March 16, 2023 – BBC Amharic

አንቶኒ ብሊንከንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

15 መጋቢት 2023

በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በነበራቸው ቆይታ በጦርነቱ ወቅት ለተፈጸሙ ጥሰቶች ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጠየቁ።

ለሁለት ዓመት የዘለቀው ጦርነት ተጀምሮ በሰላም ስምምነት ከተቋጨ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን የጎበኙት ብሊንከን፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ዛሬ መጋቢት 6/2015 ዓ.ም. በተገናኙበትም ወቅት ነው ይህንን የተናገሩት።

ብሊንከን ባለፈው ጥቅምት መጨረሻ ላይ የተፈረመው ግጭትን በዘላቂነት የማስቆም ስምምነት በትግራይ አፈሙዝን ጸጥ በማስገኘት ረገድ የተደረሰበትን ሂደት አድንቀው፤ አገራቸውም ለዚህ ድጋፏን እንደምትቀጥል ቃል ገብተዋል።

ሆኖም በትግራይ ተከስቶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በተዛመተው ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ተሳታፊ በሆኑ አካላት በተፈጸሙ ጥሰቶች ዙሪያ ተጠያቂነት ሊኖር እንደሚገባ አሳስበዋል።

በመቶ ሺዎች በተቀጠፉበት ጦርነት መደፈር፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የዘፈቀደ ግድያ፣ ረሃብ በጦር መሳሪያነት ጥቅም ላይ መዋላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ሪፖርት ያሳያል።

በጦርነቱ ተሳታፊዎች የጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች መፈጸማቸውን የመንግሥታቱ ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በሪፖርቶቻቸው ይፋ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ እነዚህን ጥሰቶች ለመርመር እና ተጠያቂነት ለማስፈን የሽግግር ወቅት ፍትሕን እንደ አንድ አማራጭ አቅርባለች።

እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ያቋቋመው የባለሙያዎች ቡድንም ሥራው እንዲቋረጥ እየጠየቀች ትገኛለች።

ይህንንም ተከትሎ ከስድሳ በላይ የሚሆኑ ዓለም አቀፍ የሲቪል ማኅበራት እና የመብት ተሟጋቾች የኢትዮጵያ ጥረት ‘ያልተጠበቀ’ እና ዓለም አቀፍ ምርመራን ለማስቀረት የሚደረግ ጥረት ነው ማለታቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የውጭ ጉዳይ ኃላፊው በውይይታቸው ወቅት በተለያዩ የአገር ውስጥ፣ አህጉራዊ እና ሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት መደረጉን ያስታወቀው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት፣ ብሊንከን በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ቃል ገብተዋል ብሏል።

በተጨማሪም በምጣኔ ሃብት፣ ልማት በተለይም በግብርና እና ቀጣናው በማረጋጋት ረገድም ትኩረት ያደረገ ውይይት ተካሂዷል ሲል ጽህፈት ቤቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።

ብሊንከን በዚሁ ጉብኝታቸው ለኢትዮጵያ ከ331 ሚሊዮን ዶላር በላይ አዲስ የሰብዓዊ እርዳታ ለመለገስም ቃል ገብተዋል።

አገራቸው ይህንን የገንዘብ እርዳታ የምታደርገው በጦርነቱ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ፣ በድርቅና በምግብ እጦት ለተጎዱ የህይወት አድን ድጋፍ እንደሚሆንም ተገልጿል።

የሰላም ስምምነቱ መፈረምን ተከትሎ ጦርነቱ ጋብ ያለ ሲሆን ተቋርጦ የነበረው ሰብዓዊ እርዳታም ተደራሽነቱ ጨምሯል።

ሆኖም የመሠረታዊ አገልግሎቶችን እንደገና የመመለስ ሂደት አዝጋሚ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በጦርነቱ ምክንያት የደረሰውን መጠነ ሰፊ ጉዳት ለመገንባት ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል።

ብሊንከን ከሰላም ስምምነቱ በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል የቀጠለው ግጭት እና አለመረጋጋት ያሳደረባቸውን ስጋት ገልጸው በውይይት እንዲፈታም አሳስበዋል።

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ወደ ኒጀር የሚያቀኑት አንቶኒ ብሊንከን ይህ ጉብኝታቸው በአፍሪካ እያደገ የመጣውን የቻይና እና የሩሲያን ተጽእኖ ለመመከት ያለመ እንደሆነ ይነገራል።