March 15, 2023 – BBC Amharic 

ሰሌዳው ላይ የተጻፈውን የሂሳብ ስሌት የምትመለከት ተማሪ
የምስሉ መግለጫ,በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና በተሳካ ሁኔታ ተማሪዎችን በማዘጋጀት ሁሉንም ተማሪዎቻቸውን ወደ ቀጣይ የትምህርት ደረጃ ያሳለፉ ሰባት ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው

ከ 5 ሰአት በፊት

ጆርጂያ ቴክ በኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ ስማቸው ከሚጠራ የአሜሪካ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል ቀዳሚው ነው።

በአጠቃላይ በኢንጂነሪንግ ትምህርት ደግሞ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ወደዚህ ዩኒቨርስቲ ገብተው የመማር ዕድል ካገኙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች መካከል መርሲሞይ መርጋ አንዱ ነው።

መርሲሞይ ወደዚህ ተቋም ለመግባት ከ50,601 ተማሪዎች ጋር ለፈተና መቀመጡን ያስታውሳል።

መርሲሞይ ወደ አሜሪካ ለትምህርት ከማቅናቱ በፊት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በኦሮሚያ ልማት ማኅበር ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ነው።

የአዳማው ኦልማ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት እንደ መርሲሞይ ያሉ በትምህርታቸው የላቁ ተማሪዎችን ከመላው ኦሮሚያ እየመለመለ በማስተማር ስሙን ተክሏል።

በ2014 ዓ.ም. የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናን በማስፈተን ተማሪዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካስገቡ ትምህርት ቤቶች መካከልም አንዱ ነው።

በእርግጥ በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘዉ ስቴም ኢኖቬሽን ማዕከል፣ የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት፣ የወላይታ ሊቃ የአዳሪ ትምህርት ቤቶችም እንዲሁ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤትም ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች በሙሉ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሳልፈዋል።

ለመሆኑ የእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውጤታማነት ከምን የመነጨ ነው? ቢቢሲ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ከቻሉ አዳሪ ትምህርት ቤቶች መካከል ሦስቱን ቃኝቷል።

መርሲሞይ መርጋ
የምስሉ መግለጫ,ጆርጂያ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ እያጠና የሚገኘው መርሲሞይ

መምህራንንም ጎበዝ የሚያደርጉ ተማሪዎች

የትምህርት ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት የኦሮሚያ ልማት ማኅበር አዳማ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት፣ የወላይታ ሊቃ እንዲሁም ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች በሙሉ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግባት የሚያስችላቸውን ውጤት አግኝተዋል።

የአዳማ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በ2006 ዓ. ም ነው የመጀመሪያዎቹን ተማሪዎች ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው።

በየዓመቱ 200 ተማሪዎችን የመቀበል አቅም ያለው ይህ ትምህርት ቤት፣ ተማሪዎቹ ከመላው ኦሮሚያ ከመንግሥትም ሆነ ከግል ትምህርት ቤቶች ተወዳድረው እንደሚገቡ የኦሮሚያ ልማት ማኅበር ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ደጀኔ ኢቲቻ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ልጆቹ ወደዚህ አዳሪ ትምህርት ቤት ለመግባት በስምንተኛ ክፍል ያስመዘገቡት ውጤት፣ እንዲሁም ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍል ያላቸው የክፍል ውጤት ይታያል።

ይህ ግን በቂ አይደለም፤ ትምህርት ቤቱ ያዘጋጀውን የመግቢያ ፈተና መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።

ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ማስፈተን የጀመረው እና በደቡብ ክልል የሚገኘው የወላይታ ሊቃ አዳሪ ትምህርት ቤትም ተመሳሳይ መስፈርትን ተከትሎ ነው ተማሪዎችን የሚመለምለው።

ወላይታ ሊቃ ተማሪዎች በትምህርታቸው አቅም እያላቸዉ ነገር ግን በቤተሰቦቻቸው የኢኮኖሚ ሁኔታ የተነሳ ጥራት ያለው ትምህርት ማግኘት ያልቻሉ ተማሪዎችን በወላይታ ልማት ማኅበር አማካኝነት ሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖ እንደሚማሩ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ማቱሳላ ቦና ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በእርግጥ ይላሉ አቶ ማቱሳላ በወጪ መጋራት የሚማሩ የተወሰኑ ተማሪዎች በግቢያቸው ውስጥ ይገኛሉ።

የወላይታ ሊቃ አዳሪ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር እንደሚሉት ከሆነ ልጆቻቸውን በዚህ ትምህርት ቤት ለማስተማር የሚፈልጉ ወላጆች ካሉ፣ ከየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ቢመጡ የመግቢያ ፈተናውን በመስጠት ይቀበላሉ።

የካቲት 4/2011 ዓ.ም. ሥራ የጀመረው የደሴ አዳሪ ትምህርት ቤት ደግሞ 100 ተማሪዎችን ብቻ ተቀብሎ የማስተማር አቅም ያለው ነው።

የትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ፍቅር በላይ ከአማራ ክልል በስምንተኛ ክፍል ፈተና አማካኝ ውጤታቸው 85 እና ከዚያ በላይ የሆኑትን በመመዝገብ በሳይንስ ትምህርቶች፣ በእንግሊዝኛ እና አማርኛን ጨምሮ ፈተና በመስጠት እንደሚቀበሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት
የምስሉ መግለጫ,የካቲት 4 2011 ዓ.ም ስራ የጀመረው የደሴ አዳሪ ትምህርት ቤት 100 ተማሪዎችን ብቻ ተቀብሎ የማስተማር አቅም አለው

ለሌሎች ተምሳሌት የሚሆኑ ተማሪዎች

የኦሮሚያ ልማት ማኅበርም ሆነ የወላይታ ሊቃ አዳሪ ትምህርት ቤቶች እስካሁን ያስፈተኗቸው ተማሪዎች በሙሉ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋም አብቅተዋል።

የእነርሱ ተማሪዎች በሚገቡበት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሁሉ በከፍተኛ ውጤት እንደሚመረቁ የሚናገሩት አቶ ደጀኔ፣ በአሁኑ ወቅት በሥራው ዓለም ላይ የተሰማሩ መኖራቸውንም ይጠቅሳሉ።

ይህንኑ የአቶ ደጀኔን ሀሳብ የሚያጠናክረው ሦስት መጻሕፍትን የጻፈው እና በልማት ማኅበሩ ውስጥ ተቀጥሮ እየሰራ የሚገኘው ገለታ ፀጋ ነው።

በምዕራብ ሸዋ ዞን ሚዳ ቀኝ ቀበሌ ተወልዶ ያደገው ገለታ ወደ ኦሮሚያ የልማት ማኅበር ልዩ አዳሪ ትምህርት የገባው በ2006 ዓ.ም ነው።

ጉቴ ቡሌ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለተማረው ገለታ፣ የኦልማ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተወዳድሮ መግባት “አሜሪካ ስኮላርሺፕ እንደማግኘት ነው” በማለት በሕይወቱ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት እንዳስቻለው ይናገራል።

ከአንዲት አነስተኛ የገጠር መንደር ወጥቶ ወደ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ሲገባ “አመለካከቴ ነው የተቀየረው” የሚለው ገለታ፣ “ማንበብም፣ ከቴክኖሎጂ ከላብራቶሪም ጋር መገናኘት የቻልኩት በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ነው” ይላል።

ገለታ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ሲወስድም ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት ሀሮማያ ዩኒቨርስቲ ገብቶ የሕብረተሰብ ጤና አጥንቷል።

ዩኒቨርስቲው በመምህርነት እንዲቀጥል አድርጎት የነበረ ቢሆንም እርሱ ግን የልማት ማኅበሩ ያቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ አብሯቸው እየሠራ ይገኛል።

የወላይታ ሊቃ አዳሪ ትምህርት ቤትም ቢሆን በ2014 ዓ.ም. በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተመርቀው አገራቸውን እያገለገሉ የሚገኙ ልጆችን አፍርቷል።

እነዚህ ትምህርት ቤቶች በየዓመቱ ተማሪዎቻቸው ከሚያስመዘግቡት የላቀ ውጤት በተጨማሪ አንድም ተማሪ በታሪክ ወድቆባቸው አያውቅም።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥናት እና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር በላይ ሐጎስ (ዶ/ር) እነዚህ ትምህርት ቤቶች፣ ክልሎች ካሏቸው ምርጥ ተማሪዎች መካከል “ክሬሙን” በማወዳደር መውሰዳቸው ለውጤታማነት እንደረዳቸው ይናገራሉ።

አክለውም የሚያፈሯቸው ተማሪዎች ለሌሎች ተማሪዎች “ብቃት ምንድን ነው?” የሚለውን በማሳየት ረገድ ተምሳሌት እንደሚሆኑ ገልፀዋል።

እነዚህ ተማሪዎች የተሰባሰቡት በፈተና ተለይተው በመሆኑ “አስተማሪ የማያውቀውን ጭምር አውቀው መገስገስ የሚችሉ” ናቸው ይላሉ።

ለኦሮሚያ ልማት ማኅበር ዳይሬክተሩ አቶ ደጀኔ ግን ለውጤታማነታቸው ምክንያቱ ይዘው የተነሱት ዓላማ ነው።

አቶ ደጀኔ ማኅበራቸው ሲመሠረት መንግሥት የሚሰራቸውን ሥራዎች ደግሞ የመሥራት ዓላማ አልነበረውም።

እነርሱ የአዳሪ ትምህርት ቤት በከፈቱበት ወቅት መንግሥት በከፍተኛ ሁኔታ ትምህርት ቤቶችን ለማዳረስ ይሰራ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ደጀኔ፣ ነገር ግን እነዚህ ትምህርት ቤቶች ብቁ ዜጎችን ለማፍራት በሚያስችል ቁመና ላይ አልነበሩም ይላሉ።

የሚሰጡት የትምህርት ጥራት ጥያቄ ውስጥ ወድቆ ስለነበር ከአገር ውስጥ አልፎ በዓለም አቀፍ መድረኮች ተወዳዳሪ የሚሆኑ ዜጎችን ለማፍራት ዓላማ አድርገው ትምህርት ቤቶቹን ለመክፈት በቅተዋል።

“የእኛ ልጆች ተወዳዳሪነታቸው ከአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረክ ጭምር ነው” ከዚህ ባሻገር ከሚማሩት የሳይንስ እውቀት ባሻገር የማኅበረሰቡን ባሕል፣ እሴት እና ወግ ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ የሚያከብሩ እና የሚጠብቁ ልጆችን ለማፍራት አንደሚሰሩ ይናገራሉ።

ትምህርት ቤታቸው፣ ችሎታው ተሰጥኦው እያላቸው ዕድሉን ላላገኙ ተማሪዎች መድረኮችን በማመቻቸት ውጤታማ እንዲሆኑ የማድረግ ዓላማ ይዞ መነሳቱንም ያክላሉ።

አቶ ማቱሳላ በበኩላቸው እንደሚሉት መስከረም ወር ዓመቱ የትምህረት ካላንደር ሲጀመር የተማሪ ወላጆች እና ትምህርት ቤቱ ውል ይፈራረማሉ።

ይህ ውል ለውጤታማነታቸው ካገዙ አሰራሮች መካከል አንዱ ነው።

ይህ ውል ተማሪው ውጤቱ ከቀነሰ እና የዓመቱ መጨረሻ ላይ አማካይ ውጤቱ ከ75 በታች ከሆነ እንደሚሰናበት የሚገልጽ ነው።

ዓመቱን በሙሉ ግን ተማሪው ላይ የድጋፍ፣ የክትትል እና የእገዛ ሥራዎች እንደሚሰሩ አቶ ማቱሳላ ያነሳሉ።

መመህራኖቻቸው ዓመቱን በሙሉ የተማሪዎቹን ውጤት በመከታተል ድጋፍ አንደሚያደርጉ የጠቀሱት አቶ ማቱሳላ፣ ተማሪዎችም የሚኖራቸውን ጥያቄ ያለምንም ችግር ማቅረብ የሚችሉበት የመማር ማስተማር ሥርዓት መዘርጋታቸውን ይናገራሉ።

በዚህ ረገድ የኦሮሚያ ልማት ማኅበር ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት አሰራር ከወላይታ አቻው ጋር ተመሳሳይ ነው።

በኦልማ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ በትምህርት ቤቱ ውስጥ በሚኖረው ቆይታ ወቅት ከ79.09 በታች ካመጣ ይሰናበታል።

ይህ እንዳይሆን ግን ተማሪዎቹን የሚያማክሩ መምህራኖች ተመድበዋል።

የትኛውንም ጥያቄ በማንኛውም ሰዓት መምህራኖቹ በቅርብ ሆነው ለተማሪዎቻቸው ይመልሳሉ። ያስረዳሉ፣ ያፍታታሉ።

የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር በበኩላቸው ተማሪዎች በትምህርት ቤት ቆይታቸው 85 እና ከዚያ በላይ አማካኝ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ይጠበቃል። ከዚያ በታች የሚያመጡ ተማሪዎች ሲኖሩ ግን ክትትል እና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ የመምህራን ቅጥር ላይም ጠንከር ያለ ሥርዓት ይከተላል።

ትምህርት ቤቱ የሚቀጥራቸው መምህራን በሙሉ ሁለተኛ ዲግሪ እንዲኖራቸው እንደሚጠበቅ የሚናገሩት ምክትል ርዕሰ መምህሩ፣ በሁለተኛ ዲግሪያቸው 3.5 እና ከዚያ በላይ በመጀመሪያ ዲግሪያቸው ደግሞ 3.00 ያስመዘገቡ መሆን ይኖርባቸዋል።

ከዚያ በኋላም በወሎ ዩኒቨርስቲ የመግቢያ ፈተና ተፈትነው ያለፉት መቀጠራቸውን ገልፀዋል።

የኦሮሞ ልማት ማሕበር አዳሪ (አዳማ) ትምህርት ቤት መግብያ በር
የምስሉ መግለጫ,የኦልማ አዳማ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በ2006 ዓ. ም ነው የመጀመሪያዎቹን ተማሪዎች ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው

የተሞክሮ ማዕከል

ራጂ አሸናፊ በ2014 ዓ.ም ከአዳማ ሳይንስ ኮሌጅ ሲመረቅ በፊዚክስ እና ሒሳብ የትምህርት መስኮች በአንድ ጊዜ ሁለት ዲግሪውን ማግኘት ብቻ ሳይሆን ስድሳ ትምህርቶችን ኤ+ አምጥቶ ነው ያጠናቀቀው።

ራጂ የአሜሪካው አምአይቲ ዩኒቨርስቲ በቀጥታ ሦስተኛ ዲግሪውን እንዲሰራ የሚያስችለውን ነጻ የትምህርት ዕድል ሰጥቶታል።

እንዲህ ዓይነት ውጤታማ ተማሪዎችን የሚያፈሩት አዳሪ ትምህርት ቤቶች ለሌሎች አርዓያ የሆኑ ይመስላል።

ኦሮሚያ ክልል ሰባት ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የእነርሱን ተሞክሮ በመውሰድ ገንብቷል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) 50 ደረጃቸውን የጠበቁ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ለመገንባት አቅደው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን በአንድ ወቅት ተናግረዋል።

አቶ ደጀኔ በኦሮሚያ ውስጥ ላሉ በሺህ ዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ይህ ትምህርት ቤት የተሞክሮ ማዕከል አንዲሆን ዓላማቸው መሆኑን ይናገራሉ።

የተሞክሮ ማዕከል ከመሆን ባሻገር በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች መካከል የውድድር እና ፉክክር መንፈስ የመፍጠር ዓላማ አላቸው።

ይህም ትምህርት ቤቶቹ በውጤታቸው የላቁ ተማሪዎችን ለማፍራት እንዲተጉ እንደሚያደርግ እግረ መንገድም የትምህርት ጥራትን ለመጠበቅ እንደሚያግዝም ያስረዳሉ።

አንድን ትምህርት ቤት ጥሩ ትምህርት ቤት የሚያሰኘው ተማሪው ነው ይላሉ በላይ ሐጎስ (ዶ/ር)።

ተማሪው ውጤታማ ከሆነ ትምህርት ቤቱ ውጤታማ ይባላል የሚሉት ምሁሩ፣ ይህ ትምህርት ቤት ደግሞ ለሌሎች አርዓያ መሆን ብቻ ሳይሆን ሠርቶ ማሳያ ሆኖ ማገልገል አለበት ሲሉ ይመክራሉ።

ተማሪዎቹ ከሌሎች አጎራባች ትምህርት ቤቶች ካሉ ተማሪዎች ጋር ቢገናኙ፣ እነርሱ ለሌሎች የሚያካፍሉት እውቀት የመኖሩን ያህል የሚማሩት ነገርም እንደሚኖር ያነሳሉ።

ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸው ተወዳድረው ወደ አዳሪው ትምህርት ቤት እንዲገቡላቸው በሚያደርጉት ፉክክር ውስጥ የትምህርት ጥራትን ለማረጋጋጥ እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል።

አቶ ደጀኔ ትምህርት ቤታቸው ለተለያዩ ክልሎች ተሞክሮውን አንደሚያካፍል በማንሳት በኦሮሚያ የተወሰኑ ወረዳዎች የእነርሱን ልምድ በመያዝ ጎበዝ ተማሪዎችን የሚያግዙባቸውን ክፍሎች ማቋቋማቸውን ጠቅሰዋል።

እነዚህ ወረዳዎች የተወሰኑ ሰባተኛ እና ስምንተኛ ከፍል ያሉ ተማሪዎችን ሌሎቹ ደግሞ ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ በትምህርታቸው የላቁ ተማሪዎችን የሚያግዙበት፣ ነገር ግን አዳሪ ያልሆኑ ትምህርት ቤቶችን የማቋቋም ሥራ ጀምረዋል።

አቶ ደጀኔ በተለያዩ አካባቢዎች የአዳሪ ትምህርት ቤቶች መከፈታቸው መልካም መሆኑን በማንሳት “የተከፈተው ነገርንም እንዴት መርተው ለውጤት አበቁ” የሚለውን የእነርሱን ልምድ በሚገባ መውሰድ ተገቢ መሆኑን ይመክራሉ።

በአሁኑ ሰዓት እነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚከተሉት አዳሪ ትምህርት ቤት አንደኛው ሞዴል መሆኑን የሚያነሱት በላይ (ዶ/ር)፣ ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ሳይርቁ፣ ከትምህርት ቤታቸው ሳይነጠሉ ተለይተው ተጨማሪ ድጋፍ የሚያገኙበት እና እነርሱም ሌላውን የሚረዱበት፣ ከሌላው ጋር ተባብረው የተሻለ ውጤት የሚያመጡበት ሞዴል መኖሩን ያስረዳሉ።

እነዚህን ክፍሎች ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ በማደራጀት፣ የሚፈጥኑ ተማሪዎች ሳያዘገዩ እንደ ፍጥነታቸው ልክ እያገዙ ማስተማር ይቻላል ሲሉ ይናገራሉ።

ለእነዚህ ተማሪዎች ግን የተለየ የትምህርት ዕቅድ፣ መምህራን፣ ሥልጠና እንዲሁም መመሪያ መዘጋጀት እንዳለበት በመግለጽ፣ ይህንንም መሞከር ለትምህርት ጥራቱ አስተዋጽኦ ያደርgኣል ይላሉ።

ኮምፒውተር እየተጠቀመ የሚገኝ ተማሪ
የምስሉ መግለጫ,አዳሪ ትምህርት ቤቶቹ የተለያዩ ግብዓቶችን ለተማሪዎቻቸው በማሟላት ውጤታቸው ያማረ እንዲሆን እገዛ ያደርጉላቸዋል

መሠረተ ልማቶች ምን ያህል የተሟሉ ናቸው?

ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥናት እና ምርምር ተቋም ዳይሬክተሩ በላይ ሐጎስ (ዶ/ር) በትምህርት ውጤታማ ለመሆን ወሳኝ እና አጋዥ የሆኑ ጉዳዮች አሉ።

ምሁሩ ወሳኝ ነው ብለው የጠቀሷቸው የተማሪውን ፍላጎት፣ ጥረት እና ትጋትን ነው።

አክለውም “የመማሪያ ቁሳቁስ ባልተሟላበት እና የመምህራን እጥረት በሚታይበት ተማሪ ውጤታማ መሆን ይቸገራል” ብለዋል።

ይህንን የተማሪውን እውቀት የመፈለግ ትጋት እና ጥረት የሚያግዙት ጥሩ መምህራን እና የመማሪያ ቁሳቁሶች መሟላት፣ ምቹ የሆነ የመማሪያ አካባቢ መኖር ናቸው ሲሉም በቅደም ተከተል ያስቀምጧቸዋል።

የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ከጀመረ ወዲህ በርካታ ተግዳሮቶች አንደገጠሙት የትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ፍቅር በላይ ይናገራሉ።

ቀዳሚው ተግዳሮት የነበረው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንደነበር ያስታወሱት መምህሩ፣ በዚህም የተነሳ ለግማሽ ዓመት የመማር ማስተማር ሥራው ተቋርጦ ቆይቷል።

ከዚያ በኋላም የሚገኝበት አካባቢ የጦርነት ቀጠና የነበረ በመሆኑ በርካታ ንብረቶቹን ወድመውበታል።

ከጦርነቱ በፊት ትምህርት ቤቱ ሦስት የሳይንስ ቤተ ሙከራዎች፣ ሦስት የአይሲቲ (ኮምፒውተር) ማዕከሎች እንዲሁም ቤተ መጻሕፍቱ በወሎ ዩኒቨርስቲ መደራጀቱን ያስታውሳሉ።

አሁን ግን የትምህርት ቤቱ ቤተሙከራዎች እና ቤተመጻሕፍቶች ተዘርፈው ባዷቸውን መቅረታቸውን የሚናገሩት መምህሩ፣ በአሁኑ ወቅት ተዘርፈው የተመለሱ ኮምፒውተሮች ተጠግነው አንድ የአይሲቲ ላይብረሪ መኖሩን፣ የሳይንስ ቤተሙከራውም የግብዓት እጥረት አጋጥሟቸዋል።

“ከመደበኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተለየ መሠረተ ልማት የለንም” የሚሉት መምህሩ የስፖርት ማዘውተሪያዎቸም የሏቸውም።

ልጆቹን ውጤታማ ያደረጋቸው የመምህራን ጥረት እና ትጋት እንዲሁም የተማሪዎቹ ብርታት መሆኑን ይናገራሉ።

የኦሮሚያ ልማት ማኅበር ያቋቋመው ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ለተማሪዎቹ ብቻ ሳይሆን ለመምህራኖቹም ማደሪያ እንዳለው ዳይሬክተሩ አቶ ደጀኔ ይናገራሉ።

አቶ ደጀኔ በመሠረተ ልማት ደረጃ እጅግ በሚያረካ ሁኔታ የተሟሉ አለመሆናቸውን ጠቅሰው “ከሌላው ግን የተሻልን ነን” ይላሉ።

አባላቶቻቸው ባደርጉላቸው ድጋፍ የሳይንስ ቤተ ሙከራዎች፣ ቤተ መጻህፍቶቻቸው እንዲሁም የአይቲ ክፍሎቻቸው በቁሳቁስ ደረጃ መደራጀታቸውን ይናገራሉ።

የወላይታ ሊቃ ርዕሰ መምህሩ አቶ ማቱሳላ በበኩላቸው “ምቹ የመማር ማስተማር ከባቢን ከመፍጠር አኳያ የሚቀሩን ብዙ ነገሮች አሉ” በማለት ትምህርት ቤቱ ካለበት የፋይናንስ ውስንነት የተነሳ የሚጎድላቸው በርካታ ነገሮች መኖራቸወን ያነሳሉ።

ከቤተሙከራዎች እና ቤተ መጻህፍት አንጻር የሚጠበቅበትን አለመሟላቱን በማንሳት፣ ዋነኛ ትኩረታችን ባለን ውስን ሀብት እንዴት ብቁ ዜጎችን ማፍራት እንችላለን የሚለው በመሆኑ የልጆቹ ውጤታማነት ላይ ብቻ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው ይላሉ።

የአዳማ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎቹ ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች የትምህርት ዕድል አግኝተው ሲሄዱ እንዳይቸገሩ በማሰብ የተለያዩ የውጪ ቋንቋዎችን ይማራሉ።

መርሲሞይ “ቻይንኛም፣ አማርኛም የተማርኩት በአዳሪ ትምህረት ቤቱ ውስጥ ነው” ይላል።

ተማሪዎቹ ከመማሪያ ቋንቋዎች ባሻገር አንድ ቋንቋ ጨምረው መማር ግዴታቸው ሲሆን፣ ከዚህ ውጪ ግን ያሉትን ቋንቋዎችን መርጠው ይማራሉ።

በትምህርት ቤቱ ቻይንኛ፣ አረብኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዘኛ እና ኮርያኛ እንደሚሰጥ የሚናገሩት አቶ ደጀኔ “ሰባት ቋንቋዎችን የሚናር ተማሪ አለን” ይላሉ።

የጆርጂያ ቴክ ኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ ተማሪው መርሲሞይም ሆነ ገለታ ፀጋ እነርሱ የተማሩበት የመማር ማስተማር ሂደት ለበርካታ የቀለም ቀንዶች ተዳርሶ ማየት ሕልማቸው ነው።