March 15, 2023 – BBC Amharic 

ፖሊሶች ከአንዲት ተማሪ ጋር

ከ 5 ሰአት በፊት

በደቡብ ክልል በሀላባ ቁሊቶ ከተማ በሚገኘው የሀለባ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪዋ ሊዲያ አበራ የካቲት 22/2015 ዓ.ም. ከትምህርት ቤቷ ተወስዳ ከታሰረች በኋላ ጉዳዩ የማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆኗል።

ሊዲያ ከታሰራች በኋላ ለአምስት ቀናት ፍርድ ቤት ሳትቀርብ መቆየቷን እና በእስር ቤት ውስጥም የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባት አባቷ አቶ አበራ ሻሞሮ እንዲሁም ጠበቃዋ አቶ አበባየሁ ጌታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሕግ እና ፖሊስ ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ወ/ሮ ታሪኳ ጌታቸው የ14 ዓመቷ ተማሪን ጉዳይ ኮሚሽኑ እየተከታተለ እንደሆነ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የሊዲያ እስር ምክንያት ምንድን ነው?

በሀላባ ቁሊቶ ከተማ 30 ዓመታት የኖሩት አቶ አበራ ሻሞሮ፣ ሁለት ሴት ልጆች የሃላባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ እና 11ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው።

ሊዲያ የካቲት 22/2015 ዓ.ም. በመደበኛ ትምህርቷ ላይ ተገኝታ ነበር።

በዚያን ዕለት ሊዲያ በምትማርበት ክፍል ውስጥ አንዲት ተማሪ መውደቋ የነገሮች ሁሉ መነሻ እንደሆነ ነው ሰሜ አይጠቀስ ያሉ የሀላባ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ለቢቢሲ የገለጹት።

“ተማሪዋ የወደቀችው ሊዲያ መተት አሰርታባት ነው” በሚል በተፈጠረ “ግርግር” የትምህርት ቤቱ ሥራ በጊዜያዊነት መስተጓጎሉን ነው መምህሩ የሚገልጹት።

መምህሩ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ፖሊሶች ወደ ትምህርት ቤቱ እንደመጡ አስረድተዋል።

“ያለምንም መጥሪያ. . . ፖሊሶች መጥተው ከነዩኒፎርሟ፣ ከነደብተሯ እያለቀሰች” ከትምህርት ቤት እንደወሰዷት የተናገሩት መምህሩ፣ ነገሩ “በጣም አሳሳቢ እና የሚያሳዝን ነው” ብለዋል።

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ወንድሙ መርጋም በዚያን ዕለት ሌላ ተማሪ መውደቋ ለሊዲያ እስር ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሆኖም ታዳጊዋ ላይ ቀደም ብሎ ተማሪዎች እና ወላጆቻቸው አቤቱታ ያቀርቡባት ነበር ብለዋል።

“ከእሷ ጋር አብረን ምግብ በልተናል የሚሉ” ስምንት ተማሪዎች ወላጆች ቅሬታ ማቅረባችውን እና “ትምህርት ቤቱ እርምጃ ይውሰድ” የሚል ጫና እየበረታ መምጣቱን ያስረዳሉ።

በዚህም ሳቢያ ትምህርት ቤቱ የቅሬታ አቅራቢ ተማሪዎች ወላጆች ጉዳዩን ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲወስዱ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

ርዕሰ መምህሩ በትምህርት ቤት ውስጥ “ከእሷ [ሊዲያ] ጋራ ግንኙነት ነበረን፣ ምግብ በልተናል ያሉ ስምንት ተማሪዎች መውደቃቸውን” ገልጸው “ይሄ ነገር ከእሷ ጋር ግንኙነት አለው? ወይስ የለውም? የሚለውን ለማጣራት ነው ክስ ተመስርቶ በዚያው እየታየ ያለው” ብለዋል።

በዕለቱ ተማሪዎች ስለተረበሹ እና “እርምጃ መውሰድ አለብን. . . ለፖሊስ ልጅቷን በአፋጣኝ ይዛችሁ ብትሄዱ የተሻለ ይሆናል ያልነው” ሲሉም አክለዋል።

ርዕሰ መምህሩም ይሁን ስሜ አይጠቀስ ያሉት መምህር ሊዲያ እና በዚያው ትምህርት ቤት የምትማረው እህቷ በትምህርታቸው እጅግ ስኬታማ እንደሆኑ ገልጸዋል።

ሆኖም ይህ በሊዲያ ላይ የቀረበው “ቅሬታ” በእህቷ ላይ አልተሰማም።

ታዳጊዋ ላይ የቀረበው ክስ

የሊዲያ ጠበቃ አቶ አበባየሁ ጌታ፣ ሊዲያ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰደች በኋላ ከሕግ ውጪ ለአምስት ቀናት ፍርድ ቤት ሳትቀርብ ታስራ መቆየቷን ገልጸዋል።

ከአምስት ቀናት በኋላ ሃላባ መጀመሪያ ፍርድ ቤት ካለ ጠበቃ ጋር ቀርባ የ14 ቀናት ቀጥሮ ለምርመራ ከተሰጠ በኋላ ወደ ሃላባ ቁሊቶ ማረሚያ ቤት መወሰዷን ጠቅሰዋል።

ሆኖም ጠበቃዋ “ይህ ድርጊት ከሕግ ጋር የሚጻረር ነው” ይላሉ። ለአካለ መጠን ያልደረሰ ሰው በወንጀል ሲጠረጠር ከቤተሰቦቹ ጋር ቆይቶ ለምርመራ ሲፈልግ እንደሚጠራ በሕግ መደንገጉን ጠቅሰዋል።

“በተጠረጠረችበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆና ብትገኝ እንኳን የማረሚያ ቤት እስር እንደማይፈረድባት የወንጀል ሕጉ ያስቀምጣል” ብለዋል ጠበቃዋ።

በተሰጠው የጊዜ ቀጠሮ ላይ ለሃላባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ተጠይቋል።

ይግባኙም የታዳጊዋ አያያዝ እንዲሁም ለቀናት በእስር ላይ እንድትቆይ መደረጉ ተገቢ አይደለም የሚል ነው።

የሊዲያ ከሳሾች ጉዳት ደርሶብናል ያሉት ተማሪዎች ወላጆች ሲሆኑ “ልጆቻችንን ላይ ባደረገችባቸው መተት/ድግምት አፍዝዛ ጉዳት አድርሳባቸዋለች” የሚል ማመልከቻ አቅርበው እንደተከሰሰች አስረድተዋል።

ክሱ ተሰራ በተባለው “መተት/ድግምት” ተጎድተው ሕክምና ላይ የሚገኙ ተማሪዎች አሉ እንደሚልም አክለዋል።

በሌላ በኩል ታዳጊዋን ጠበቆቿ ባለፈው አርብ አግኝተው እንዳናገሯት የሚጠቅሱት አቶ አበባው “ንቅሳት ካለብሽ እናይሻለን በሚል እርቃኗን እንደፈተሿት ተናግራለች” ይህም የሕግ ጥሰት ነው ብለዋል።

ጠበቃው ሊዲያ እስሩ በተፈጸመባቸው የመጀመሪያዎቹ ቀናት ታለቅስ እንደነበረ ገልጸው አሁን መምህራን፣ የትምህርት ቤት ጓደኞቿ እና ሌሎች ሰዎች እየጠየቋት በመሆኑ “በጥሩ ሞራል ላይ ትገኛለች” ሲሉ ገልጸዋል።

አቶ አበባየሁ በኢትዮጵያ ሕግ ‘ድግምት’፣ ‘ጥንቆላ’፣ ‘እኔ አውቅልሃለሁ ባይነት’፣ ‘መንፈስ መጥራት’ እና መሰል ወንጀሎች የሚዳኙበት ድንጋጌ መኖሩን ይናገራሉ።

ሆኖም እነዚህ ወንጀሎች ጥቅምን ለማግኘት በማሰብ እና የሌላን ሰው ገንዘብ ለማግኘት የሚፈጸም እንጂ “የግል ጥቅም ምን እንደሆነ በማታውቅ ታዳጊ ልጅ፣ ገንዘብ ያለበትን እጠቁማቸኋለሁ ባላለችበት ሁኔታ. . . [ሕጉ] ይህንን ሁኔታ ሊቀበለው አይችለም” ብለዋል።

ሰዎችን ለማፍዘዝ የተለያዩ ዱቄት መሰል ምርቶችን ማምረት፣ መሸጥ እና ማሰተላለፍ ወንጀል መሆኑን ጠቅሰው ታዳጊዋ ይህንን ሁሉ አላደረገችም ብለዋል።

ጠበቃዋ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ለታዳጊዋ ሕይወት የሚያሰጉ ዛቻዎች እና ማስፈራሪያዎች እየተዘዋወሩ እንደሆነም አስረድተው፣ በደረሰባት የሥነ ልቦና ጫና ምክንያት “ከሥነ ልቦና ጫና ተላቃ ትምህርቷን ትቀጥላለች ማለት ይከብዳል” ሲሉ ገልጸዋል።

ይህንን ጉዳይ የሚከታተለው የጠበቆች ቡድን “ውጤት ባያመጣም” ጉዳዩን ለክልል ፍትህ ቢሮ፣ በሴቶች መብት ዙሪያ ለሚሰሩ እና ለሌሎች ተቋማት አሳውቋል።

የሊዲያ አባት አቶ አበራ የልጃቸው እስር “የተወረወረ ዱብ ዕዳ” ነው ይላሉ።

ልጆቻቸው በትምህርታቸው ከአጠቃላይ ተማሪ ተሸላሚ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ አበራ “እያጠኑ የሚያድሩ” ናቸው ይላሉ።

የልጆቻቸውን የተቀረውን የትምህርት ጊዜ በሌላ አካባቢ እንዲጨርሱ እየሞከሩም መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ሊዲያን በማረሚያ ቤት ባነጋገሩበት ወቅት “መቼ ነው ከዚህ የምወጣው?” ብላ እንደጠየቀቻቸውም አባት ተናግረዋል።

ጉዳዩን አስመልክቶ ከሃላባ ቁሊቶ ፖሊስ መምሪያ ጽህፈት ቤት መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።

ሆኖም የሀላባ ዞን የቁሊቶ ከተማ አሰተዳደር ሰላም እና ፀጥታ ጽህፈት ቤት በፌስቡክ ገጹ ባለፈው ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ ታዳጊ ሊዲያ ብቻ ሳትሆን አቶ ናስር የሚባሉ ግለሰብ በተመሳሳይ አይነት ወንጀል ተጠርጥረው ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ አስታውቋል።

መግለጫው ሊዲያ “ሙስሊም ተማሪዎች ላይ ድግምት አሲራለች” በሚል መታሰሯን በመግለጽ “ማንም በተጠረጠረበት ወንጀል ታስሮ እንደሚጣራ” ይታወቃል ብሏል።

ሆኖም ጉዳዩን “በማጦዝ ሃይማኖታዊ ለማስመሰል” የሚደረግ ጥረት እንዳለ እና ሰዎች ከዚህ ድርጊት እንዲቆጠቡም አሳስቧል።