
ከ 7 ሰአት በፊት
በትግራይ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ከሁለት ዓመታት በላይ ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶችን እንደገና ለመክፈት ዕቅድ መውጣቱ ተገለጸ።
ትምህርት ቤቶቹ ለሦስት ዓመት ያህል ተዘግተው ቆይተዋል።
ከሁለት ዓመት በላይ በዘለቀው ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት በክልሉ ያሉ በርካታ ትምህርት ቤቶች ተዘርፈዋል እንዲሁም ወድመዋል።
በትግራይ ከሚገኙት ትምህርት ቤቶች ሩብ የሚሆኑት በጦርነቱ ወቅት ጉዳት እንደደረሰባቸው የአውሮፓውያኑ 2021 የሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት ያሳያል።
መምህራንም ለሁለት ዓመታት ደመወዝ አልተከፈላቸውም።
ትምህርት ቤቶቹን በመጪው ሚያዝያ ወር እንደገና ለመክፈት ዕቅድ እንደተያዘም የዩኒሴፍ የትምህርት ኃላፊ ቻንስ ብሪግስ ለቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ሬዲዮ ተናግረዋል።
“በትግራይ ሙሉ በሙሉ የትምህርት ሥርዓቱ ፈርሷል። ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ 2.3 ሚሊዮን ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸው የሚያሳይ መረጃ አለን” ሲሉ ኃላፊው አክለዋል።
- ብሊንከን በጦርነቱ ለተፈጸሙ ጥሰቶች ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጠየቁ15 መጋቢት 2023
- በትግራይ እና በኦሮሚያ ካጋጠመው የጥሬ ገንዘብ እጥረት ጀርባ ያሉ ምክንያቶች16 መጋቢት 2023
በትግራይ መዲና መቀለ ከባለቤታቸው እና ከአራት ልጆቻቸው ጋር ነዋሪ የሆኑት አቶ መንግሥት ገብረመድኅን ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ የእርስ በርስ ጦርነቱ በተቀሰቀሰበት ወቅት ሁለቱ ልጆቻቸው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ይከታተሉ ነበር።
ትምህርት ከተቋረጠም በኋላ “እነሱን ለማስተማር ሞከርኩ፣ ነገር ግን መረጋጋት እና ትኩረታቸውን መሰብሰብ አልቻሉም። የአየር ጥቃቶች እና የድሮን ጥቃቶች ድምጽ ይሰማሉ። ህጻናቱን ጠመንጃ ይዘው የሚሄዱ ወታደሮችንም ያያሉ። እነሱንም ለማስመሰል ይሞክራሉ” ብለዋል።
በመቀለ ዩንቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት አቶ መንግሥት ለወራት ደመወዝ ሳይከፈላቸው ቆይተዋል።
“ደመወዛችን አየተሰጠን ስላልነበር ልጆቻችን ምን እንደምንመግባቸው ያስጨንቀን ነበር። ስለዚህ እነሱን በማስተማር ላይ ማተኮር ፈታኝ ነበር። ነገር ግን ትናንትና ደመወዜን ተቀበልኩ፣ አሁን ለልጆቼም ልብስ እና ምግብ መግዛት እችላለሁ” ብለዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት ተቀስቅሶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን ለቀጠፈውና በሚሊዮኖች ሕይወት ላይ ከባድ ሰቆቃን ያደረሰው ደም አፋሳሽ ጦርነት ከአራት ወራት በፊት መቆሙ ይታወሳል።
ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ መደረሱ ስምምነት ደርሰዋል።