March 14, 2023 

በአዲስ አበባ 18 ተማሪዎች ያለ አግባብ ከትምህርት ታግደናል አሉ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ዕድገት ጮራ ኹለተኛ ደረጃ ት/ት ቤት 18 ተማሪዎች ከሕግ አግባብ ውጪ ከትምህርት ማገዱን ተገለጸ፡፡

ተማሪዎቹ ከትምህርታቸው ለመታገዳቸው ትምህርት ቤቱ የሰጠው ምክንያት፣ አዲስ አበባ ላይ የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ መሰቀልና የክልሉ መዝሙር መዘመር ጋር በተገናኘ ተፈጥሮ በነበረው አለመግባባት ነው ተብሏል፡፡

ከትምህርታቸው የታገዱ ተማሪ ወላጆች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ተማሪዎቹ በወቅቱ ተከሰቶ በነበረው አለመግባበት ታስረው ከነበሩ 250 ተማሪዎች መካከል የነበሩ ሲሆን፣ ከእስር ተፈተው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ሳሉ ትምህርት ቤቱ የዲስፕሊን ጥሰት ፈጽመዋል በሚል ምክንያት ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ ከትምህርት አግዷቸዋል ተብሏል፡፡

ተማሪዎቹ ከትምህርት መታገዳቸውን ተከትሎ፣ ወላጆቻቸው ከትምህርት የታገዱበትን ውሳኔ በመቃወም ለተለያዩ አካላት ጥያቄ ቢያቀርቡም ችግሩን የሚፈታ አካል አልተገኘም ብለዋል፡፡

ተማሪዎቹ ለተባረሩበት ውሳኔ ኃላፊነት የሚወስድ አካል አለመኖሩን የተናሩት ወላጆች፣ ለከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ጥያቄ አቅርበው “ለውሳኔው ኃላፊነት የሚወስድ አካል መኖሩን የሚያረጋግጥ ፊርማ ስለሌለ፣ ችግሩን አንመለከተውም።” የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

አዲስ ማለዳ ከትምህርት የታገዱ 18 ተማሪዎች ሥም ዝርዝር የሰፈረበት የትምህርት ቤቱን የውሳኔ ደብዳቤ የተመለከተች ሲሆን፣ በደብዳቤው ላይ ውሳኔውን ያሳለፈው የት/ት ቤቱ አመራር ነው ቢባልም በሥምም ይሁን በፊርማ የተረጋገጠ የወሳኙን ማንነት የሚገልጽ መረጃ የለውም፡፡

በውሳኔው ላይ የተማሪዎች ዲስፕሊን ኮሚቴ የተሳተፉ መሆኑ በደብዳቤው ላይ ቢገለጽም፣ የተማሪዎች ወላጆች ተማሪዎቹ በጉዳዩ ላይ ለዲስፕሊን ኮሚቴ አለመቅረባቸውን ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ተማሪዎቹ ላይ የተወሰነው ውሳኔ አንድ ዓመት ከትምህርት መታገድና በሚቀጥለው ዓመት መሸኛ ወስደው ከትምህርት ቤቱን እንዲለቁ ወይም በትምህርት ቤቱ መማር እንዳይችሉ ነው፡፡ የተማሪ ወላጆች በውሳኔው ላይ ያላቸው ቅሬታ ይዘው ከክፍለ ከተማ እስከ ትምህር ቢሮ፣ ከትምህርት ቢሮ እስከ ትምህርት ሚኒስቴር ጉዳዩን ቢያስረዱም ጉዳዩን መርምሮ መፍትሔ የሰጠን አካል እስካሁን አላገኘንም ብለዋል፡፡

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ከትምህርት ቤቱ ምላሽ ለማግኘት ጥረት ብታደርግም አልተሳካላትም፡፡ ትምህርት ቤቱ በጉዳዩ ላይ ሚዲያዎች ቢጠይቁትም ምላሽ እንደማይሰጥ ሲገልጽ እንደነበር የተማሪዎቸ ወላጆች ጠቁመዋል፡፡

ምንጭ  አዲስ ማለዳ