March 16, 2023 – BBC Amharic 

ቻይናዊውን ባለጸጋ ጉዎ ዌንጋይ
የምስሉ መግለጫ,ቻይናዊውን ባለጸጋ ጉዎ ዌንጋይ

ከ 3 ሰአት በፊት

የአሜሪካ ባለስልጣናት ኑሮውን ኒውዮርክ ያደረገ አንድ ቻይናዊ ባለሃብት አንድ ቢሊዮን ዶላር አጭበርብሯል የሚል ክስ አቅርበዋል።

ጉዎ ዌንጋይ እና ኪን ሚንግ የተባለ የንግድ አጋሩ በኢንተርኔት፣ ባንክና የደህንንት ስርዓት በማጭበርበር እንዲሁም ህገወጥ ገንዘብን ህጋዊ ለማስመሰል በመሞከር ክስ ቀርቦባቸዋል።

የቻይናን መንግሥት በመተቸት የሚታወቀው ጉዎ የቀድሞው የኋይት ሃውስ ዋና የስትራቴጂ ሰው ተባባሪም ነበር።

ባለሃብቱ ከታሰረ ከጥቂት ሰዓታት በኃላ በማንሃተን የሚገኘው አፓርታማው ላይ እሳት ተቀስቅሷል።

የከተማው እሳት አደጋ መከላከል መስሪያ ቤቱ እሳቱ በቁጥጥር ስር እንደዋለና የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ገልጾ የአደጋው መንስኤ እየተጣራ ነው ብለዋል።

ቀድም ብሎ ባለሃብቱ ጉዎ በማህበራዊ ሚዲያ ባሰራጨው መልዕክት እጁ ታስሮ ከአንድ ሰዓት በላይ ምርመራ እንደተደረገበት ገልጸዋል።

ባለሃብቱ በተለያዩ ሰሞች የሚጠራ ሲሆን ትላንት ረቡዕ በቀረበው የክስ መዝገብ ላይ ሆን ዋን ካውክ በሚል ስያሜ ተጠቅሷል።

ጉዎና አጋራቸው የመገናኛ ብዙሃን ቢዝነስ ላይ እናሳትፋችኋለን በሚል በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ከተጠቃሚዎች አንድ ቢሊዮን ዶላር ማሰባቸውሰባቸውን የቀረበባቸው ክስ ያስረዳል።

በተጨማሪም ከተጠቃሚዎች ገንዘብ ለመስረቅ ክሪፕቶከረንሲ ተጠቅመዋል የሚል ክስ ቀርብቧል።

ባለጸጋው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ላይ ያለውን ተቃውሞና ከፍተኛ ስም ካላቸው የአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር ያለውን ግንኙነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮችን በማህበራዊ ሚዲያ እንዲያገኝ አስችሎታል። አብዛኞቹ ተከታዮች በምዕራባውያን ሀገራት የሚኖሩ ቻይናውያን ናቸው።

አቃብያነ ህግ ግለሰቡ ማህበራዊ ሚዲያ ያለውን ስም ለንግድ ስራ በሚል ገንዘብ ማሰባሰቢያ እንዳደረጉት ጠቅሰዋል። ሆኖም ያገኙትን ገንዘብ ወደንግድ ስራ ከማዋል ይልቅ ከራሳቸው ጋር ወደ ተያያዘ የግል ገንዘብ ቋት ወስደውታል የሚል ክስ ቀርቦበታል።

የተሰበሰበውን ገንዘብ 4 ሺህ 345 ካሬ መሬት ለሚሸፍን እና በኒውጀርሲ ለሚገኝ መሬት፣ እጅግ ቅንጡ መኪናዎችና ወደ 1 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ለሚያወጡ የቻይናና ፐርዥያ ምንጣፍ ለመግዛት መዋ ተገልጿል።

አቃብያነ ህጉ ከተሰበበሰበው ገንዘብ 1 ሚሊዮን ዶላር ከፍተኛ ስጋት ለተጋረጠበት ንግድ መዋሉን ገልጸው የተቀረው ግን 140 ሺህ ዶላር ለሚያወጣ ፒያኖ፣ ለ62 ሺህ ዶላር ቴሌቪዥን፣ ለ53 ሺህ ዶላር የሳሎን እሳት ማያያዣ እና መሰል ቅንጡ ምርቶች ግዢ መዋሉን ጠቁመዋል።

ባለሃብቱ ወደ 4.4 በሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ የሚያወጣውን ይህንን ቡጋቲ የተባለ ቅንጡ መኪና በፍላጎታቸው መሰረት ማስመረታቸውን አቃቢያነ ህግ ገልጸዋል
የምስሉ መግለጫ,ባለሃብቱ ወደ 4.4 በሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ የሚያወጣውን ይህንን ቡጋቲ የተባለ ቅንጡ መኪና በፍላጎታቸው መሰረት ማስመረታቸውን አቃቢያነ ህግ ገልጸዋል

ከባለፈው መስከርም ወር ጀምሮ የአሜሪካ መንግሥት ከ21 የተለያዩ ባንኮች ወደ 634 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ አግዷል።

ጉዎ ሁለት ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶችን አቋቁሚያለሁ በሚል የቻይና መንግሥትን የሚቃወሙ ተከታዮችን ለማፍራት መሞከሩም በክሱ ተመላክቷል።

ባለጸጋው በሪል ኢስቴት ግንባታ ላይ የተሰማራ ሲሆን እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 ሀገሩን ለቆ ከመሄዱ በፊት በቻይና ከሚገኙ ባለሃብቶች አንዱ ነበር።

በ2017 በቻይና ኮሚኒቲ ፓርቲ ጫና ይደርስብኛል በሚል የአሜሪካ መንግስትን ጥገኝነት ጠይቋል።