March 15, 2023 

በፌደራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሠረት ይመሰረታል ተብሎ የሚጠበቀው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እስካሁን የዘገየው በፌደራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል ባለው የፖለቲካ ሽኩቻ ምክንያት መሆኑን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡

ከውስጥ አዋቂዎች ተገኘ በተባለው መረጃ መሠረት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ለኹለት ዓመታት የዘለቀው ጦረነት እንዲነሳ ምክንያት የሆኑት የሕወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ናቸው ብለው ይወነጅላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ጠቅላይ ሚንስትሩ ዶክተር ደብረጽዮን እንደ አዲስ በሚመሰረተው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የፕሬዘዳንትነት ሚና እንዲኖራቸው አይፈልጉም ተብሏል፡፡

የአስተዳደሩ ፕሬዘዳንት ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱትም ከሕወሓት ተለይተው ከወጡ በኋላ ዳግም በመመለስ በጦርነቱ የተሳተፉት ጻድቃን ገብረትንሳኤና በሕወሓት የአምስት ሰዎች ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ ብቸኛው የሕግ ምሩቅ የሆኑት የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ መሆናቸው ተነግሯል፡፡

የትግራይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕወሓት በጊዜያዊ አስተዳደሩ ስለሚኖረው ድርሻ የተለያዩ የተቃውሞ ሀሳቦችን ሲያነሱ የቆዩ ሲሆን፣ ሕወሓት በሽግግር አስተዳደሩ ዙሪያ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ያልተወከሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

የሕወሓት አባላት ከዚህ በፊት ለትግራይ ሕዝብ ደም አፍስሰናል በማለት የክልሉ ሰልጣን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረው ነበር ያሉ የሳልሳይ ወያኔ ደጋፊ እንደሆኑ የተናገሩ አስተያየት ሰጪም፣ አሁን ሁሉም ትግራይ ውስጥ ያለ ቤተሰብ ደም ገብሯልና የትግራይ ሕዝብን የሚስማማ መሪ ሊኖር ይገባል ብለዋል፡፡

ቃላቸውን ለዋሽንግተን ፖስት የሰጡ የመቀሌ ነዋሪዎችም ከዶክተር ደብረጽዮን ይልቅ ሌሎች የሕወሓት አባላት የክልሉን የመሪነት ቦታ ቢይዙ እንደሚመርጡ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ ይህ የነዋሪዎች አስተያትም ከጠቅላይ ሚንስትሩ ፍላጎት ጋር ተመሳሳይ መሆኑ ተዘግቧል፡፡

በሌላ ዜና፣ የሰላም ስምምነት ተፈርሞ በትግራይ ያለው የኑሮ ሁኔታ መሻሻል ማሳየቱን ተከትሎ የሕክምና ተቋማትንና ትምህርት ቤቶችን መልሶ የመገንባት ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን እንዳለበት ሴቭ ዘ ችልድረን አስታውቋል፡፡

መሠረቱን በዩናይትድ ሰቴትስ አሜሪካ ያደረገው ድርጅቱ በትግራይ ያሉ ከ80-90 በመቶ የሚሆኑት የሕክምና ተቋማትና ትምህርት ቤቶች ወድመዋል ያለ ሲሆን፣ ይህም የክልሉን ነዋሪዎች ኑሮ አስቸጋሪ አድርጎታል ብሏል፡፡ ለዚህም ርብርብ ተደርጎ መልሶ ግንባታዎች እንዲጀመሩ መደረግ አለበት ሲል ድርጅቱ አሳስቧል፡፡

source adis maleda