አማራ ሚዲያ ማዕከል / Amara Media Center

 · የአማራ ተማሪዎች ማህበር (አተማ) በድሬድዋና ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲዎች በአማራ ተማሪዎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በማውገዝ በአስቸኳይ ጥቃቱ እንዲቆም፣ የታሰሩትም እንዲፈቱ ጠይቋል።

አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ

መጋቢት 2 ቀን 2015 ዓ/ም

አዲስ አበባ ሸዋ

የአማራ ተማሪዎች ማህበር (አተማ) በድሬድዋና ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲዎች በአማራ ተማሪዎች ላይ እየደረሰ ነው ያለውን በደል በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።

ማህበሩ ሲቀጥል የአማራ ሕዝብ ለዘመናት በጠላቶቹ የተሴሩበት ሴራዎች እና የጥላቻ ትርክቶች ጊዜያትን እየጠበቁ ሲፈነዱና ሕዝቡን እንደ ሕዝብ ከየአቅጣጫው ለሠቆቃ እና ለጥፋት ሲዳርገው ማየት የተለመደ ነው ብሎታል።

በዚህም የአማራው ተማሪ እንደ አንድ የአማራ ሕዝብ የማህበረሰብ ክፍል ለዘመናት በጠላቶቹ ተዘርቶ፣ተኮትኩቶና አድጎ እዚህ የከፋ ደረጃ ላይ የደረሰው ፀረ-አማራ ትርክት ገፈት ቀማሽ ስለመሆኑ አውስቷል።

ከሰሞኑ በድሬድዋ እና ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ በሚገኙ የአማራ ተማሪዎች ላይ የሚደርሰው ብሔርን ትኩረት ያደረገ ድብደባ ፣እስር እና ማዋከብ የዚህ ፀረ-አማራ ትርክት ማሳያ ነው ያለው አተማ በሁለቱም ዩኒቨርስቲዎች የደረሰውን ጉዳት አሳይቷል።

በድሬድዋ ዩኒቨርስቲ በቀን 23 /06/15 ዓ.ም የጀመረው የአማራ ተማሪዎችን ላይ በፀጥታ አካላት የተደገፈ ድብደባ ፣ እስር እና ማዋከብ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሶ ከ 400 በላይ የአማራ ተማሪዎች ተደብድበው እንዲሁም የመታወቂያ ካርዳቸውን እና የመመገቢያ መለያቸውን ተቀምተው ከግቢ ውጭ እንዲወጡ ተደርገዋል ብሏል።

በተጨማሪም ከ 20 በላይ የአማራ ተማሪዎች ታስረው እንደሚገኙ የገለጸው አተማ ከታሰሩ ተማሪዎች መካከልም አብዛኞቹ የት እደታሰሩ የሚታወቅ ነገር የለም ሲል አክሏል። ሆኖም እነዚህ ከ 400 በላይ የሚሆኑ የአማራ ተማሪዎች በቤተ-ክርስቲያን እና መስጊድ ተጠግተው እንደሚገኙ እና በችግር ላይ እንዳሉ ለማወቅ መቻሉንም ጠቅሷል።

በተመሳሳይ በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ከ 15 ቀናት በላይን ያስቆጠረው ግጨት በመጀመሪያ ሃይማኖታዊ መነሻ ምክንያት ያለው መስሎ ግን ብዙም ሳይቆይ መልኩን እና ቅርፁን ቀይሮ የአማራ ተማሪዎች ላይ ባነጣጠረ መልኩ አሰቃቂ ድብደባ እና ማዋከብ እየተደረገ እንዳለና ይህም በአካባቢው ተወላጆች እና ነዋሪዎች የተደገፈ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል ብሏል።

በዚህም ምንም እንኳን ዩኒቨርስቲው የማጠቃለያ ፈተና እያስፈተነ ቢሆንም ተማሪዎች ፈተናውን እየጣሉ ወደቤታቸው እየተመለሱ ይገኛሉ ነው ያለው።በመጨረሻም የአማራ ተማሪዎች ማህበር (አተማ) በድሬድዋ እና በዋቻሞ ዩኒቨርስቲ በሚገኙ የአማራ ተማሪዎች ላይ የሚደርሰውን ድብደባ፣እስር እና ማዋከብ አስመልክቶ የሚከተሉት ተግባራት እንዲፈጸሙ ለሚመለከተው አካል ሁሉ አሳስቧል።

1ኛ) በድሬድዋ ዩኒቨርሲቲ በመማር ላይ እያሉ የታሰሩ የአማራ ተማሪዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እና ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ።

2ኛ) በቤተ-ክርስቲያን እና መስጊድ ተጠግተው የሚገኙ ከ400 በላይ የሚሆኑ የአማራ ተማሪዎች በአስቸኳይ ወደ ትምህርት ገበታቸው እዲመለሱ።

3ኛ) በዋቻሞ ዩኒቨርስቲ የአማራ ተማሪዎች ላይ እሚደረገው ድብደባ እና ማዋከብ እንዲቆም እና ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ እንዲሁም በዚህ ምክንያት ፈተና ያለፋቸው ተማሪዎች እንዲፈተኑ እንጠይቃለን።

የሚመለከተው አካል ሁሉ በአስቸኳይ ተረባርቦ ለተነሱ ጥያቄዎች መፍትሔ የማይሰጣቸው ከሆነ ማህበራችን የአማራ ተማሪዎች ማህበር (አተማ) ጉዳዩን ከክልል ትምህርት ቢሮ አንስቶ እስከ ፌደራል ትምህርት ሚንስቴር ድረስ ይዞ እንደሚቀርብ ልናሳስብ እንወዳለን ሲል አሳስቧል።

በተጨማሪም ወደ ሚመለከተው የፍትሕ ተቋም በተዋረድ ጉዳዩን ይዘን የምንቀርብ ይሆናል ብሏል።

ሆኖም ይህ ሳይሳካ ቀርቶ የአማራ ተማሪዎች ላይ የሚደርሰው በደል እና ግፍ ካላቆመ እና ተባብሶ ከቀጠለ በቀጣይ በምናደርገው ሁለንተናዊ ትግል ለሚፈጠረው ችግር ሃላፊነቱን የሚወስዱት የድሬድዋ እና የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም መንግሥት መሆናቸውን ለማሳወቅ እንወዳለን ብሏል አተማ በመግለጫው።