March 15, 2023 – Getachew Shiferaw
ትህነግ ከሽብርተኝነት መዝገብ መነሳት የለበትም!

ብሊንከን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የትህነግንና የፌደራል “መንግስት” አመራሮች አግኝቶ እንደሚያወያይ ይጠበቃል። አጀንዳ ይሆናሉ ከተባሉት መካከል አንደኛው የትህነግ ከሽብርተኝነት መዝገብ መነሳት ነው። ነገር ግን ይህ ጉዳይ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል።
1) አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የፀጥታ ተቋማትን መረጃ ተጠቅሞ በሚመስል በተደራጀ መልኩ ባጋራው መረጃ እንዳስረዳው 7000 ያህል የትህነግ ነፍሰ ገዳይ አሸባሪዎች ወደ መሃል ኢትዮጵያ ስምሪት ተሰጥቷቸዋል። ይህ ትህነግ የሽብር ተግባሩን ካለፈውም በባሰ ሊሰራ እንደሆነ ማሳያ ነው። የአቶ አንዳርጋቸው መረጃ የግለሰብ አስተያየት እንዳልሆነ ይታወቃል።
2) ትህነግ በተለያዩ ግንባሮች ስልጠና እየሰጠ፣ ወደ ኤርትራ፣ አማራና አፋር ክልሎች ኃይል እያስጠጋ ነው። በሱዳን በኩልም በተመሳሳይ። ስለሆነው ትህነግ በሽብር የተፈረጀበትን ተግባሩን እንደገና ሊጀምር እንጅ አልተወም።
3) የሰላም ስምምነቱ በሚያዘው መልኩ ትህነግ /ህወሓት ትጥቅ አልፈታም። በስምምነቱ መሰረት ትጥቅ ሲፈታና ሌሎች ግዴታዎቹን ሲወጣ ነው ከሽብር መዝገብ ይነሳል የተባለው። በሰላም ስምምነቱ መሰረት እንኳን ከሽብር መዝገብ እንዲፋቅ ቅድመ ሁኔታዎቹ አልተሟሉም።
4) የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በትህነግ የተያዙ ቦታዎችን ተረክቦ እያስተዳደረ አይደለም። ትህነግ ትጥቅ ባላወረደበት፣ እንደባለፈው በተለያዩ አካባቢ ያለውን ሰራዊት መምታትን ጨምሮ፣ የሽብር ዝግጅትና እንቅስቃሴ የማድረግ እድሉ ሰፊ ነው። እያደረገም ነው።
5) ትህነግ ለፈፀመው ወንጀል ተጠያቂነት አልሰፈነም። የሽግግር ፍትሕ የሚባለው ገና አልተሄደበትም። ለፈፀማቸው ዘግናኝ ወንጀሎች ሳይጠየቅ ከሽብር መዝገብ ሊነሳ አይችልም። ይህ በንፁሃን ቁስል ላይ መቀለድ ነው። ለቀጣይ የኢትዮጵያ ሰላምም መልካም ተሞክሮ አይሆንም።
6) ይህ ሁሉ በሆነበት ትህነግ ከሽብር መዝገብ ተነስቶ ሌላ ወ*ረ*ራ እና ወንጀል ቢፈፅም የሰላም ስምምነት፣ ሰላም ወዘተ የሚባለው ላይ ጥቁር ጥላ ያጠላል። ታማኝነት የሚባል ነገር እንዳይኖር ያደርገል።
7) ትህነግ አሁንም በቀልን እየሰበከ ያለ ቡድን ነው። እድሉን አግኝቶ፣ ከሽብር መዝገብ ተነስቶ እንደገና በደል እንዲፈፅም፣ ዘር እንዲያጠፋ መፍቀድ አይገባም።
8/ በትግራይ ህዝብ ላይም እየፈፀመ ያለው ተመሳሳይ ነው። በፓትሮል እየዘረፈ እንደሆነ መንግስት በመግለጫው አሳውቋል። እርዳታውን ለታጣቂ ማሰልጠኛ እየተጠቀመ ይገኛል። ለባንኮች የተላከውን 5 ቢሊዮን ብር በሳምንት አውጥቶ አስቀምጧል። ተቀናቃኞቹን እየገደለ ነው። ባለው የስልጣን ሽኩቻ የባሱ ጉዳዮች ሊከተሉ ይችላሉ። ሴቶች እየተደፈሩ፣ በርካታ በደሎችን እየፈፀመ ነው። ያለፈው ሳይበቃ አሁንም ከሽብር መዝገብ ስሙ ከተነሳ በደል እንዳይፈፀም አያስተምረውም። የከፋ ነው የሚሆነው!
ሌሎች በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። በእነዚህ ከበቂ በላይ ምክንያቶች ትህነግ ስሙ ከሽብር ወንጀል ለመነሳት ብቁ አይደለም። ምንም አይነት መስፈርት አያሟላም። ቅድመ ሁኔታ፣ ግዴታምን አልተወጣም። በተቃራኒው ለሽብር እየተዘጋጀ ነው። ይህ ቡድን የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በመፈታተን ካለው የቅርብ ጊዜ ታሪክና ፍላጎት አንፃር በፍፁም ከሽብር መዝገብ መነሳት እንደሌለበት መታወቅ አለበት።