March 17, 2023 – BBC Amharic 

ኮኬይን

16 መጋቢት 2023

በኮቪድ-19 ምክንያት የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉ የኮኬይን ምርት እና ፍላጎት እንዲጨምር ማድረጉን አንድ ጥናት አመለከተ።

የተባበሩት መንግሥታት የአደንዛዥ ዕጽ እና ወንጀል ቁጥጥር ቢሮ በሠራው ጥናት ለኮኬይን ምርት ግብዓት የሚሆነው ኮካ የተባለው ተክል ምርት በአውሮፓውያኑ 2020 እና 2021 መካከል በ35 በመቶ ጨምሯል ብሏል።

እንደ መንግሥታቱ ድርጅት ቢሮ ከሆነ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኮኬይን ምርት እና የተጠቃሚዎች መጠን ብቻ ሳይሆን ከፍ ያለው፤ የአደንዛዥ ዕጹ መተላለፊያ መንገዶች ቁጥርም ጨምሯል።

ሪፖርቱ በምዕራብ እና በመካከለኛው አፍሪካ አዲስ የአደገኛ ዕጽ ማስተላለፊያ መስመሮች መከፈታቸውን አጋልጧል።

ከዚህም በተጨማሪ ሪፖርቱ ዕጽ አዘዋዋሪዎች በሕግ የተከለከለውን ምርት በዓለም አቀፍ የፖስት አገልግሎት አማካይነት ጭምር ለማንቀሳቀስ እየተጠቀሙ መሆኑን ገልጿል።

በአጠቃላይ ሪፖርቱ አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ የኮኬይን ትልቁ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ያሳየ ሲሆኑ፤ ከሁለቱ አህጉራት በመቀጠል ደቡብ እና ማዕከላዊ አሜሪካ እንዲሁም የካረቢያን አገራት የኮኬይን ምርት መዳረሻ ናቸው።

ምንም እንኳ በአፍሪካ እና እስያ አህጉራት የኮኬይን ገበያ ‘አሁንም የተገደበ’ ቢሆንም የገበያ መስፋፋት ዕድሉ ግን አደገኛ አውነታ ነው ሲሉ የድርጅቱ አጥኚ ቡድን ባልደረባ ጋዳ ዋሊ ተናግረዋል።

ሪፖርቱ የኮኬይን ምርት እንዲጨምር ሁለቱ ዋነኛ ምክንያቶች የኮካ ተክል ምርት መጨመር እንዲሁም ተክሉን ወደ የኮኬይ ዱቄት ለመቀየር ጥቅም ላይ የሚውለው አሰራር ላይ መሻሻል መምጣቱ ነው ተብሏል።

በኮቪድ-19 ወረርሽን ምክንያት የእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት የኮኬይን ዝውውር ተቀዛቅዞ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ይፋ የሆኑ አሃዞች ግን የኮኬይን አቅርቦት ከምንጊዜውም በበለጠ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳያል ይላል ሪፖርቱ።

ይህም ብቻ አይደለም ፀጥታ አስከባሪዎች በሚያደርጓቸው ፍተሻዎች የሚያዘው የኮኬይን መጠን በከፍተኛ መጠን ጨምሯል።

ኮሎምቢያ አሁንም ከፍተኛ ዝውውር የሚደረግባት አገር ሆና ቀጥላለች። በአውስትራሊያ ደግሞ በእአአ 2020 ላይ የኮኬይን ተጠቃሚዎች ቁጥር በ50 በመቶ ጨምሮ ነበር።

በጠጣር መልክ የሚቀርበው ኮኬይን ተጠቃሚዎች ቁጥር በዩናይትድ ኪንግደም፣ በቤልጂየም፣ በፈረንሳይ እና በስፔን ጨምሯል።