March 16, 2023 – BBC Amharic 

አሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን)

ከ 4 ሰአት በፊት

በጥቁር ባህር ላይ የወደቀውን የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ቀሪ አካል ለማውጣት እንደምትሞክር ሩሲያ አስታወቀች።

ኤም ኪው 9 ሪፐር የተሰኘው የአሜሪካ ድሮን ማክሰኞ መጋቢት 5፣ 2015 ዓ.ም ነው ወደ ጥቁር ባህር የወደቀው።

አሜሪካ ድሮኑ በሩሲያ ተዋጊ ጄት ጋር ከተጋጨ በኋላ “ሊበር ወደማይችልበት ደረጃ” ላይ በመድረሱ እንደወደቀ ብታስታውቅም ሩሲያ በበኩሏ ይህንን አልተቀበለችውም።

በመንግሥት ቴሌቪዥን ላይ ንግግር ያደረጉት የሩሲያ የጸጥታ ምክር ቤት ጸሐፊ ኒኮላይ ፓትሩቬቭ ሞስኮ ድሮኑን ለማግኘት እየሞከረች መሆኑን አረጋግጠዋል።

“ልናገኘው እንችላለን ወይ የሚለውን ባናውቅም መሞከር አለብን” በማለት ኒኮላይ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ድሮኑ በጥቁር ባህር ውስጥ መገኘቱ አሜሪካ በጦርነቱ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዳደረገች የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

የዋሽንግተን ከፍተኛ ባለስልጣን ጆን ኪርቢም አሜሪካ ድሮኑን እየፈለገች እንደሆነ አስታውቀው ሩሲያ በማግኘቱ ረገድ ከቀደመች ጠቃሚ የሚባል የደህንነት መረጃን ለማግኘት አዳጋች ያደርገዋል ሲሉ አሳስበዋል።

የአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣን ጄኔራል ማርክ ሚሌይም ተመሳሳይ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በወደቀው ሰው አልባ አውሮፕላን ላይ ጠቃሚ ያለው መረጃ እንዳይኖርም አንዳንድ የጥንቃቄ እርምጃዎችን አገራቸው ወስዳለች ብለዋል።

ሰው አልባ አውሮፕላኑን ለማውጣት ፈታኝ እንደሚሆን የጠቆሙት ባለስልጣኑ ለዚህም የውሃው ጥልቀት ከ1 ሺህ 200-1 ሺህ 500 ሜትር መሆኑም እንደ ምክንያት ተጠቅሷል።

ማክሰኞ ጥዋት ላይ ከ30-40 ደቂቃ በዘለቀው ክስተት ድሮኑ ከሩሲያ ጄቶች ጋር ከመጋጨቱ በፊት ሩሲያ በተደጋጋሚ በነዳጅ እንደደፈቀችው ነው አሜሪካ የገለጸችው።

የፔንታጎን ቃለ አቀባይ ብሪጅ ጄኔራል ፓት ራይደር ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ድሮኑ ከጥቅም ውጭ ሆኖ የማይበርበትና መቆጣጠር የማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ነው። በዚህም ግጭት የሩሲያ የጦር ጄቶች ሳይጎዱም እንዳልቀረ አክለዋል።

ሆኖም ሩሲያ ሱ27 የተሰኙት ሁለቱ ተዋጊ ጄቶቿ ከድሮኗ ጋር ምንም አይነት ንክኪ አልነበራቸውም ብላለች።

የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር ሰው አልባ አውሮፕላኑ ተከስክሶ የወደቀው ራሱ ባደረገው እንቅስቃሴና የመገናኛ መሳሪያው ጠፍቶ ሲበር እንደነበር ገልጿል።

የድሮኑ መውደቅን ተከትሎ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲንና ከሩሲያ አቻቸው ሰርጌ ሾይጉ ጋር መነጋገራቸውን አረጋግጠዋል።

ከስልክ ጥሪው በኋላ በተለቀቀው መግለጫ የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር ድርጊቱን “ከሩሲያ ፌደሬሽን ጥቅም ጋር የሚጻረር የስለላ ስራዎች መጨመሩን የሚያሳይ ነው” ሲል ወቅሷል።

በተጨማሪ በክሬሚያ የባህር ጠረፍ ላይ የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላኖች መገኘታቸው “ተንኳሽ ነው” ሲልም ገልጿል።