆም ሰዓት ወደ እግር ኳስ በቅርቡ ይመጣል ብሎ መገመት ቢከብድ የኳታሩ የዓለም ዋንጫ ግን አዲስ መላ አስተዋውቋል።

በዚህ የዓለም ዋንጫ በመጀመሪያው አጋማሽ እና በጨዋታው ፍፃሜ የሚጨመረው ደቂቃው ያለወትሮ ከፍ ያለ ነበር።

ጭማሪ ሰዓት

የኳታሩ የዓለም ዋንጫ ጭማሪ ሰዓት

ኳታር ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ በመጀመሪያው ዙር የምድብ ጨዋታ በአካማይ በየጨዋታው 11 ደቂቃ ከስምንት ሰከንድ ተጨምሯል።

በመጀመሪያው አጋማሽ 4 ደቂቃ፤ በሁለተኛው አጋማሽ መገባደጃ ደግሞ 7 ደቂቃ ታክሏል።

ነገር ግን ወድድር እየተጋመሰ ሲመጣ የሚጨመረው ደቂቃ መቀነስ ጀመረ።

ይህ መረጃ እንደሚያሳየው የኳታሩ ዓለም ዋንጫ ከዚህ በፊት ከነበሩት ሁሉ ልቆ በርካታ ተጨማሪ ደቂቃ የተሰጠበት ሆኗል።

በዚህ የዓለም ዋንጫ ብዙ ተጨማሪ ደቂቃ ያየው ጨዋታ እንግሊዝ ከኢራን ያደረጉት የጠራራ ፀሐይ ፍልሚያ ነው።

እንግሊዝ ከኢራን የነበራቸው ፍልሚያ 10 ደቂቃ ጭማሪ የተሰጠው ሲሆን፣ በተጨማሪው ደቂቃ ግጥሚያው 9 ጊዜ ተቋርጧል።

በጨዋታው መስተጨረሻ ዳኛው የቪድዮ እርዳታ ተመልክተው የፍፁም ቅጣት ምት ለመስጠት ከሦስት ደቂቃ በላይ ወስዶባቸዋል።

ኢራን ጎል ካስቆጠረች በኋላ ዳኛው የጨዋታ መገባደጃ ፊሽካ ነፍተዋል። ነገር ግን 56 ሰከንድ ይቀር ነበር።

ምንም እንኳ ጨዋታውን እንግሊዝ በበላይነት እየመራች የነበረ ቢሆንም ዳኛው የቀረውን ሰከንድ ማጫወት ነበረባቸው ወይ የሚለው አነጋጋሪ ሆኗል።

በተመሳሳይ ደቡብ ኮሪያ ከጋና የነበራቸው ጨዋታ 10 ተጨማሪ ደቂቃ ተሰጥቶት ኮሪያዎች አቻ የምታደርጋቸውን ጎል ፍለጋ ላይ ሳሉ እንግሊዛዊው ዳኛ ፊሽካቸውን አሰምተዋል።

በጭማሪው 10 ደቂቃ የተጨዋች ጉዳት እና ቅያሪ ነበር። ይህ 1 ደቂቃ ከ42 ሰከንድ ወስዷል። ዳኛው በስሌቱ መሠረት 11፡42 ነበር ፊሽካ መንፋት የነበረባቸው። ነገር ግን ጨዋታው የተገባደደው 10፡52 ነው።

በዚህ የተበሳጩት የደቡብ ኮሪያው አሠልጣኝ ፓውሎ ቤንቶ ከዳኞች ጋር እሰጥ-አገባ በመግባታቸው የቀይ ካርድ ሰለባ ሆነዋል።

ተጨማሪው 102 ሰከንድ የት ገባ?

ምንም እንኳ ብዙ የሚባል ጭማሪ ደቂቃ ቢሰጥም 50 በመቶው ብቻ ነው ጥቅም ላይ የሚውለው።

በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ባለፉት ዓመታት ኳስ ጨዋታ ላይ የሚውለው ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል። ታድያ ጭማሪ ሰዓት ከፍ ይበል መባሉ ውሃ ያነሳ ይሆን?