March 16, 2023 – BBC Amharic 

የአውሎ ንፋስ ያስከተለው ከባድ ጎርፍ

ከ 2 ሰአት በፊት

የአውሎ ንፋስ ባስከተለው ከባድ ጎርፍ በተመታችው ማላዊ ከ225 ሰዎች በላይ ሞቱ።

ከፍተኛ ጥፋት ያስከተለውንም ይህንን ቀውስ “ብሄራዊ ሃዘንን” አስከትሏል ሲሉ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ገልጸዋል።

በጎርፉ ህይወታቸውን ባጡ ተጎጂዎች የቀብር ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ላዘረስ ቻክዌራ የፍለጋ እና የማዳን ስራዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ቃል ገብተዋል።

ፍሬዲ በተሰኘው አውሎ ንፋስ ባስከተለው ጎርፍ በርካቶች ተወስደዋል፤ እንዲሁም በተፈጠረውም የመሬት መንሸራተትም በፍርስራሾች የተቀበሩም አሉ።

መንግሥት ከቤታቸው ለቀው ለወጡ ቢያንስ 20 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች 30 የድንገተኛ አደጋ መጠለያዎች አቋቁሟል።

ኮረብታማዋ የማላዊ የንግድ ማዕከል የሆነችው ብላንታይር ከተማ በከፋ ሁኔታ ተጎድታለች። በመሬት መንሸራተቱ ነዋሪዎቿ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን መኖሪያ ቤቶችም በጎርፉ ፈራርሰዋል።

“የጤና ሰራተኞቻችን እርዳታ በሚፈልጉበት ሁኔታ ላይ ነው ያለነው” ሲሉም የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ኩምቢዜ ካንዶዶ ቺፖንዳ ለቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ተናግረዋል።

ከፍተኛ ቀውስ እንደተፈጠረ የተናገሩት ሚኒስሯ ይህ አውሎ ንፋስ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎችንም ጎድቷል ብለዋል።

“አውሎ ንፋስ በአገሪቷ በተደጋጋሚ የሚታይ ነው። ነገር ግን እን አለመታደል ሆኖ ፍሬዲ አውሎ ንፋስ ፈጽሞ ታይቶ የማይታወቅና ያልተጠበቀ ነው” ብለዋል።

አክለውም “በአሁኑ ወቅት አስከሬኖችን የመሰብሰብ ስራ ላይ ነን። አንድ ህጻን ልጅ በአስከሬኖች መካከል በህይወት አግኝተናል” ብለዋል።

የመንግስት የአደጋ አስተዳደር ኤጀንሲ እንዳስታወቀው በብላንታይር እና በሌሎች የደቡብ ማላዊ አካባቢዎች 41 ሰዎች እስካሁን የጠፉ ሲሆን ከ700 በላይ ሰዎች ቆስለዋል።

“የቅርብ ጓደኛዬ፣ ወንድሟ፣ እህቷ እና እናቷ በመሬት መንሸራተቱ የተወሰዱ ሲሆን እስካሁንም አስከሬናቸው አልተገኘም። በጣም ልብ የሚሰብር ነው። እርማችንን እንኳን ማውጣት አልቻልንም” ስትል የብላንታየር ነዋሪ የሆነችው ፋዲላ ንጆሎሞሌ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግራለች።

ፕሬዚዳንቱ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ21 ግለሰቦች የቀብር ስነስርዓት ላይ በተገኙበት ወቅትም “ከአለም አቀፍ አጋሮች እና ለጋሾች ተጨማሪ እርዳታ እንዲደረግልን እንጠይቃለን። እያንዳንዳንዱን ዜጋ የጎዳ ሀገራዊ አደጋ ነው” ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ የ14 ቀናት ብሔራዊ ሃዘን አውጀዋል።