
16 መጋቢት 2023, 13:13 EAT
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊነት ከያዙ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት አንቶኒ ብሊንከን፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ ከተለያዩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ከህወሓት አመራሮች እና ከአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር ጋር ተገናኝተዋል።
ግጭትን በዘላቂነት የማስቆም ስምምነቱ ላይ የታየውን እመርታ ያደነቁት ብሊንከን በትግበራው፣ በሰብዓዊ እርዳታ እንዲሁም ተጠያቂነትን በማስፈን እና በሽግግግር ፍትህ ሥርዓቱ አካታችነት ዙሪያ ከባለሥልጣናቱ ጋር ተነጋግረዋል።
ረቡዕ መጋቢት 6/2015 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ የገቡት የውጭ ጉዳይ ኃላፊው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከጋዜጠኞች ስለ ተጠያቂነት፣ ስለ ኤርትራ ጦር እና ሌሎች ኃይሎች ከትግራይ አለመውጣት እንዲሁም ኢትዮጵያን ወደ አጎዋ ተጠቃሚነት የመመለስን ጉዳይ በተመለከተ ጥያቄዎች ቀርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በቀጠፈው ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት እና ከተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ የአሜሪካ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ሻክሮ የነበረ ሲሆን፣ ይህንንም ግንኙነት ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ተገልጿል።
የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. በፕሪቶሪያ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።
ወደ አጎዋ ተጠቃሚነት የመመለስ ጥያቄ
የአሜሪካ መንግሥት ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገራት የዘረጋው ከቀረጥ ነጻ ዕድል ተጠቃሚ የነበረችው ኢትዮጵያ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች አጎዋ ከተሰኘው ከዚህ ዕድል ታግዳለች።
አሜሪካ ይህንን እገዳ ለመጣል በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በመፈጸሟ እንደሆነ የገለጸች ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ይህንን ስትቃወም ቆይታለች።
በ2005 ዓ.ም የአጎዋ ፎረምን ያስተናገደችው ኢትዮጵያ በአጎዋ በኩል ለሁለት አስርት ዓመታት የተለያዩ ምርቶችን [በስፋት ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት] ለአሜሪካ ገበያ በማቅረብ ለመቶ ሺዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በሚሊዮኖች የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ ስታገኝ ቆይታለች።
ኢትዮጵያን ከቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት ዕድል፣ አጎዋ ማስወጣትም ከ200 ሺህ በላይ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ቤተሰቦች ላይ ተፅእኖ እንደሚኖረው እና በተለይም ከግጭቱ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ሴቶች ላይ ጉዳቱ ይበረታል ስትል ቆይታለች።
በተለይም በጥቅምት መጨረሻ ላይ የተደረሰውን ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ተከትሎ ወደ ተጠቃሚነቱ እንድትመለስ ጥያቄ እያቀረበች ይገኛል።
ብሊንከን በዚህ ወቅትም ኢትዮጵያ ከቀረጥ ነጻ ንግድ ተጠቃሚ አገራት እንድትሰረዝ የተደረገችው ሕግን በተከተለ መልኩ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ሳቢያ ነው ሲሉም አውስተዋል።
ኢትዮጵያ ወደ አጎዋ ተጠቃሚነት ለመመለስ መሟላት ያለባቸው ግልጽ የሆኑ መስፈርቶች እንዳሉም ጠቅሰው፣ የባይደን አስተደደር ይህንን ከግብ ለማድረስ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርበት መሥራቱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ግጭት የማስቆም ስምምነቱ ጋር በተያያዘ በተለይም የአተገባበሩ ዘላቂነት መቀጠል ለዚህ ወሳኝ ነው ያሉት ብሊንከን፣ ስምምነቱ ዘላቂ እንደሚሆን ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ኢትየጵያ ወደ አጎዋ ተጠቃሚነት የመመለሷን ጥያቄም እንደሚረዱ ገልጸው፣ ግጭት በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ትግበራው መቀጠል ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ የሚወስድ ሂደት ነው ብለዋል።
- ብሊንከን በጦርነቱ ለተፈጸሙ ጥሰቶች ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጠየቁ15 መጋቢት 2023
- ሻክሮ ለቆየው የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ግንኙነት የአንቶኒ ብሊንከን ጉብኝት ምን ይዞ ይመጣል?14 መጋቢት 2023
ብሊንከን ከባለሥልጣናት ጋር ያደረጉት ቆይታ
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም በሰላም ስምምነቱ ተደራዳሪ ከነበሩ ባለሥልጣናት ጋር ተነጋግረዋል።
የፌደራሉ መንግሥት ዋነኛ ተደራዳሪ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የህወሓት ተደራዳሪ እና ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር መወያየታቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል።
በዚህ ውይይትም ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነቱ እንዴት እየሄደ እንደሆነ የተገመገመ ሲሆን፣ ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እንደሚቀሩም መስማማታቸው ተገልጿል።
በተጨማሪም ሁለቱም ወገኖች የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መመሥረትን የስምምነቱ ቁልፍ ተግባር አድርገው ማየታቸው ተጠቅሷል።
አሜሪካ ለሰላም ስምምነቱ የምትሰጠውን ድጋፍ እንዲሁም ስለ ሂደቱ ተወያይተዋል።
“ሰላም በሰዎች ሕይወት ላይ ተጨባጭ ውጤት እንደሚያመጣ ማየት አለባቸው። ይህም የሚጀምረው ግጭት ሲቆም ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ ግን መሠራት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ” ብለዋል።
በጦርነቱ በሁሉም ወገኖች የተፈጸሙ ሰብዓዊ ጥሰቶችን በተመለከተ ዕውቅና መስጠት ዘላቂ ሰላምንም ለማስፈን ወሳኝ እርምጃ እንደሆነም ብሊንከን ገልጸዋል።
ስለ ጦርነቱ እና የሰላም ስምምነቱ አተገባበር
ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነትን “ፍጹም አውዳሚ” ሲሉ ብሊንከን ገልጸውታል።
የመቶ ሺዎችን ሕይወት እንደቀጠፈ፣ በሴቶች ላይ ሰለደረሰው መጠነ ሰፊ ወሲባዊ ጥቃት እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ቀያቸውን ጥለው እንዲሰደዱ አስገድዷል ብለዋል።
ብሊንከን ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች እና የንግድ ተቋማት በከባድ መሳሪያዎች ተመትተው መውደማቸውን እንዲሁም በርካቶች መሠረታዊ የሚባሉ በምግብ፣ በመጠለያ እና በመድኃኒት እጦት እየተሰቃዩ እንደሆነም በዚሁ አጋጣሚ ገልጸዋል።
ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነቱ ሕይወትን ለመታደግ እና ለማሻሻል ትልቅ ስኬት እና አንድ እርምጃ ወደፊት የተራመደ እንደሆነም ብሊንከን ጠቁመው አፈሙዞች ጸጥ ተሰኝተዋል ብለዋል።
ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እንዲሁም በሌላ ወገን የትግራይ ክልል አመራሮች ስምምነት ላይ በመድረሳቸው እንዲሁም ቃላቸውን በመፈጸም ስምምነቱ ላሳየው ጉልህ ለውጥ አመስግነዋል።
የስምምነቱ ጥረቶች በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በጦርነቱ የተጎዱ ማኅበረሰቦችን መልሶ ለመገንባት ሁነኛ መሠረት መሆናቸውን የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣኑ የተነገረው።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ብሊንከን በጥብቅ ያሳሰቡት በስምምነቱ አተገባበር ላይ የሴቶች ተሳትፎ በተለይም በውሳኔ ሰጪነት ሚና መካተታቸውን ነው።
ጦርነቱ ከመቆሙ ጋር ተያይዞ እየተያዩ ያሉ መሻሻሎችን የጠቀሱት ብሊንከን፣ በዚህም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ቀንሰዋል፣ የሰብዓዊ እርዳታም እየገባ ነው፣ በትግራይ ክልል መሠረተ ልማቶች እየተመለሱ ነው ብለዋል።
በስምምነቱም መሠረት የህወሓት ኃይሎች ከባድ መሳሪያ እየፈቱ ነው፣ የኤርትራ እና ሌሎች የፌደራል መንግሥቱ ያልሆኑ ኃይሎች እየወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል ብሊንከን።
ሆኖም የኤርትራ ኃይሎች በድንበር አካካቢ እንዲሁም የፋኖ እና የአማራ ሚሊሻዎች በምዕራብ ትግራይ ስለመገኘታቸው በጋዜጠኞች ተጠቅሷል።
በፕሪቶሪያ እና በናይሮቢ የተፈረመው የሰላም ስምምነት እና የመተግበሪያ ሰነድ መሠረት የትግራይ ኃይሎች ከባድ መሳሪያ ሲያስረክቡ የውጭ ኃይል እና ከአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎች በተመሳሳይ ወቅት ከክልሉ ይወጣሉ መባሉ ይታወሳል።
በትግራይ የመድፈር ወንጀሎች መቀጠላቸው ሪፖርት መደረጉ እንዲሁም የእነዚህ ወታደሮች ከክልሉ አለመውጣታቸው የስምምነቱ አተገባበር ውጤታማ እንዳይሆን ስጋት አለዎት ወይ? የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች ለብሊንከን ተነስቶላቸዋል።
የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የደረሰበት ሂደት ጥሩ መሆኑን የገለጹት ብሊንከን፣ የኤርትራን ጦር ጨምሮ ከፌደራሉ መንግሥት ውጪ ያሉ ኃይሎች እየወጡ ነው ብለዋል። ሆኖም የኤርትራ ጦርን በተመለከተ እየወጡ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ እንዳልወጡ ገልጸዋል።
ግጭትን በዘላቂነት ለማስቆም ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ የኤርትራ ሠራዊት አባላት በትግራይ ሴቶች ላይ የመድፈር ወንጀል ስለመፈጸማቸው ክስ እየቀረበባቸው ይገኛል።
እየተነሱ ካሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለተ የተባበሩት መንግሥታት ተወካዮችን ጨምሮ ከተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና ባለሙያዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸው፣ በትግራይ እነዚህ ጥሰቶች መቀነሳቸውን መረዳታቸውን ገልጸዋል።
ጥሰቶቹ ሙሉ በሙሉ ቆመዋል ማለት እንዳልሆነም ገልጸው፣ የጦርነቱ ተሳታፊ ወገኖች ሙሉ በሙሉ ጥሰቶቹ እንዲቆሙም ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አጥብቀው አሳስበዋል።

ተጠያቂነት የማስፈን አስፈላጊነት
በጦርነቱ ለተፈጸሙ ጥሰቶች ተጠያቂነት መስፈን እንዳለበትም ብሊንከን አሳስበዋል።
በመቶ ሺዎች በሞቱበት ጦርነት መደፈር፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የዘፈቀደ ግድያ፣ ረሃብ በጦር መሳሪያነት ጥቅም ላይ መዋላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ሪፖርት ያሳያል።
በጦርነቱ ተሳታፊዎች የጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች መፈጸማቸውን የመንግሥታቱ ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በሪፖርቶቻቸው ይፋ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ እነዚህን ጥሰቶች ለመርመር እና ለመዳኘት ያቀረበችው የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት ዕርቅን እና ተጠያቂነትን ማዕከል ባደረገ መልኩ ሁሉንም አካታች እንዲሁም ሁለገብ በሆነ መልኩ ተግባራዊ እንዲሆንም ጥሪ አድርገዋል።
አገራቸውም የሰላም ስምምነቱን በማስፈጸም ሂደት፣ የሰብዓዊ ጥሰቶች መቆማቸውን ማረጋገጥ እንዲሁም የሽግግር የፍትሕ ሥርዓቱ ሁሉን አቀፍ እና ተዓማኒነት ባለው ሁኔታ መተግበሩን በተመለከተ እገዛዎች እና ተሳትፎ እንደሚኖራት አስረግጠዋል፥
በተለያዩ በአገሪቱ ክልል እየደረሱ ያሉ የብሔር ጥቃቶችን፣ እንዲሁም ስር የሰደዱ ቅሬታዎች እና የብሔር መከፋፈልን በአገሪቱ የሚታየውን አዙሪት መስበር አስፈላጊ እንደሆነም ገልጸዋል።
አገራቸው ይህንንም ሂደት ለመደገፍ ቴክኒካዊ እና የገንዘብ ድጋፍ እያደረገች ስለመሆኑም ተናግረዋል።
ብሊንከን አገሪቷ በኢኮኖሚያዊ ችግሮች፣ በድርቅ እና በምግብ ዋስትና ስጋቶች እየተፈተነች ትገኛለች ያሉ ሲሆን፣ በዚሁ ጉብኝታቸው ለኢትዮጵያ ከ331 ሚሊዮን ዶላር በላይ አዲስ ሰብዓዊ እርዳታ ለመለገስ ቃል ገብተዋል።
አሜሪካ የገንዘብ እርዳታውን የምትሰጠው በጦርነቱ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ፣ በድርቅ እና በምግብ እጦት ለተጎዱ የሕይወት አድን ድጋፍ እንደሚሆንም ተገልጿል።
አገራቸው በኢትዮጵያ፣ ኢኮኖሚ፣ ልማት፣ ትምህርት፣ ዲሞክራሲ የምታደርገውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደምትቀጥል ቃል የገቡት ብሊንከን፣ “ተልዕኳችን በአሜሪካ እና በኢትዮጵያ መካከል ጠንካራ አጋርነት መገንባት ነው” ብለዋል።
አንቶኒ ብሊንከን ዛሬ መጋቢት 07/2015 ዓ.ም. አገራቸው ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ስላላት አጋርነት ለመወያየት ከአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት ጋር ተገናኝተዋል።
አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እና ቡድን 20ን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ እንድትወከል ድጋፋቸውን እንደሚሰጡም የውጭ ጉዳይ ኃላፊው ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ወደ ኒጀር የሚያቀኑት አንቶኒ ብሊንከን በእነዚህ አገራት የሚያደርጉት ጉብኝት ፕሬዝዳንት ባይደን በአሜሪካ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ላይ የገቡትን ቃል ለማረጋገጥ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሆኖም ጉብኝታቸው በአፍሪካ እያደገ የመጣውን የቻይና እና የሩሲያን ተጽእኖ ለመመከት ያለመ እንደሆነ ይነገራል።