March 19, 2023 – BBC Amharic 

አንዲት እርጉዝ እናት

19 መጋቢት 2023, 08:05 EAT

አሜሪካ በዓለም ላይ ካሉ ሀብታም አገራት መካከል ለወላድ እናቶች በጣም አደገኛዋ እንደሆነች እንደቀጠለች የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) ሪፖርት አመለከተ።

ሲዲሲ ይፋ ባደረገው አዲስ መረጃ መሠረት በአገሪቱ ውስጥ የወላድ እናቶች ሞት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከፍተኛው ደረጃ ላይ በደረሰበት ጊዜ በ40 በመቶ ከፍ ብሏል።

በአውሮፓውያኑ 2021 ከ100,000 ወላድ እናቶች መካከል 33ቱ ከወሊድ ጋር በተያያዙ ችግሮች ምክንያት ለህልፈት ተዳርገዋል። ይህ አሃዝም ቀደም ባለው ዓመት ከነበረው 23.8 በመቶ ከሰባት በመቶ በላይ በሆነ መጠን ነው ያሻቀበው።

ይህ አሃዝ ደግሞ በጥቁሮች ዘንድ ሲሆን ከእጥፍ በላይ ነው። በዚህም ጥቁር እናቶች ከነጮቹ በሦስት እጥፍ በላቀ ሁኔታ በወሊድ ምክንያት ለህልፈት የመዳረግ ዕድል እንዳላቸው ማዕከሉ አመልክቷል።

በአሜሪካ ያለው የእናቶች ሞት ከሌሎች ያደጉ አገራት ጋር ሲነጻጸር በዩናይትድ ኪንግደም፣ በጀርመን እና በፈረንሳይ ካለው በሁለት እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን፤ በስፔን፣ በጣሊያን፣ በጃፓን እና በሌሎች አገራት ካለው ደግሞ በሦስት እጥፍ የላቀ መሆኑን የዓለም ባንክ የቅርብ ጊዜ መረጃ ያመለክታል።

ይህ የእናቶች ሞት ከአውሮፓውያኑ 2000 ወዲህ በአሜሪካ በተከታታይ እየጨመረ መጥቷል። ነገር ግን በሌሎች 37 አገራት ውስጥ መቀነስ ማሳየቱን መረጃው ጠቅሷል።

ከዚህ አንጻር አሜሪካ ወደ ኋላ መቅረቷን የሚናገሩት በለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ የጤና ኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ጆአን ኮስታ አይ ፎንት “በአሜሪካ ዋነኛ ችግር ሆኖ የቆየውን የእናቶች ሞት ኮሮና የበለጠ አባብሶታል” ብለዋል።

ፕሮፌሰሩ ጨምረውም በ2021 (እአአ) በአሜሪካ ውስጥ የወላድ እናቶች ሞት እንዲያሻቅብ ወረርሽኙ፣ የዘር እኩልነት አለመኖር፣ ዝቅተኛ የጤና መድን ሽፋን እና ከፍተኛ የመድን ክፍያ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ይገልጻሉ።

“በአሜሪካ ውስጥ ያለው የመድን ዋስትና አሰራር ነፍሰጡር ሴቶች እንዳይካተቱበት በርካታ እንቅፋቶችን የሚያስቀምጥ ነው” ያሉት ምሁሩ “የኢንሹራንስ ሥርዓቱ ድጋፍ የሚፈልጉትን ችላ ያለ እና ሃብታሞች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነው” ሲሉም ይተቻሉ።

ነገር ግን በዩናይትድ ኪንግደም እና በአውሮፓ ባሉ አገራት እናቶች በህክምና ተቋም ውስጥ ልጅ ለመውለድ ምንም አይነት ክፍያ አይጠየቁም። በአሜሪካ ግን ኢንሹራንስ ያላቸውን ጨምሮ ሌሎቹም ለወሊድ በሺህ የሚቆጠር ዶላር ይከፍላሉ።

አንዲት እርጉዝ እናት

በአሜሪካ ውስጥ ያለው መዋቅራዊ ችግር ለእናቶች ሞት ምክንያት መሆኑን የሚጠቅሱት ፕሮፌሰሩ፣ የኮቪድ ወረርሽኝ ደግሞ ያለውን ችግር የበለጠ አባብሶታል ይላሉ።

“ለጤና የሚጠየቀው ከፍተኛ ክፍያ በቀለም፣ በማኅበራዊ እና በምጣኔ ሀብታዊ አቅም አንጻር ያለውን የኑሮ ልዩነት፣ የእናቶች ሞት መጠንን ለዓመታት ከፍ እያለ እንዲሄድ አድርጎታል” ብለዋል ጆአን ኮስታ አይ ፎንት።

በተጨማሪም በኮቪድ የተያዙ ነፍሰጡር እናቶች ከባድ ህመም ስለሚገጥማቸው ለሞት የመጋለጥ ዕድላቸውን ያሰፋዋል። ከልክ ያለፈ ውፍረት እና የስኳር ህመም ያለባቸው ሴቶች በእርግዝና ወቅት ሞትን ጨምሮ የተወሳሰበ የጤና እክል ይገጥማቸዋል።

“አሜሪካ ውስጥ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የተለያዩ የጤና ችግር ያለባቸው፣ ከፍተኛ የጤና አገልግሎት የሚፈልጉ እና ዝቅተኛ የኢንሹራንስ ሽፋን ያላቸው ናቸው” ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

በተለይ ጥቁር አሜሪካውያን ከልክ በላይ በሆነ ውፍረት ወይም በዚህ ሳቢያ 20 በመቶ የሚሆኑት የደም ግፊት ችግር የማጋጠም ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው። ይህም ሆኖ የጤና ኢንሹራንስ ሽፋን የሌላቸው ጥቁር አሜሪካውያን ከነጮቹ በሁለት ሦስተኛ የበለጡ ናቸው።

የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል የእናቶች ሞት የሚለው በእርግዝና ጊዜ ወይም ከወሊድ በኋላ ባሉት 42 ቀናት ውስጥ የሚከሰትን ህልፈትን ነው።

ባለሙያዎች እንደሚሉት አብዛኛው የእናቶች ሞት የሚከሰተው ከወሊድ በኋላ ባለ አጭር ጊዜ ውስጥ ነው። ለዚህም ምክንያቱ እናቶች የግድ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ሲገደዱ እና ከወሊድ በኋላ የሚያስፈልግ እንክብካቤን ማግኘት ሳይችሉ ሲቀር ነው።

አብዛኞቹ ጥቁር አሜሪካውያን ደግሞ የሚሰሩት ዝቅተኛ ክፍያን በሚያስገኙ እና ትንሽ ወይም ምንም አይነት የጤና ኢንሹራንስ ሽፋን በማይሰጡ፣ እንዲሁም በቂ ያልሆነ የወሊድ ፈቃድ በሌላቸው የሥራ ሁኔታዎች ውስጥ ነው።

የምግብ ምርት አገልግሎቶች በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በጣም አስፈላጊ በመሆናቸው እና ከቤት በመሆን የሚሰሩ ስላልነበሩ በርካታ ጥቁር ሴቶች ለወረርሽኙ እንዲጋለጡ ምክንያት ሆኗል።

በዚህም ሳቢያ በቂ የጤና እንክብካቤ ድጋፍ ስለማያገኙም ከፍተኛ የሞት መጠን እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።

አስፈላጊው ድጋፍ ስለሌላቸው በርካታ ሴቶች በእርግዝና እና ከወሊድ በኋላ ደም መፍሰስ እና የራስ ምታትን የመሳሰሉ ምልክቶች በሚያጋጥማቸው ጊዜ ቀለል አድርገው በመመልከት ወደ ህክምና ተቋማት ለመሄድ አይፈልጉም፤ ይላሉ የሃዋርድ ዩኒቨርስቲ የእናቶች ጤና እና ህክምና ባለሙያዋ ዶክተር ሮቻንዳ ሚሼል።

ጨምረውም “በእርግዝና ወቅት ሁሉም ሰው በእናቲቱ ዙሪያ በመሆን፣ ለእርግዝናው ደስታውን ይገልጻል። ነገር ግን የእናቶች ሕይወት አደጋ ላይ የሚወድቀው ከወሊድ በኋላ ባለው ጊዜ ስለሚሆን ድጋፍ የሚያስፈልገው በዚያ ወቅት መሆን አለበት” ይላሉ ዶክተሯ።

ዝቅተኛ ገቢ በሚያስገኙ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ እናቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ስለማያገኙ፣ በርካታ እናቶች ለጤና ጠንቅ ሊሆኑ የሚችሉ ችግሮች በመጀመሪያ ላይ የሚያሳይዋቸውን ምልክቶች ችላ ይሉታል።

በዚህም ሳቢያ በአሜሪካ የጤና ሥርዓት ላይ ሰፊ ማሻሻያ አስካልተደረገ ድረስ፣ የእናቶች ሁኔታ የመሻሻሉ ነገር የሚመስል አይደለም ብለዋል ዶ/ር ሚሼል።