ድሮን

ከ 1 ሰአት በፊት

የሩሲያ የጦር ጀቶች ከአሜሪካ የቅኝት ሰው አልባ በራሪ (ድሮን) ጋር ተጋጭቶ ጥቁር ባሕር ውስጥ መውደቋን አሜሪካ የገለጸች ሲሆን፣ ድርጊቱንም ኃላፊት የጎደለው ነው ብላለች።

አሜሪካ ድሮኑ በዓለም አቀፍ የአየር ክልል ውስጥ በመደበኛ የቅኝት በረራ ላይ እንዳለ ሁለት የሩሲያ ተዋጊ ጀቶች ሊጠልፉት እንደሞከሩ ገልጻለች።

ክስተቱ በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት ሩሲያ እና አሜሪካ ቀጥተኛ ግጭት ውስጥ እንዳይገቡ የተፈጠረውን ስጋት አጉልቶታል።

ሆኖም ሩሲያ ተዋጊ ጀቶቹ ከድሮኗ ጋር ምንም አይነት ግኙነት አልነበራችወም ብላለች።

የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ድሮኑ በራሱ ምክንያት መውደቁን ጠቁሟል።

“ኤምኪው 9 የተባሉት የጦር አውሮፕላናችን በዓለም አቀፍ የአየር ክልል ውስጥ እየተንቀሳቀሰ በነበረበት ጊዜ በሩሲያ የጦር አውሮፕላን ተጠልፎ ተመቷል። በውጤቱም ድሮኑ ተከስክሶ ወድሟል” ሲል የአሜሪካ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

ኤስዩ 27 የተባሉት የጦር ጀቶች ድሮኑን ከመግጨታቸው በፊት “ኃላፊነት በጎደለው መንገድ፣ ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር ባልተገባ እና ሙያዊ ባልሆነ መንገድ” በተደጋጋሚ ነዳጅ ሲያፈሱ ነበር ብሏል።

ድርጊቱን በመቃወም አሜሪካ በዋሽንግተን የሚገኙትን የሩሲያ አምባሳደር አናቶሊ አንቶኖቭን ለማብራሪያ ጠርታለች።

ንግግሩንም ተከትሎ የሩሲያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን አምባሳደር አንቶኖቭን ጠቅሰው እንደዘገቡት፣ ሩሲያ የድሮኑን ክስተት “እንደ ትንኮሳ” እንደምትቆጥረውና “የአሜሪካ ጦር ከድንበራችን አቅራቢያ ስጋት ሊጭር የሚችል ድርጊት መፍጠሩ ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2014 ሩሲያ ክሪሚያን ከጠቀለለች በኋላ በጥቁር ባሕር አቅራቢያ ውጥረት ነግሷል።

ሩሲያ ዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ ከፈጸመች በኋላ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪምግደም (ዩኬ) ስምምነታቸውን በማደስ ዓለም አቀፉ የአየር ክልል የቅኝት በረራዎችን ያደርጋሉ።

ታዲያ ረቡዕ ዕለት የሩሲያ ተዋጊ ጀቶች የፈመጹት ተግባር የአሜሪካንን ድሮን እንቅስቃሴን ለማስተጓጎል የተደረገ ወይስ ሆን ተብሎ ድሮኑን ለመጣል የተሰነዘረ ጥቃት ነው የሚለው ጥያቄ ሆኖ ቀርቷል።

እንደ አሜሪካ ገልጻ ከሆነ ሩሲያ በቀጠናው ከሚገኙ የአሜሪካ አጋር አገራት አውሮፕላኖች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ተደጋጋሚ እና አደገኛ እንቅስቃሴዎችን ስታደርግ ቆይታለች።

ስለዚህ የአሜሪካ ድሮን ላይ የተፈጸመው ተግባር በዚህ ሂደት ውስጥ በስህተት የተፈጸመ ሊሆን ይችላል።

እናም ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ ይህ ድርጊት በሩሲያ ሆን ተብሎ የተፈጸመ ከሆነ ግን እንደ ትልቅ ጸብ አጫሪነት የሚወሰድ እና ከፍተኛ ጡዘት ሊያስከትል የሚችል ነው።

ይህም ማለት የሩሲያ መንግሥት የአሜሪካንን ምላሽ ለመፈተሽ የፈጸመው ድርጊት ሊሆን ይችላል ተብሏል።

የአሜሪካ የጦር አዛዦች ባወጡት መግለጫ ድርጊቱ አደገኛ ነው ያሉ ሲሆን “ይህም ወደተሳሳተ ስሌት እና ባልታሰበ ሁኔታ ሊባባስ” ይችላል ብለዋል።