
+ኦርቶዶክስ ወንጌል አትሰብክም+
ብዙ ጊዜ ወንጌል መስራት ማለት መጽሐፍ ቅዱስን እያንዳንዱ ሰው እንዲያነበው ማድረግ ማለት ይመስለናል ይሄ ፍጹም ስህተት ነው። ስህተት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከፕሮቴስታንት ተጽዕኖ የመጣም ጭምር ነው።
ወንጌል ከLiteracy ጋር ቀጥታ ተዛምዶ የለውም። ሐዋርያት በነበሩበት የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን አብዛኛው አማኝ ማንበብና መጻፍ አይችልም። ይሄም ብቻ ሳይሆን መጽሐፉም ተጽፎ አላለቀምና ይሄ ነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚሉት ጥራዝም አልነበራቸውም። ወንጌል ገብቷቸው ነበር ወይ ካልን አዎ!
ወንጌል ምንድነው? ካልን የምስራች ነው። ስለጌታችን መምጣት ሰው መሆን መመላለስ መጠመቅ መሰቀል መሞት መነሳትና በክብር ማረግ ስለ ሰው ልጅ መዳን የተነገረ የምስራች ነው። ወንጌል ስለ ልጁ ነው የሚለንም ለዚህ ነው። ስለ ልጁ የሚያወሩ ሰዎች ብቻ ግን አላፈሩም። አላማው ክርስቶስን መምሰል ነበር። ለሞተልን መሞት። የዘመኑ ክርስቲያኖች ለስሙ ሞቱ። ለተገባላቸው ቃል ህይወታቸውን ሰጡ። ይሄ ነው ምስክር እንዲሆነን ለስሙ ምስክር መሆን። (ሰማዕት ማለት ምስክር ማለት ነው)
+ወንጌል ይለውጣል+
በመጀመሪያው ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ወንጌልን ሲሰሙ ምን ሆኑ? ተለወጡ። ጴጥሮስ አሳ አጥማጅ ነበር ተለውጦ ሐዋርያ ሆነ። ከስቅለት በፊት ክዶት ነበር ተለውጦ የሐዋርያት አለቃ ሆነ። ቀረጥ ቀራጩ(tax collector) ማቴዎስ ሰው ሁሉ ከሚጠላው የደሀን ገንዘብ ከሚበላ ለሮማውያን ካደረ የቀራጭነት ማንነት ተለውጦ ሐዋርያ ሆነ። ጭራሽ ጸሐፌ ወንጌል ሆነ። ወንጌል ይለውጣል ማለት ይህ ነው። የሰማ ክርስቶስን ወደ መምሰል ይለወጣል። እርሱ ቅዱስ ነውና ወንጌል የለወጣቸው በወንጌል Brag ወደማድረግ አልመጡም። በጣም ትሁትና የክርስቶስ ልብ ያላቸው ሆኑ። ዓለምን ናቁ ከስጋና ከምኞታቸው ታገሉ። እንጂ ጥቅስ ሸምድዶ ሰው መከራከርና አውቃለሁ በማለት ከሁሉ ለምትበልጠው የego ኃጢአት ራሳቸውን አልሸጡም። የተለወጠ ሰው selfless እንጂ ሰው ጠል አይደለም። እኒህ ሐዋርያት የቤተክርስቲያን መሠረት ተባሉ። እኛም የነዚህ ልጆች ነን።
+ቤተክርስቲያን ምን ሰራች?+
ሰው የሚለወጠው ቅዱሱን ወንጌል(የምስራች) በመስማት እና በመኖር ነው። እምነት ከመስማት ነው። መስማትም በእግዚአብሔር ቃል።
ቤተክርስቲያን ወንጌል ሰራች!
ልክ እንደ ዘመነ ሐዋርያት በዘመናት ለሰው ልጅ ያልተቋረጠ ምስክርነት የምትሰጥ ቤተክርስቲያን አለች። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትም ዛሬም ያው ነው። የማይለወጥ ክርስቶስ ያለባት በዘመን መሠረተ እምነት የማትቀያይር “ኦርቶዶክስ” የሆነች የቀናች ቤተክርስቲያን ባልተቋረጠ ምስክርነት ክርስቶስን በማሳየት አሁንም አለች። ቤተክርስቲያናችን መኖሯ በራሱ እንዲሁ የወንጌል ምስክርነት ነው። ወንጌል ምን አለ?
“እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” የማቴዎስ ወንጌል 28: 19-20
ደረጃ በደረጃ እንየው።
ሂዱና አሕዛብን ሁሉ:- ሂዱ ስለተባለች ሐዋርያዊት ናት። ሖረ ማለት ሄደ ነው። ቤተክርስቲያን መሄድ ስራዋ ነው።
እያጠመቃችሁ:- ዓለምን ሁሉ ያጠመቁት እኒህ አባቶቻችን ናቸው። ልጆቻቸውም አሁንም ክርስትና በሌለበት እየገቡ የምስራቹን እየነገሩ ያጠምቃሉ። The living church የምንላት ለዚህ ነው።
ያዘዘእኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ:- ላመኑት የሚያስፈልገው ከፍቅር ጋር ትዕዛዙን መጠበቅ ነውና አሁንም በተደጋጋሚ ትዕዛዙን ጠብቁ ትላለች( አንዱ የምንተችበት ነገር ቢሆንም። መ*ና*ፍ*ቃኑ ኦርቶዶክስ ስለክርስቶስ ሳይሆን ስለህግ ነው የምትሰብከው ዘንድሮም ይላሉ። እኛ ደግሞ አማኝ ማመኑን የሚገልጠው በመታዘዝ ነው እንላለን። ብትወዱኝ ትዕዛዜን ጠብቁ ነው ቁም ነገሩ።)
እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ከናንተ ጋር ነኝ:- ይሄ ትልቅ እውነት። ክርስቶስ ከቤተክርስቲያን ጋር ነው። ሁሌም ይጠብቃታል። ሁሌም ይመራታል። ክርስቶስ ስለማይለወጥ ያው ስለሆነ ቤተክርስቲያን በሺህ ዘመናት ያው ሆና ሳትለወጥ መኖሯ ክርስቶስ ከርሷ ጋር እንዳለ መግለጫዋ ነው።
ቤተክርስቲያን እንዲሁ ራሱ ወንጌል ናት። ኦርቶዶክሱ ወንጌል ተሰብኮታል። ገና ከቤተክርስቲያኑ በር እስከ ውስጥ መቅደስ እውቀትና ምጥቀት ባይኖርህ እንኳን በትንሽ ማስተዋል ክርስቶስን የሚሰብክህ ነገር ብዙ ነው። ሳር ቅጠሉ ወንጌል ነው። (አበዛኸው አትበለኛ! ሳሩ ምሳሌ ስላለው ነውኮ! በቤተክርስቲያን ያለ ሳር በምዕመናን ይመሰላል። ቆጥረህ አትጨርሰውም። ቤተክርስቲያን ለክርስቶስ የምትማርከው ነፍስም ቁጥር የለውም።)
ደክሞህ አንዱ ዛፍ ስር ጥላ ከተጠለልክ ወንጌል ነው። “ እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎቼ ናችሁ” የተባለላቸው ቅዱሳን ምሳሌ ነው። በጌታችን ግንድነት በቅርንጫፍነታቸው ያስጠልሉሀል። ራቅ ብለህ ከቆምክ ወንጌሉን ያሳልሙሀል። ምን የተከበርክ ብትሆን ትንሽዬ ህጻን ልጅ ለያዘው ወንጌል ስትል በአሳላሚው ህጻን ፊት ሸብረክ ብለህ ትጎነበስና ትሳለማለህ።
የታሸገ ውኃ በልዩ መጠጫ አማርጠህ እንኳ ብትጠጣ ከህዝቡ ጋር ተጋፍተህ ጠብታ ጸበል ሁሉም በሚጠጣበት ተራ የፕላስቲክ እቃ ትጠጣለህ። ክርስቶስ እኩል ያደርግሀል። ሰው ያደርግሀል። ቤተክርስቲያን “እከሌነትህን” ሳይሆን ልጅነትህን ትመሰክራለች። ለሷ “አምሳለ ክርስቶስ” እንጂ ባለስልጣን ወይ ባለሀብት አይደለህም።
በደንብ ከተጠጋህ ደግሞ ስጋ መለኮት ደመ መለኮት ተደግሶ ይጠብቅህና በልተህ ትድናለህ። አባትህ አዳም በልቶ እንደሞተው። ወንጌል ይሄ ነው። ትለወጣለህ። ነፍሰ ገዳይ ብትሆን ለዚህች ቅጽበት ትንቀጠቀጣለህ። ኃጢአተኛ ብትሆን ለዚህች ቤት ትማረካለህ። ቢያንስ እስክትወጣ ትህትናህና ሰዋዊ ማንነትህ ከፍ ያለ የመለወጥ ብልጭታ ይታይብሀል። ስትወጣ ይሄን ማንነት ይዘህ ከወጣህ ቅድስና ተጀምሯል ብለህ ቁጠረው።
ጠቅለል ለማድረግ
መጽሐፍ ቅዱስ ሳይኖር ቤተክርስቲያን ነበረች። መጽሐፍ ቅዱስን የጻፈችው ቤተክርስቲያን ናት። መጽሐፍ ቅዱስ ኖሮም ሳይኖርም ቅዱሳን አሉ። ክርስቶስን መምሰል አለ። ምን ለማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የቤተክርስቲያን መለኪያ ሳይሆን ቤተክርስቲያን ናት የመጽሐፍ ቅዱስ መለኪያ።
የክርስትና ፍጻሜው ጥቅስ ማወቅ አይደለም። ክርስቶስን መምሰል ነው። ክርስቶስን በመምሰል ሂደት ውስጥ ግን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ትልቅ ሚና አለው። የማያነብ ነው ግን ወዮለት የሚለው ኦርቶዶክሳዊ አይደለም። ፕሮቴስታንታዊ እንጂ።
“ ያመነ የተጠመቀ” ስለሚል መጀመሪያ ሰው የግድ ማመን አለበትና ህጻናትን እንዴት ታጠምቃላችሁ ሲያድጉ አይሻልም? ለሚሏችሁ አንድ የአእምሮ ህሙም ቢገጥማችሁ እንዴት መጽሐፍ ቅዱስ አስተምራችሁ ልታሳምኑልኝ ነው በሉልኝ። እና መቼ ሊጠመቅ ነው?
ወንጌል በመማርና አለመማር በሀብትና ድህነት በእድሜና በጾታ ሲወሰን ክርስትናው ምዕራባዊ መለኪያው ፕሮቴስታንታዊ ይሆናል።
በ ኦርቶዶክስ “ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ” ስለሚል ሀብትና ድህነት አይለየውም። “ ህጻናትን ወደኔ ይመጡ ዘንድ አትክልክሏቸው” ስለሚል እድሜ አይለየውም። “ሴቶች አስገረሙን” ስለሚል ጾታ አይለይም። ክርስትናው ምስራቃዊ መለኪያው ክርስቶስ ነው።( ምስራቅ የፀሐይ መውጫ ምሳሌው ፀሐይ ክርስቶስ መውጫው በሁሉ ንጽኅት የምትሆን ድንግል ማርያም)
ኦርቶዶክስ ወንጌል ላይ አልሰራችም ማለት በጣም ትልቅ ይቅር የማይባለእ ስህተት ነው። ነውር ነው። ዓለም በሙሉ ክርስትናን የተቀበለው ኦርቶዶክስ በመላው ዓለም መንበር ዘርግታ ዞራ በማስተማሯ ነው። በሀገራችንም እንዲሁ ቢያንስ ዞረህ የምትወጋት የክርስቶስ ቤተክርስቲያን አሁን ያለህበትን አሁን ያለህበትን ሰዋዊ ከፍታ ሰርታ ነው ሰው ያደረገችህ።
ተገቢው ጥያቄ (ቢሆን ደስ የሚለኝ)
አሁን ያለው ትውልድ ከአለመማር ወደ መማር የመጣ ማንበብ መጻፍ የሚችል ነውና መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠና እናድርገው ማለት ይገባል። ከማን ጋር ያንብብ ካልን አሁንም ከመጽሐፉ ጸሐፊ ከቤተክርስቲያኗ ጋር።
ይሄነው ትክክለኛ ቀኖና ብላ መጽሐፍ ቅዱስን ጽፋ ሰፍራ የሰጠችን ቤተክርስቲያን አልሰበክሽም ማለት ከትቢያ ከጭቃ ሰው ያረገህን እግዚአብሔር በሜካፕ እንደመፎካከር ይመስላል።
የጻፈችውን ተቀብለህ ይሄ ነው ካልክ ዘንዳ ተርጉማም ስታስረዳህ አሜን ብሎ መቀበል ከዝንጀሮ ከፍ የሚያደርግ ጢኒጥዬም ቢሆን intellect አለህ ያስብላል። “ማንም እንደ ገዛ ፈቃዱ እንዲተረጉም አልተፈቀደምና”
Deacon Esdros Haile