የምርጫ ቦርድ አርማ

15 መጋቢት 2023, 15:41 EAT

ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ እንዳያደርጉ መከልከል፣ በእስር እና በእንግልት ማዋከብ ተቀባይነት እንደሌለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሳሳበ።

ቦርዱ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ አዳራሾች መከልከል እንዲሁም ጉባኤ ከማድረጋቸው በፊት እና በኋላ በእስር የማዋከብ ተግባር እየተፈጸመ መሆኑን ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 6/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ጉባኤ እንዳያደርጉ ከተከለከሉ ወይም አባላቶቻቸው እስር ከተፈጸመባቸው መካከል እናት፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ እንዲሁም ጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትህ ፓርቲ (ጎጎት) መሆናቸውም ተጠቅሷል።

የእናት ፓርቲ የካቲት 26/2015 ዓ.ም. በሥላሴ ዩኒቨርስቲ አዳራሽ ሊያደርገው የነበረ ጉባኤ በሕግ አስፈጻሚ ኃላፊ መደናቀፉን ጠቅሷል።

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ መጋቢት 3/2015 ዓ.ም. በጋምቤላ ሆቴል ሊያካሂድ የነበረው ጠቅላላ ጉባኤ በሆቴሉ ባለቤቶች እንዲሁም የሥራ ኃላፊዎች እና በፀጥታ ኃይሎች ማስፈራሪያ ሳይካሄድ ቀርቷል ብሏል።

እንዲሁም ጎጎት ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤውን መጋቢት 3/2015 ዓ.ም. ካከናወነ በኋላ በማግስቱ አባላቱ አቶ ዮናታን ሰለሞን እና አቶ ረመዳን ሙሉጌታ በፌደራል ፓሊስ ታሰረው ለደቡብ ክልል ፖሊስ ተላልፈው መሰጠታቸውን ነው ቦርዱ በመግለጫው ያሰፈረው።

ፓርቲዎች ጉባኤዎቻውን እንዳያደርጉ እንዲሁም በሂደት ላይ እያለ ማደናቀፍም ሆነ እየደረሰ ያለው ማዋከብ ተቀባይነት እንደሌለውና ቦርዱ በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት እንዳይወጣም ከፍተኛ ጫና እንዳሳረፈበት ገልጿል።

“ይህ ጥፋት በየትኛውም አካል ቢፈጸም በምንም መመዘኛ ተቀባይነት ያለው ድርጊት አይደለም፤ ሕገ መንግሥታዊ የመደራጀት መብትን የሚጥስ፣ በመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ሙከራ ላይም ከፍተኛ አሉታዊ ጫና ያሳርፋል” በማለት መግለጫው አትቷል።

በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሠረት ይህንን ጥሰት የፈጸሙ የሕግ አስፈጻሚ አባላት በወንጀል እንደሚያስጠይቃቸው የገለጸው ቦርዱ፣ የፍትህ ሚኒስቴር የወንጀል ምርመራ እንዲመራ እና አጥፊዎቹም እንዲከሰሱ ጠይቋል።

በተጨማሪም በእስር ላይ ያሉት የጎጎት ፓርቲ አባላትን የደቡብ ክልል ፖሊስ በአስቸኳይ ይፍታ ሲልም አሳስቧል።

በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስር የሚተዳደሩ የስብሰባ ቦታዎች ለፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤዎች ክፍት እንዲሆኑ የጠየቀው ቦርዱ፣ ይህንንም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት እንዲሁም የክልል ፕሬዝዳንቶች ጽህፈት ቤት አማካኝት እንዲፈጸም ውሳኔ አስተላልፏል።