ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን
የምስሉ መግለጫ,ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

17 መጋቢት 2023

የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የእስር ትዕዛዝ አወጣ።

ፕሬዝዳንቱ ህጻናትን በሕገወጥ መንገድ ከዩክሬን ወደ ሩሲያ ማፈናቀልን ጨምሮ በጦር ወንጀሎች ተጠያቂ ናቸው ሲል ነው የእስር ትዕዛዙን ያወጣባቸው።

እነዚህ ወንጀሎች የተፈጸሙት ሩሲያ በዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ ከከፈተችበት ካለፈው ዓመት የካቲት አጋማሽ ጀምሮ መሆኑንም አሳውቋል።

ሩሲያ ግን በወረራው ወቅት ተፈጽመዋል የተባሉን የጦር ወንጀሎችን ውድቅ አድርጋለች።

ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ፑቲን ህጻናትን በማፈናቀል እጃቸው አለበት በሚል ክስ የመሰረተው በድርጊቱ በቀጥታ በመሳተፍ እንዲሁም ከሌሎች ጋር እንደፈጸሙት የሚያሳምን በቂ ምክንያት እንዳለው አመልክቷል።

በተጨማሪም የሩሲያው መሪ ህጻናቱን ከዩክሬን የሚያባርሩ ሌሎች አካላትንም ለማስቆም ያላቸውን ሥልጣናቸውን ሳይጠቀሙ እንደቀሩ ነው ፍርድ ቤቱ ያሳወቀው።

ከፕሬዝዳንት ፑቲን በተጨማሪ የሩሲያ የህጻናት መብት ኮሚሽነር ማሪያ ሎቮቫ-ቤሎቫም በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ተፈላጊ ሰው ሆነዋል።

በፕሬዝዳንቱም ሆነ በኮሚሽነሯ ላይ የፍርድ ቤቱ የእስር ትዕዛዝ ቢወጣም፣ ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎችን የመያዝ ሥልጣን ግን የለውም።

ይህ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት የሚያወጣው ትዕዛዝ ተፈጻሚ የመሆን መብት ያለው ባቋቋሙት እና ስምምነት በፈረሙ አገራት ውስጥ ብቻ ነው።

ሩሲያ የዚህ ስምምነት ፈራሚ አይደለችም፤ ስለዚህ የፕሬዝዳንት ፑቲን ለፍርድ ቤቱ ተላልፎ የመሰጠት ጉዳይ የመነመነ ነው።

ሩሲያ በበኩሏ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ ምንም ትርጉም የለውም ብላለች።

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ በተደጋጋሚ የሚቀርቡባትን መጠነ ሰፊ ጥሰቶች ክስ በተደጋጋሚ ውድቅ ስታደርግ ቆይታለች።

ክሬምሊን ዓለም አቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ስልጣን እንደማይቀበል እና በዚያም ለመታዘዝ ምንም ዓይነት ግዴታ እንደሌለበት በተደጋጋሚ ሲያሳውቅ ቆይቷል።

ፍርድ ቤቱ በፑቲን ላይ ያወጣውን የእስር ትዕዛዝ ተከሎም የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ“ ምንም ፋይዳ የለውም” ብለዋል።

“ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የ|ሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች ለአገራችን ምንም ትርጉም የላቸውም፣ ከህግ አንፃርም ጭምር”በማለት ቃለ አቀባይዋ ማሪያ ዛካሮቫ በቴሌግራም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።