ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን

ከ 8 ሰአት በፊት

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በሩሲያ አቻቸው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላወጣው የእስር ማዘዣ ድጋፋቸውን ሰጡ።

ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ፑቲንን በዩክሬን የጦር ወንጀል በመፈጸም የከሰሳቸው ሲሆን ፕሬዚዳንት ባይደንም የሩሲያው መሪ “በግልጽ” ፈጽመውታል ብለዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ወረራ ከፈጸመች በኋላ ሕጻናትን ከዩክሬን ወደ ሩሲያ በህገወጥ መንገድ አፈናቅላለች የሚልም ክስ ቀርቦባታል።

ሞስኮ ይህንን ውንጀላ ውድቅ አድርጋ የእስር ትዕዛዙንም ‘አሳፋሪ’ ስትል ወቅሳለች።

ዓለም ዓቀፉ ፍርድ ቤት የአንድ አገር መንግሥት ካልተባበረው ተጠርጣሪዎችን የማሰር ስልጣንም ስለሌለው እርምጃው ሊያመጣ የሚችለው አዲስ ነገር የለምም እየተባለ ነው።

ሩሲያ የአይሲሲ ፈራሚም ሆነ አባል ባለመሆኗ ፍርድ ቤቱ በአገሪቱ ላይ ምንም ዓይነት ስልጣን የለውም።

ሆኖም የእስር ትዕዛዙን ፕሬዚዳንቱ በተለያየ መንገዶች ሊጎዳቸው እንደሚችልም ተጠቅሷል፤ ለምሳሌም ያህል የዓለም አቀፍ ጉዞዎችን ማድረግ አለመቻል አንዱ ነው።

ፍርድ ቤቱን ካቋቋሙትና ፈራሚና አባል ከሆኑት 123 አገራት ውስጥ አንዱን ከረገጡ ሊታሰሩ ይችላሉ።

ፕሬዚዳንት ፑቲን በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸው ሶስተኛው መሪ ናቸው።

ፕሬዚዳንት ባይደን ፍርድ ቤቱ በአሜሪካ ውስጥ ምንም አይነት ስልጣን ባይኖረውም የእስር ማዘዣው መውጣቱ “ጠንካራ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ተናግረዋል።

አስተዳደራቸው ቀደም ሲል በዩክሬን በቀጠለው ጦርነት ሩሲያ የጦር ወንጀሎችን መፈጸሟን በይፋ ያወጀ ሲሆን ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ ከጥቂት ወራት በፊት ተሳታፊዎች “ተጠያቂ ይሆናሉ” ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ባወጣው ሪፖርት ሩሲያ ዩክሬናውያን ህጻናትን በቁጥጥሯ ስር ካሉ አካባቢዎች ማፈናቀሏን አስታውቆ ይህም የጦር ወንጀል መሆኑን አረጋግጧል።

ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ፑቲን ህጻናትን በማፈናቀል እጃቸው አለበት በሚል ክስ የመሰረተው በድርጊቱ በቀጥታ በመሳተፍ እንዲሁም ከሌሎች ጋር እንደፈጸሙት የሚያሳምን በቂ ምክንያት እንዳለው አመልክቷል።

በተጨማሪም የሩሲያው መሪ ህጻናቱን ከዩክሬን የሚያፈናቅሉ ሌሎች አካላትንም ለማስቆም ያላቸውን ሥልጣናቸውን ሳይጠቀሙ እንደቀሩ ነው ፍርድ ቤቱ ያሳወቀው።

የሩሲያ የህጻናት መብት ኮሚሽነር ማሪያ ሎቮቫ-ቤሎቫም በተመሳሳይ ወንጀል በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ተፈላጊ ሰው ሆነዋል።

የአይሲሲ አቃቤ ህግ ካሪም ካን የእስር ቤት ትዕዛዙ “በማስረጃዎች፣ በምርመራ እና በሁለቱ ባለስልጣናት በተነገሩ መግለጫዎች ላይ የተመሰረቱ ናቸው ብሏል።

ፍርድ ቤቱ መጀመሪያ ላይ የእስር ማዘዣውን በሚስጥርነት ሊይዘው አስቦ የነበረ ቢሆንም ተጨማሪ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ እና እንዲቆሙ ለማድረግ በሚል ለህዝብ ይፋ ለማድረግ ወስኗል።

“ህጻናት እንደ የጦር ምርኮ ተደርገው ሊወሰዱ አይችሉም፣ ሊፈናቀሉ አይችሉም”በማለት አቃቤ ህጉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ይህ ዓይነቱ ወንጀል መሆኑን ለመረዳት አንድ ሰው ጠበቃ መሆን አያስፈልገውም። በጣም አጸያፊ እንደሆነ መታወቅ አለበት” በማለት አክለዋል።