March 14, 2023 – BBC Amharic 

ኢዋኦ ሃካማዳ ከእህታቸው ሂዴኮ ጋር
የምስሉ መግለጫ,ኢዋኦ ሃካማዳ ከእህታቸው ሂዴኮ ጋር

ከ 5 ሰአት በፊት

ሞት ተፈርዶባቸው ለግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በእስር ላይ የቆዩት ጃፓናዊ ቅጣት የተበየነባቸው ጉዳይ ዳግም በፍርድ ቤት እንዲታይ ተፈቀደላቸው።

አሁን የ87 ዓመት አዛውንት የሆኑት ኢዋኦ ሃካማዳ በ1966 (እአአ) አለቃቸውን፣ የአለቃቸውን ሚስት እና ሁለት ልጆቻቸውን በመግደል ተከሰው ነበር ሞት የተፈረደባቸው።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለው ከሃምሳ ዓመታት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት ኢዋኦ፣ በዓለም ላይ ሞት ተፈርዶባቸው ለረጅም ጊዜ በእስር ላይ የቆዩ ግለሰብ ናቸው።

የቀድሞው ቦክሰኛ ግድያውን ከፈጸሙ በኋላ ለ20 ቀናት በተደረገባቸው ምርመራ ወቅት ተፈጽሞብኛል ባሉት ድብደባ ወንጀሉን መፈጸማቸውን እንዳመኑ በመግለጽ ለፍርድ ቤት ተናግረው ነበር።

በፍርድ ሂደቱ ወቅት ዳኞች ተጨማሪ የዲኤንኤ ማስረጃ ጠይቀው ከገዳይ ጋር ተመሳሳይ መሆናቸው የተገለጸ ቢሆንም፣ ጠበቆች ግን ማስረጃው የተፈበረከ ነው በማለት ተከራክረው ነበር።

ኢዋኦ ሃካማዳ ቀጣሪያቸውን እና ቤተሰባቸውን ቶኪዮ ውስጥ በስለት በመውጋት በመግደል እና በመዝረፍ ወንጀል ተከሰው ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ነበር ሞት የተፈረደባቸው።

ተከሳሹን ጥፋተኛ የሚያስብል ማስረጃዎች በመርማሪዎች የተዘጋጁ ሊሆኑ ይችላሉ በማለት በ2014 (እአአ) ከእስር ተለቀው ጉዳያቸው እንደገና በፍርድ ቤት እንዲታይ ተወስኖ ነበር። ነገር ግን ውሳኔው በቶኪዮ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጓል።

ነገር ግን ለይግባኝ ሰሚ ችሎት አቤቱታ ከቀረበ በኋላ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፍተኛው ፍርድ ቤት ጉዳዩን መልሶ እንዲመለከተው ካዘዘ በኋላ የቀደመው ውሳኔ መልሶ እንዲታይ ተወስኗል።

ውሳኔውን ተከትሎ “ይህችን ቀን ለማየት ለ57 ዓመታት ስጠብቅ ነበር፤ አሁን ደረሰች” በማለት ደስታቸውን የገለጹት የወንድማቸው ጉዳይ በድጋሚ እንዲታይ ዘመቻ ሲያካሂዱ የነበሩት የ90 ዓመቷ ሂዴኮ ናቸው።

“በመጨረሻም ትከሻዬ ላይ ወድቆ የነበረው ሸክም ተነስቶልኛል” በማለት ውሳኔው እፎይታን እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

የእስረኛው ቤተሰቦች እንደሚሉት ወንድማቸው ከ50 ዓመታት በላይ በእስር ቤት በመቆየታቸው የአእምሮ ጤናቸው አሽቆልቁሏል።

በዓለም ላይ ካሉ ዋነኛ የሰለጠኑ እና ዴሞክራት ከሆኑ አገራት መካከል ከአሜሪካ ቀጥላ ጃፓን ወንጀለኞችን በሞት የምትቀጣ አገር ናት።

ይህ የኢዋኦ የሞት ፍርድ ከ50 ዓመታት በኋላ መልሶ እንዲታይ መወሰኑን አምነስቲ በአዎንታዊነት እንደሚያው ገልጾ “ተገቢውን ፍትሕ ለመስጠት በጣም የዘገየ አጋጣሚ ነው” ብሎታል።

“በግለሰቡ ላይ የሞት ፍርድ የተሰጠው በኃይል በማሳመን ሲሆን፣ ጥፋተኝነቱን ለማረጋገጥም የቀረቡት ማስረጃዎች በከፍተኛ ሁኔታ አጠራጣሪዎች ነበሩ” ሲሉ በጃፓን የአምነስቲ ኢንትርናሽናል ዳይሬክተር ሂዴኪ ናካጋዋ።

የፍርድ ውሳኔው ከእንደገና እንዲታይ ልዩ ይግባኝ ከተጠየቀ ሂደቱ ዓመታትን ሊወስድ ስለሚችል፣ ጠበቆች ይህ አይነቱ ሂደት እንዲቀር ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።

የኢዋኦ ብይን ከእንደገና እንዲታይ መወሰኑ የጃፓን ጠበቆችን ያስደሰተ ሲሆን፣ “የፍርድ ሂደቱም በጠቅላይ ፍርድ ቤት ልዩ የይግባኝ ጥያቄ ሳይቀርብበት በፍጥነት እንዲጀመር” ዐቃቤ ሕጎችን ጠይቀዋል።

“ለአስርታት በእስር ቤት ቆይተው አካላዊ እና አእምሯዊ ጉዳት ለደረሰባቸው እስረኛ ጉዳይ በፍጥነት መፍትሄ ሊሰጣቸው ይገባል” በማለት የጃፓን የጠበቆች ማኅበር ኃላፊ ሞቶጂ ኮባያሺ የፍርድ ሂደቱ መዘግየት እንደሌለበት ተናግረዋል።