March 13, 2023 – Mereja.com 

ማሳሰቢያ፣የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማኅበር በሰሜን አሜሪካ ስፕሪንግፊልድ ቨርጂኒያ ውስጥ በየዓመቱ የሚያደርገውን የአድዋ ድል በዓል አክብሯል። በበዓሉም ላይ የታደሙ ወገኖች የሚከተለውን የአቋም መግለጫ በአንድ ድምፅ አውጥተዋል።

የአቋም መግለጫ

የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማኅበር በሰሜን አሜሪካ (ኢ.ው.ቅ.ማ.ሰ.አ.) ጥር 2003 ዓ.ም. ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የቀደሙ አባቶቻችንና እናቶቻችን ያወረሱንን ታሪክ፣ ትውፊትና ቅርስ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍና ተተኪው ትውልድ በአገራችን ባሕልና ወግ እንዲታነጽ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷና አንድነቷ የተጠበቀ አንዲሁም ዜጎቿ በሰላም የሚኖሩባት አገር እንድትሆን የኢ.ው.ቅ.ማ.ሰ.አ. ጽኑ ምኞት አለው።

ድርጅታችን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ጉዳይ ላይ እንደሚሰራ ተቋም የህዝብን ሰላምና ደህንነት የሚመለከቱ ጉዳዮችን ይከታተላል። በዚህም መሠረት ላለፉት አምስት ዓመታት በበርካታ የአገሪቷ ክፍሎች ውስጥ እየደረሰ ያለው ማንነትንና ሐይማኖትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በእጅጉ አሳዝነውናል አስቆጥተውናልም። የተሳሳተ የፖለቲካ አስተሳሰብ የወለደው የጭካኔ ድርጊት የዜጎች ፍጅትን፣ ንብረት ውድመትን፣ ዘረፋን፣ የአብያተ ክርስትያናትን መቃጠል በማስከተሉ በእጅ አስቆጭቶናል። ክርስቲያንና ሙስሊም ተከባብሮና ተፋቅሮ በሚኖርባት አገር ውስጥ በማናቸውም ቤተ እምነት ላይ የሚደርስ ጥቃት እጅግ ከባድ ወንጀል በመሆኑ በዝምታ መታለፍ እንደሌለበት እናምናለን።

የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማህበር በሰሜን አሜሪካ እንደ አንደ ተቆርቋሪና ጉዳዩ እንደሚመለከተው ተቋም በቤተ እምነቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ሐይማኖታዊ ጥቃቶች ብቻ ሳይሆኑ የአገርን ቅርስና ታሪክም የሚጎዱ መሆናቸውን ይገነዘባል።ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ቃጠሎ፣ ውድመትና ዘረፋ ደርሶባቸዋል። በርካታ ካህናት፣ ዲያቆናትና ምዕመናን ተገድለዋል። ቤተክርስቲያን ጥንታዊ መጽሐፍትን፣ አልባሳትን፣ ንዋየ ቅዳሳትንና ሌሎችም አያሌ ቅርሶችን ለበርካታ ዘመናት ጠብቃ በማቆየት ከትውልድ ወደ ትውልድ ስታስተላልፍ ቆይታለች። በመሆኑም አንድ ቤተክርስቲያን ተቃጠለ ማለት በርካታ ምትክና አምሳያ የሌላቸው ቅርሶችም አብረው ወደሙ ማለት ነው።

የአድዋ ድልን በተዛባ ሁኔታ እንዲታይ፣ የታሪኩ ባለቤቶች የሆኑትን ዳግማዊ አጼ ሚኒሊክና እቴጌ ጣይቱን አንግበውት የዘመቱትን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የመሰረዝና የጦርነቱን እውነትኛ ታሪክ አወላግዶ ጥላቻ ለመዝራት የሚደረገው ድርጊት እጅግ ያሳዝናል። የአድዋ ድል በዓልን ህዝብ ለዘመናት ሲያከብርብት በመኖረው መንገድ እንዳያከብር በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተለያዩ ዕንቅፋቶችና መሰናክሎችን ከመጋረጡም በላይ በዓሉን ሊያከብሩ አደባባይ የወጡ ዜጎችን መግደልና አካል ማጉደል እየተከሰተ ነው።

በ127ኛው የአድዋ ድል በዓል አከባበር  ላይ ህዝብ በተለምዶ ሲያከብርበት ከኖረበት ዳግማዊ አጼ ሚንሊክ አደባባይ እንዳያከብር ከመከልከሉም በላይ መናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ለንግስ በዓል የታደሙት ምዕመን ላይ ጥይት ተተኩሶ አንድ ምዕመን በአልሞ ተኳሽ ወታደር ተመቶ ከመገደሉም በላይ በሽዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን ላይ የአስለቃሽ ጭስ ተለቆባቸው ለከፍተኛ ህመምና ለአካል ጉዳት ተዳርገው በስቃይ ላይ ይገኛሉ።

 የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስና ማኅበር በሰሜን አሜሪካ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመንግሥት ያቀርባል።

1) የአደባባይ የሐይማኖት በዓላትን በተለይም መስቀል፣ጥምቀት ከተራ እንዲሁም በየዓመቱ የሚከበሩ የተለያዩ የንግስ በዓላት እንዳይከበሩ መንግሥት የሚያደርገውን ማደናቀፍና ጣልቃ ገብነት በአስቸኳይ እንዲያቆም እንጠይቃለን።

2) በቅርቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ለመክፈልና ምዕመኑን በብሔረሰብና በቋንቋ ለመለያየት መንግስት ሕገ ወጥ ጣልቃ ገብነትና በደል መፈጸሙይታወቃል።የደረሰውን በደል በመቃወም ቅዱስ ሲኖዶስ ባዘዘው መሠረት ጥቁር በመልበሳቸው ምክንያት ድብደባ፣እስራት፣መንገላታትና ከሥራ መባረር የደረሰባቸው ወገኖቻችን በርካታ ቁጥር ያላቸው ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ የአድዋ ድል ክብረ በዓልን ለማክበር የዳግማዊ አጼ ምኒሊክንና የእቴጌ ጣይቱን እንዲሁም የአጼ ቴዎድሮስን ምስል የሚያሳዩ ልብሶች እንዳይለበሱ ስለመከልከሉና በለበሱም ላይ ለደረሰው ድብደባ፣ እስራትና ወከባ፣ በዓሉን የሚገልጹ አልባሳትን ለገበያ በማቅረብ የሚተዳደሩ ወገኖቻችን መደብሮቻቸው እንዲታሸጉና በነሱም ላይ የደረሰውን እንግልት፣ድብደባና እስራት አስመልክቶ መንግሥስት ይፋዊ ይቅርታ እንዲጠይቅ እናሳስባለን። ይህንን ህገ ወጥና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትቶች የፈጸሙ የጸጥታ ሰራተኞች በኃላፊነት እንዲጠየቁና ለወደፊቱ መንግሥት እንደዚህ ዓይነት ወንጀል ከመፈጸም እንዲቆጠብ እንጠይቃለን።

3) ከላይ ከተጠቀሰው አሳዛኝ በደል በተጨማሪ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ታሪካዊውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በያዙና በለበሱ ዜጎች ላይ በተደጋጋሚ እየደረሱ ያሉት ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲያቆሙና ህዝቡ በፈለገውና ባመነበት መንገድ በዓላትን የማክበር መብቱን መንግሥት እንዲያከብር እንጠይቃለን።

4) በተደራጀ መንጋና በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ድጋፍ የፈረሱ ኃውልቶች ለመጥቀስም ያህል በሐረር ከተማ ለአድዋው ጀግና ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል ቆሞላቸው የነበረው ሐውልት መልሶ እቀደመ ቦታው እንዲተከል እንጠይቃለን።

5) ታሪካዊ መኖሪያ ቤቶችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ መናኸሪያዎችን፣ የንግድ መደብሮችን የማፍረስና መልካቸውን የመቀየር እርኩስ ተግባር በእስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን።

የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማኅበር በሰሜን አሜሪካ

ስፕሪንግፊልድ፣ ቨርጂኒያ

መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. (March 12, 2023)