
ከ 5 ሰአት በፊት
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ።
ብሊከን አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ከአፍሪካ ኅብረት መሪዎች ጋር ተገናኝተው ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የውጭ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ዋነኛ አጀንዳ ለሁለት ዓመታት ዘልቆ የቆየውን የሰሜን ኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት ለማቆም የፌደራሉ መንግሥት እና ህወሓት የደረሱት የሰላም ስምምነት አፈጻጸም መመልከት እንዲሁም በሽግግር ፍትሕ ጉዳይ ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ከሆኑ አጋሮችን እና የሲቪል ማኅበረሰብ አካላት ጋር በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት፣ በምግብ ዋስትና እና በሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ላይ እንደሚያዩም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል።
ብሊንከን በአዲስ አበባው ቆይታቸው ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት ጋር በዓለም አቀፋዊ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች፣ ከወራት በፊት በተካሄደው የአፍሪካ-አሜሪካ ጉባኤ ላይ ስለተነሱ ጉዳዮች ቀጣይ ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል።
- ባለ ብሩህ አእምሮ ወጣቶችን እያፈሩ ያሉት የኢትዮጵያ የአዳሪ ትምህርት ቤቶችከ 5 ሰአት በፊት
- በሃላባ ከትምህርት ቤት ተወስዳ የታሰረችው ታዳጊ እና የቀረበባት ክስከ 5 ሰአት በፊት
- ሻክሮ ለቆየው የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ግንኙነት የአንቶኒ ብሊንከን ጉብኝት ምን ይዞ ይመጣል?14 መጋቢት 2023
እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች ያሉ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ብሊንከን በጉብኝታቸው በጦርነቱ ወቅት ለተፈጸመሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነትን ማስፈን በአጀንዳቸው እንዲያካትቱ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ብሊንከን በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከአገሪቱ ባለስልጣናት ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ ይነጋገራሉ ብሏል።
አንቶኒ ብሊንከን እስከ አረብ መጋቢት 7/2015 ዓ.ም. በአፍሪካ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በኒጀር ጉብኝነት ያደርጋሉ።
ብሊንከን በኒጀር ጉብኝታቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ ኒጀር በማቅናት በሳህል ቀጠና የጂሃዲስት መስፋፋት ጉዳይ ጋር ከባለስልጣናት ጋር ይነጋገራሉ።
በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የርስ በርስ ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ መንግሥታት ግንኙነት ሻክሮ መቆየቱ ይታወሳል።
በጦርነቱ ወቅት በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያትም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጫናዎችን የሚያሳድሩ እርምጃዎችን የወሰደች ሲሆን፣ ከዚህም መካከል ኢትዮጵያ ከቀረጥ ነጻ ምርቶችን ወደ አሜሪካ ለማስገባት ከሚያስችለው የአጎዋ መረሃ ግብር እንድትወጣ ተደርጓል።
ጦርነቱን ያስቆመው ስምምነት ከተደረሰ በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት መሻሻልን እያሳየ ሲሆን፣ የብሊንከን ጉብኝት ከጦርነቱ መቆም በኋላ በከፍተኛ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣን የተደረገ የመጀመሪያው ጉብኝት ነው።