March 15, 2023 – DW Amharic 

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፣ ከዛሬ መጋቢት አምስት እስከ መጋቢት ስምንት ቀን 2015 ድረስ  ወደ ኢትዮጵያና ኒጀር እንደሚያቀኑ መስሪያ ቤታቸው  ያወጣው መግለጫ ያመለክታል።

አንቶኒ ብሊንከን፣  በአዲስ አበባ በሚያደርጉት ጉብኝት በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭትን ለማስቆም የተደረሰው የሰላም ስምምነት አተገባበር እና የሽግግር ፍትህ ጉዳይ ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

የኢትዮጵያንና የአሜሪካን ፖለቲካዊ ጉዳዮች በቅርበት የሚከታተሉት፣ልጅ ነቢያት አክሊሉ እንደሚሉት፣ብሊንከን በዚህ ጉብኝታቸው፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረሰዉ ስምምነት መሬት ላይ ወርዶ በትክክል ተፈጻሚ የመሆን ያለመሆኑን ጉዳይ እንደሚገመግሙ ይጠበቃል።