March 13, 2023 – BBC Amharic 

ለሁለት ዓመታት ያህል በጦርነት ውስጥ በቆየችው ትግራይ ካሉት የመገናኛ ብዙኃን መካከል አንዱ በሆነው የድምፀ ወያኔ ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ውስጥ የሚሠሩ በርካታ ጋዜጠኞች ሥራቸውን የለቀቁ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ለመልቀቅ ደብዳቤ ማስገባታቸው ተነግሯል።

ጋዜጠኞቹ ሥራቸውን ለመልቀቅ እንደ ምክንያት ያቀረቡት “ሙያዊ ነጻነት ማጣት” የሚል ሲሆን፣ ጣቢያው የአንድ ፖለቲካ አቋም ማንፀባረቂያ መሆኑንም በማንሳት ይከሳሉ።

የመገናኛ ብዙኃን ተቋሙ ከትጥቅ ትግል አንስቶ በክልሉ እንዲሁም በመላው አገሪቱ ዋነኛ የፖለቲካ ኃይል በመሆን ለበርካታ አስርት ዓመታት በቆየው በህወሓት ስር የሚመራ መሆኑ ይታወቃል።

ጣቢያው ባለፈው ሳምንት በፌስቡክ ገፁ ላይ ባሰፈረው መልዕክት ላይ ግን ጋዜጠኞቹ በሥነ ምግባር ጉድለት የተባረሩ እና በደመወዝ ጥያቄ የለቀቁ መሆናቸውን ገልጿል።

ለ40 ዓመታት ያህል በስርጭት ላይ የሚገኘው ድምፀ ወያኔ ሠራተኞቹ ጥለውት እየሄዱ ያሉት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑን ቢቢሲ ትግርኛ ያነጋገራቸው የተቋሙ ሠራተኞች ይናገራሉ።

እነዚህ ጋዜጠኞች ድርጅቱን በሙያዊ ነጻነት ማሳጣት፣ በተቋማዊ አሰራር ብልሹነት የሚከሱ ሲሆን፣ ድርጅቱ በበኩሉ “የተሻለ የሕይወት አማራጭ ፈልገው” የለቀቁ ናቸው በማለት ክሳቸውን ያጣጥላል።

በመገናኛ ብዙኃን ድርጅቱ ውስጥ ከሚሰሩ ምንጮቹ ማጣራት እንደተቻለው በአሁኑ ወቅት በፈቃዳቸው ሥራቸውን ለመልቀቅ ደብዳቤ ያስገቡ በርካታ ጋዜጠኞች ናቸው።

ሐፍቶም ኃይሌ በድምፀ ወያኔ ተቀጥሮ መሥራት የጀመረው ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ነው። በዚህ ዓመት ጥር ወር መገባደጃ ላይ ግን ከድርጅቱ ለመልቀቅ ደብዳቤ አስገብቷል።

የሥራ መልቀቂያውን ባስገባበት ወቅት ግን እርሱም ሆነ ሌሎች ባልደረቦቹ ላይ የቀረበባቸው የሥነ ምግባር ጉድለት ክስ እንደሌለ ተናግሯል።

ሐፍቶም ድምፀ ወያኔ በትግራይ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ማብቃቱን ተከትሎ የተለያዩ ሃሳቦችን ለማስተናገድ የማይፈልግ እየሆነ መምጣቱን በማንሳት ድርጅቱ ላይ ያለውን ቅሬታ ይገልጻል።

አክሎም “የጋዜጠኞች ሥራ በፖለቲካ አቋም የሚገመገም መሆኑ እና ነጻነትን የሚገድብ አስተዳደር ያለው ድርጅት ነው” ሲል ይወቅሳል።

በተጨማሪም በተለይ የህወሓት አመራሮች በፕሪቶሪያ ከፌደራል መንግሥት ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ፥ በጦርነቱ ምክንያት ተፈጽመዋል የሚባሉ ክሶች የፌዴራል ኃይሎችን የሚነኩ ከሆኑ እንዳይስተናገዱ እንደሚደረግ ያስረዳል።

ሐፍቶም በሚሠራበት ተቋም ሊያስተላልፋቸው ያልቻላቸውን ዘገባዎች ወደ ግል ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ አውጥቶ በመጻፉ በእርሱ እና በአለቆቹ መካከል አለመግባበት መነሳቱንም አልካደም።

ባለፈው ሳምንት ድምፀ ወያኔ ሠራተኞቹ ሊኖራቸው የሚገባ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ መመርያ አውጥቷል።

የሚታገዱ ፕሮግራሞች

ላለፉት አምስት ዓመታት በድምፀ ወያኔ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት ሲሰራ የቆየው እና በ2014 ዓ.ም ኅዳር ወር ላይ ድርጅቱን ለቆ የወጣው ረዳት አዘጋጅ ካሕሳይ መሰለ እንደሚለው፣ ለሥርጭት የተዘጋጁ ፕሮግራሞች የህወሓት አመራሮችን እንዳያስቆጡ በሚል ሳይተላለፉ እንደሚቀሩ ይናገራል።

ከዚያ በኋላም ለሚያቀርባቸው የተለያዩ ጥያቄዎች አወንታዊ ምላሽ ባለማግኘቱ ለመልቀቁ ምክንያት እንደሆነው ይናገራል።

ጋዜጠኛ መሐሪም በጦርነቱ ወቅት ‘ረመጥ’ በሚል ርዕስ የሠራው ዶክመንተሪ ፊልም የመጀመሪያ ክፍል ከተላለፈ በኋላ ቀጣዩ አየር ላይ እንዳይውል እንደተደረገ ይጠቅሳል።

ህወሓት ሰኔ 2013 ዓ.ም የመቀለ ከተማን ከተቆጣጠረ በኋላ ሚዲያዎችን በብቸኝነት በመያዝ በባለሙያዎች ላይ “ትልቅ አፈና” እየፈፀመ መቆየቱን ጋዜጠኞቹ ይናገራሉ።

“ድርጅቱ ሃሳብን የሚያፍን፣ . . . በሙያዊ ብቃት የማይመራ ስለሆነ እና በራሴም ላይ ጭቆና እና አፈና ስለነበረ አስቀድሜ ለቀቅኩ። ድርጅቱም በኤዲቶሪያል ፖሊሲ ሳይሆን በግለሰቦች ፍላጎት ስለሚመራ ወደ አላስፈላጊ ባርነት የሚገቡ አሉ” ሲል ካህሳይ ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግሯል።

እነዚህን ክስተቶችን ተከትሎ ባለሙያዎቹ የሥነ ልቦና ነፃነት አይሰማቸውም የሚለው ጋዜጠኛው፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት ያልተከፈላቸው ወርሃዊ ደሞዝ እንደ መያዣ ተደርጎ ለማስፈራራት እንደሚጠቀሙበት ይናገራል።

የድምፀ ወያኔ ምላሽ

ድምፀ ወያኔ ትግራይ በአሁኑ ወቅት የአጭር ሞገድ እና የኤፍኤም ስርጭቶችን ጨምሮ በትግርኛ፣ በአማርኛ እና በሌሎች ቋንቋዎች የሚተላለፍ የሳተላይት ቴሌቪዥን ስርጭት ያለው ድርጅት ነው።

የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ለሆኑት አቶ አባዲ ገብረሥላሴ ጋዜጠኞቹ ሚያቀርቡትን ክስ እና ቅሬታን በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡን በተደጋጋሚ በእጅ ስልካቸው ላይ ብንደውልም ለጊዜው ልናገኛቸው አልቻልንም።

ጣቢያው ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ጉዳዩን አስመልክቶ በፌስቡክ ገፁ ላይ ባጋራው መግለጫ ግን፣ በኤዲቶሪያል እንደሚመራ በመግለጽ ከዚህ ውጪ “ነጻነት አጣሁ፣ ታፈንኩኝ የሚል በማንኛውም የድርጅታችን መድረክ ላይ አልገጠመንም” በማለት ክሱን አስተባብሏል።

በጉዳዩ ላይ ሀሳባቸውን እየገለጹ ላሉት አካሎችም ባለፉት ሁለት ዓመታት ይሁን ድርጅቱ ዳግም ሥራ ከቀጠለ በኋላ “ለአንድም ቀን እንኳ ሥራ ያልሰሩ ናቸው፤ በድምፀ ወያኔ ደመወዝ እየተከፈለ ስላልሆነ፣ ደመወዝ ፈልገው ነው ሥራ የቀየሩት” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

በተጨማሪም ጦርነት እየተካሄደ በነበረባቸው ወቅቶች “በዲሲፕሊን የተባረሩም አሉ” ብሏል።

የሙያ ነጻነት ጥያቄ

የካቲት 28/2015 ዓ.ም. ለድርጅቱ የሥራ መልቀቂያ ያስገባው የአማርኛ ቋንቋ ክፍል አስተባባሪ እና የኤዲቶሪያል ኮሚቴ አባል ጋዜጠኛ አንገሶም አብረሃ፣ እስካሁን የለቀቁት ጋዜጠኞች በአመራር ጉድለት አይደለም የሚለው አባባል “ክህደት ነው” ይላል።

“እኔ እስከማውቀው ድረስ፥ በድርጅታችን ውስጥ ማብራሪያ የሚሻ ጥያቄ ካለ፣ የኤዲቶሪያል ኮሚቴው ነው አቋም ወስዶ ማብራሪያ ወይም መግለጫ የሚሰጠው። ነገር ግን ይህ ሁኔታ በድርጅቱ ውስጥ ያለውን ግለሰባዊ አካሄድ አመላካች ሊሆን ይችላል” ብሏል።

“የወጣው መግለጫ አብዛኛዎቹን የለቀቁ ሠራተኞች አይገልጽም” የሚለው አንገሶም፣ እሱ ራሱ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ባለው ተጽዕኖ የተነሳ ሥራቸውን ከለቀቁት ሠራተኞች መካከል አንዱ መሆኑንም ተናግሯል።

አንገሶም እንደሚለው በጋዜጠኞቹ የሚነሱት ዋነኛ ጥያቄዎች በክልሉ ውስጥ ያሉ አስተሳሰቦች በኤዲቶሪያል ፖሊሲ መሠረት እንዲስተናገዱ፣ ነፃነታቸው እንዲጠበቅ እና የአንድ ቡድን የበላይነት እንዲቀር የሚል ነው።

ጋዜጠኛ መሐሪ ሰለሞን በበኩሉ በአሁኑ ወቅት ጋዜጠኞቹ የወሰዱት እርምጃ በመገናኛ ብዙኃን ውስጥ ያለውን መሠረታዊ ችግር የሚፈታ ባይሆን እንኳ፣ ይህ እንዲለወጥ ለሚፈለግ ሁሉ የማንቂያ ደወል ነው ይላል።