አቶ ጌታቸው ረዳ

ከ 3 ሰአት በፊት

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ትናንት አርብ መጋቢት 08/2015 ዓ.ም. ባካሄደው ምርጫ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳዳር ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ መምረጡ ተነገረ።

አቶ ጌታቸው ረዳ አዲስ የሚቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳዳር ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ በህወሓት መመረጣቸውን የትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ዘግቧል።

በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ከወራት በፊት በፕሪቶሪያ በተደረሰው ግጭትን በዘላቂነት ለማቆም በተደረሰው ስምምነት መሠረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሰረት ተወስኗል።

ህወሃት የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ካዋቀረ በኋላ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት በፌዴራል መንግሥት መጽደቅ አለበት።

በሚዋቀረው ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የሚኖርን ውክልናን በተመለከተ 30 በመቶ ለህወሓት፣ 25 በመቶ ለትግራይ ሠራዊት፣ 15 በመቶ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ቀሪው ለምሁራንና ለሲቪክ ማህበራት እንደሚሰጥም ከዚህ ቀደም መገለጹ ይታወሳል።

ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በሰላም ስምምነቱ ተደራዳሪ ከነበሩ ባለሥልጣናት ጋር መነጋገራቸው የሚታወስ ነው።

የፌደራሉ መንግሥት ዋነኛ ተደራዳሪ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የህወሓት ተደራዳሪ እና ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር በተነጋገሩበትም ወቅት፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መመሥረት የስምምነቱ ቁልፍ ተግባር አድርገው ማየታቸው ተጠቅሷል።

በዚህ ውይይትም ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነቱ እንዴት እየሄደ እንደሆነ የተገመገመ ሲሆን፣ ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እንደሚቀሩ መስማማታቸው ተገልጿል።

ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ጋር ስለነበራቸውም ቆይታ የተናገሩት አቶ ጌታቸው ረዳ “ለሰላም ያለንን የማያወላውል ቁርጠኝነት አረጋግጠናል። ሰላሙን ለማደፍረስ የተነሱ ኃይሎችን ጨምሮ በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን ስቃይ ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ያሉትን እንቅፋቶችን ለመፍታት ጊዜያዊ አስተዳደር መመሥረትን ጨምሮ የበኩላችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን” በማለት በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግሥት ምሥረታ ጋር ተያይዞ ምሥረታውን ለማካሄድ የተቋቋመው አስተባባሪ ኮሚቴ ከትግራይ ተቃዋሚዎች በኩል ተቃውሞ እንደተነሳበት መገለጹ ይታወሳል።

ሳልሳይ ወያነ፣ ባይቶና እና የትግራይ ነጻነት ፓርቲዎች በኮሚቴው ላይ የገለልተኝነት እና የአሳታፊነት ጥያቄ በማንሳት ከሂደቱ ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታውቀዋል።

ኮሚቴው የትግራይ ኃይሎች አዛዥ ሌ/ጄኔራል ታደረሰ ወረደ እና አቶ ሙሉ ወርቅ ኪዳነማርያምን ጨምሮ ዘጠኝ አባላት ያሉት ሲሆን፣ ሦስት ከትግራይ ኃይሎች፣ ሦስት ከህወሓት እና ሦስት ከሲቪክ ማኅበራት የተውጣጡ መሆናቸው በወቅቱ ተገልጿል።

ጊዜያዊ መንግሥቱን ለመመሥረት የሚከናወነው የሥራ ሂደት ሁሉንም አሳታፊ እንደሆነ እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበራት፣ ሕዝብን ያሳተፈ እና ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ በሆነ ሁኔታ ለማካሄድ እንደተሞከረም ተገልጿል።

ሆኖም በአንድ ፓርቲ – በህወሓት የተመረጡ ናቸው በማለት የሰላ ትችት ሲዘነዝሩም የቆዩት ተቃዋሚዎቹ በጊዜያዊ አስተዳዳሩ ላይ በተጀመረው ሕዝባዊ ውይይትም ላይ ሳይሳተፉ ቀርተዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት ተከስቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን ለቀጠፈውና በሚሊዮኖች ሕይወት ላይ ከባድ ሰቆቃን ያደረሰውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መካከል ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ወር ላይ መደረሱ ይታወሳል።

ጥቂት ስለ አቶ ጌታቸው ረዳ

ትግራይ ውስጥ ለሁለት ዓመታት ከተካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ ስማቸው በተደጋጋሚ ሲጠቀስ ከነበሩ ሰዎች መካከል ጌታቸው ረዳ አንዱ ናቸው። አቶ ጌታቸው የትግራይ ኃይሎችን በመወከል በጦርነቱ ሂደት ውስጥ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ላይ በተደጋጋሚ ሲቀርቡ ቆይተዋል።

ጌታቸው ረዳ በፓርቲ፣ በክልል እንዲሁም ፌደራል መንግሥቱ ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ ሰርተዋል። የትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲ ሆኖ በቆየው ህወሓት ውስጥ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፣ የፕሬዝዳንቱ ረዳት እና የፓርቲው ቃል አቀባይ ሆነው ሲሰሩ ቆይተዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ከፍተኛ አማካሪ ሆነው ከመሥራታቸው በተጨማሪ፣ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትርም እና በሌሎች የኃላፊነት ቦታዎችም ሠርተዋል።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው አቶ ጌታቸው ከአሜሪካው የአላባማ ዩኒቨርስቲ ደግሞ በሕግ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በዚሁ ዘርፍ በመቀለ ዩኒቨርስቲ መምህር ሆነው ሠርተዋል።

አቶ ጌታቸው በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ ሄዶ ወደ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ተሰማርተው ከነበሩት የቡድኑ ፖለቲካዊ አመራሮች መካከል አንዱ ሆነው ቆይተዋል።

በጦርነቱ ወቅት የትግራይ ኃይሎችን የተመለከቱ መረጃዎችን ለዓለም አቀፉ የመገናኛ ብዙኃን እና በማኅበራዊ ሚዲያ በትግርኛ፣ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ሲያርቡ፣ ሲወያዩ እና ሲከራከሩ በስፋት ይታወቃሉ።

ከዚህ ባሻገርም ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስቆም ያስቻለው በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል በተደረገው ድርድር ወቅት የትግራይን ወገን በመወከል የተሳተፉ እንዲሁም የፈረሙ አቶ ጌታቸው ረዳ ናቸው።